2021-12-13 10:12:27
ትልቅ ሰው ሁሌም ትልቅ ነው!
(ሚካኤል አስጨናቂ)
ያደኩባት ከተማ ውስጥ እጅግ ትታወቅ የነበረች ጠጅ ቤት ነበረች።
አቤት ያቺ ጠጅ ቤት ስራ የጀመረች ጊዜ መቼም ዓለም ነበር !...ከሩቅ ሰፈር ድረስ የመጡ እንግዶች ጠባቧን ቤት ይሞሏታል።
ከቤቷ የተትረፈረፉ አርፋጆችም ግቢ ውስጥ የሚገኝ ጥላ ይመርጡና ቁጭ ብለው ይሸርባሉ :)
በረከታሙ ግቢ የውጭውን በር አለፍ ብለው ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ጀምሮ መዓዛው ያውዳል። እኔ ልጅ ሆኜ ብዙ ጊዜ እዛ ቤት ስላክ ደስ ይለኝ ነበር። አባዬ ከጓደኞቹ ጋር ቁጭ ብሎ አንድ ሁለት ብርሌውን ሲልፍ ጊዜ ተካፋች የሞባይል ስልኩን ያነሳና ይደውላል።
ሄሎ.. . (እናቴ ስልኩን ታነሳዋለች)
እናቴ.. . (አባዬ እናቴን የሚጠራት እንደዚህ ብሎ ነው )
እሺ.. . ቤት አይመጣም?
(ጋሼ ምን እንደሚላት እንጃ ፈገግ ትላለች)
እሺ.. .
አዎ ...አለች ያቺኛዋ ጄሪካን...
እህ?
እሺ.. .እሺ.. .
እሺ በቃ ይመጣል ።...አንተም ደግሞ ፊት አገኘሁ ብለህ አታምሽ
.
ሚኪ ... (እማዬ ትጣራለች)
በርሬ ስሯ እደርሳለሁ ። ... ወደ ጓዳ ገብታ አምስት ሊትር ጄሪካን ይዛ ትመጣና ክዳኑን ከበላይ ጥላ የምትዘጋበት ስስ ፌስታል እየፈለገች.. ..
'ሂድ አባትህ ... እከሊት ጠጅ ቤት ና ብሎሀል ። ' ትለኛለች።
መቋጠሪያ ላስቲኩንና ቢጫውን ጄሪካን ተቀብያት እከንፋለሁ።
የጠጅ ቤቷ በር ጋ ስደርስ የሰው አይን ስለሚያስፈራኝ አንገቴን ሰብሬ እገባለሁ።
ጫጫታው.. .ጨዋታው ግን አንዳች መስህብ አለው። አጎንብሼም ግን ቆሎ ከሚያዞረው ልጅ ቁና ላይ መስረቄን አልተውም።
"አባት መጣህ ? ...ግባ ወደ ጓዳ " ይላል አባዬ።
"ማነሽ ...የሺ ! ዘሪሁን መቷል ...ብርዝ ስጭውና ይዞ ይሂድ "
የጠጅ ቤቷ ባለቤት መልከ መልካሟ የሺ ትመጣለች። ሳያት ደስ ትለኛለች...እንደ እቴጌ መነን ጀነን ያለ ኩራት አለባት። በዛ ላይ እኔን ትወደኛለች...ስትንከባከበኝ ደስ ይለኛል።
"መቼም አባትህ ካንተ ውጭ ወሬ የለውም !"
ትለኛለች። ...
"ትምህርት ደግሞ ሁለተኛ ወጣክ አይደል?"
"አዎ እትዬ! "
" ታድያ ትምህርት ሁለተኛ ወጣህ ብሎ ለምን ይቆጣካል?"
"አንደኛ የወጣው ልጅም እንዳንተ እንጀራ ነው የሚበላው.. . አንተ ከሱ ለምን አነስክ ብሎ ነዋ "
"ቂ....ቂ....ቂ....ክፍል ውስጥ ስንት ተማሪ አለ ?"
"80 ነን እትዬ"
"እና ሎሎች ሰባ ስምንቱ የጠላ ቂጣ ነው የሚበሉት? ሁሌም ተማሪ ታለ ውድድር አለ ...ውድድር ካለ ደግሞ አሸናፊም ተሸናፊም አለ። ደግሞ ከአንድ እስከ ሶስት መውጣት ሁሌም ጉብዝና ነው። ምነው የአባትህ ጓደኛ የአያ ቸሬ ልጅም አለ አይደል እንዴ? እያንዳንዱን ክፍል እንደ ውዳሴ ማርያም ሳይደጋግም አያልፍም እኮ! ቂ...ቂ...ቂ "
እትዬ የሺ ትስቃለች። ስትስቅ የድዷ ውቅራት ደስ ይላል። በጥቁር ድዷ ላይ ደግሞ ነጭ ሳይሆን የሆነ ነጣ ያለ ማኪያቶ የሚመስሉ ስድር ጥርሶች አሏት ።
ከደቂቃዎች በኋላ በትንሿ ብርጭቆ ብርዝ ትሰጠኛለች። ገዝቻች አይደለም...ግዴታዋም አይደለም...ስለ ፍቅሯ ብቻ!
