2023-04-22 19:45:04
ዩኒቨርሲቲው በክረምት ወራት ለሚካሄደው 5ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ 330 ሺሕ የሚበልጥ የአቮካዶ ችግኝ ዝርያ ለተከላ ማዘጋጀቱን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው ባለፉት አራት ዓመታት ባካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ዘመቻ ከ 1 ሚሊየን የሚበልጥ የደን እና የፍራፍሬ ችግኞችን አዘጋጅቶ መትከሉም ተጠቁሟል።
___
ታሪካዊው የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በተካሄደበት ሐምሌ 22/2011 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በዩኒቨርሲቲው ተገኝተው አሻራቸውን ማኖራቸውን ተከትሎ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን ነው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ የገለጹት።
ዩኒቨርሲቲው ባለፉት አራት ዓመታት የደንና የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የፍራፍሬ ዝርያዎች በማፍላት ለተከላ ማዘጋጀቱን፥ ሕብረተሰቡን በማሳተፍ በሶስቱም ካምፓሶቹ መትከሉን እና ለአካባቢው ማሕበረሰብም በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ችግኞችን ተደራሽ ማድረጉን ፕሬዝዳንቱ አሳውቀዋል።
ባለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት በሶስቱም ካምፓሶች፣ ዩኒቨርሲቲው በሚገኝበት የተለያያዩ አካባቢዎች እንዲሁም በሶዶ ዙሪያ ወረዳ ቡጌ ዋንቼ ቀበሌ እየለማ ባለው የደን ይዞታ በመቶ ሺህዎች በሚቆጠር ሄ/ር መሬት በደን እና በፍራፍሬ የችግኝ ዝርያዎች የተሸፈነ መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ ዩኒቨርሲቲው የራሱን ችግኝ ጣቢያ በማቋቋም ባለፉት አራት ዓመታት 1,080,000 የደን እና የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የአቮካዶ፣ ማንጎ እና ፓፓያ ምርጥ ዝርያዎችን በማፍላት ለተከላ ማብቃቱን ነው የተናገሩት።
ዩኒቨርሲቲው በ2014 ዓ.ም በተካሄደ 4ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ብቻ 550,000 የደንና የፍራፍሬ ችግኞችን በማፍላት ለተከላ ማብቃቱን ፕ/ር ታከለ ተናግረው፤ በዓመቱ ከተተከሉት ውስጥ 300,000 የፍራፍሬ እንዲሁም 250,000 የደን እንደሆነም አሳውቀዋል።
«ዐሻራችን ለትውልዳችን» በሚል መሪ ቃል በዩኒቨርሲቲው በተካሄደ 4ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአንድ ጀምበር ከ15 ሺህ የሚበልጥ የአቮካዶ እና የማንጎ ችግኝ ዝርያ መተከሉን ፕሬዝዳንቱ ገልጸው፤ ይህም በሀገር ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በፍራፍሬ ችግኝ ላይ የተመሰረተ የ 30-40-30 ፕሮጀክት ጅምር ተግባር መሆኑን አብራርተዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ልማት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ እና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ከመግንባት ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ፕ/ር ታከለ የተናገሩ ሲሆን፤ ዩኒቨርሲቲው የሚበሉ የፍራፍሬ ዝርያዎች ላይ በማተኮር በቀጣይ ክረምት ለሚካሄደው 5ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 330 ሺሕ የአቮካዶ ፍሬ እያፈላ ይገኛል ብለዋል።
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲው የአረንጓዴ አሻራ ልማት የችግኝ የፅድቀት መጠን በ2011 ዓ.ም 85.98 በመቶ፣ በ2012 ዓ.ም 88.50 በመቶ፣ በ2013 ዓ.ም 88.24 በመቶ እና በ2014 ዓ.ም ደግሞ 90 በመቶ መሆኑን ከዩኒቨርሲቲው አረንጓዴ አሻራ ፕሮጀክት ዳይሬክቶሬት የተገኘ መረጃ ያመላክታል።
ዕውቀትን በተግባር!!
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት
1.2K views16:45