ብርዙን ፉት ስለው ገና ከገነት ፍሬዎች አንዱን ቀጥፌ የመጠጥኩት ይመስለኛል።
ጥፍጥ.. ..
....
ህይወት በዛ ቤት እንደዚህ ውብ ሆና ለመቀጠል ግን ጥቂት ዓመታት ብቻ ነበሩ ደግ ሆነው የቆዩት ።
ከሆነ ጊዜ በኋላ እትዬ የሺ ስኳር መጠቀም ጀመረች አሉ። ከዛ ብዙ ብዙ እኔ የማይገቡኝ የትልቅ ሰው መከራዎች ደርሰውባት ከአካባቢው ዞር አለች። የጠጅ ቤቷ ዝና ወረደ ...እኛም ያደግንባትን ከተማ ለቀን ለዩንቨርስቲ ትምህርት ተሰደድን ።
የሆነ ጊዜ ደግሞ እንደዚህ ሆነ...
5 ዓመታትን በተለያየ ከተማ ተበታትነን የነበርን ጓደኞች ተገናኝተን የድሮዋን ታዋቂ ጠጅ ቤት ለመጎብኘት ሄድን። አዲሷ ቤት ደመ ቀዝቃዛ ናት። ድሮ እታለም ጠጅ ቤት ስሄድ የነበረው ሁካታና ግርግር የለም። ቅር አለኝ። እትዬም ስራውን ለሰው ለቃ ስለነበር ብዙ ጊዜ ሳሎኑን አትጎበኘውም።
ከልጆች ጋር ተሰብስበን አንድ ሁለት ካልን በኋላ እትዬ መጣች።
ፍቅሯ እንደ ድሮው አልነበረም። ጭራሽ ረስታኛለች.. .ደግሞ ጉስቁል ብላለች ።
ስታወራ ድምፅዋ ቅልስልስ አለ ...
እኔ ከጓደኞቼ ጋር ስጫወት ቆየሁ። በመሀል የሺ ትክ ብላ አየችንና ከመሀል አንዱን ጓደኛችንን አንተ የጋሽ ክፍሌ ልጅ ነህ አይደል? አለችው።
"አዎ እትዬ" አላት...ሀዘንና ቁጣዋ እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ ፊቴ ላይ አለ።
"እናንተ ባለጌዎች አሁን እናንተም አድጋችሁ ጠጅ ለመጠጣት በቃችሁ ?" እትዬ.. .ጮኸች!
እትዬ አልገባትም እንጅ አድገን ስራ ሁሉ ይዘናል እኮ ። እንደውም አንዱ ጓደኛችን ሚስት ሊያገባ ስላሰበ ለሚዜነት ሊጀነጅነን ነበር እዛች ቤት የገባነው። የሺ ግን ልጅ ሆነን ስለምታውቀን አንጀቷ እንቢ አለ ።
ለሶስተኛ ጊዜ መጥታ ጠጅ ልትቀዳልን ያለችው ዓለም ላይ እትዬ ጮኸችባት።
"ውጡ " ...
"እንዴ እትዬ ሂሳብ አልከፈሉም እኮ" አለች ዓለም።
"የራስሽ ጉዳይ ...እነዚህ እኮ ልጆች ናቸው። አባቶቻቸው ነበሩኮ እኔ ጋር የሚመጡት.. .የዛሬን አትይ ..." እትዬ እንባዎቿ ወረዱ !
እኔ ግን እንዴት እንደሆነ ባላውቅም እትዬ የሺ አሁንም ድረስ እንደ ንጉስ ሀይለ ስላሴ ሚስት በኩራት ታየችኝ።
በዚህ ገንዘቤን እንጅ ስለ ትውልዱ ምናገባኝ የሚል ስግብግብ ነጋዴ በበዛበት ዓለም...18 ዓመት ላልሞላው ልጅ ጫት እና መጠጥ በሚሸጥበት ዓለም... እኔ ያገባኛል የሚል ነጋዴ...ለዛውም ከስሮ ችግር ላይ ያለ ነጋዴ ሲታይ እንዴት አይገርምም?
ሁላችንም ተግተልትለን መውጣት ጀመርን። እትዬ ብትናፍቀኝም...እንደ ረሳችኝ አውቄ ባፍርም የአባዬ ልጅ ነኝ ብዬ ብነግራት እጅግ የምትናደድ ስለመሰለኝ ዝም አልኳት።
የናፍቆት የናፍቆቴን በር ጋር ደርሼ ዞር ብዬ አየኋት። ነፍሷ ዛሬም ውብ ናት !
ትልቅ ሰው መቼም ትልቅ ሰው ነው
@wegoch
@wegoch
@paappii
1.5K viewsDAVE / PAPI, 07:12