2021-12-25 10:35:30
አታምጣው ስለው አምጥቶ ቆለለው #5
አፌን ለቆ ሲወጣ የሰማሁት ዓረፍተ ነገር
"አብረን በነበርንበት ጊዜ ወደኸኝ ታውቅ ነበር?" የሚል ነው። ጥያቄዬ አፌን ለቆ ወጥቶ ሳያልቅ በፊት
"ባባ ደህና ነው?" የሚለው የእርሱ ጥያቄ ዓለሜን አዞረብኝ። ለመጠየቅ መልሱን ፈርቶ እያማጠ እንደያዘው ያስታውቅ ነበር። እኔ ሳየው የ15 ዓመት ቁስሌን ነው የጠዘጠዘኝ። ለካስ የእኔ መከሰት ለእሱ የቤተሰቡ ህልውና አደጋ ላይ መውደቅ ማመላከቻ መርዶ ነው። ራስ ወዳድ እንደሆንኩ ተሰማኝ።
"እሱ ደህና ነው። እኔጋ ነው!" አልኩት። በረዥሙ ከሆዱ እስከ ጭንቅላቱ የናጠው የመገላገል ትንፋሽ ተነፈሰ።
"እሷስ?" አለኝና መልሶ "ተይው አትንገሪኝ!" አለኝ። ለሆነ ደቂቃ ስረግመው የኖርኩት አሸናፊ መሆኑን ረሳሁት። የምመልስለትም የምጠይቀውም ተወነባበደብኝ።
"ሞታ ነው አይደል? በህይወት እያለች ላንቺ እንዲደወል አታደርግም።" አጠያየቁ እንድመልስለት የፈለገ አይደለም።
"በህይወት አለች!" አልኩት:: ሲቃ አይሉት ለቅሶ አይሉት ያለየለት ድምፅ አሰምቶ በዛ ቁመቱ ግንድስ ብሎ መሬቱ ላይ ዘፍ ብሎ ተቀመጠ። ላለማልቀስ እየታገለ ግን እንባ ሳይወጣው እያለቀሰ እንደሆነ ያስታውቅበታል። ዝም ብሎ ከማየት ውጪ ማድረግ የቻልኩት ነገር የለም። ድንገት የሆነ ነገር ትዝ እንዳለው ነገር በጥያቄ እያየኝ ከተቀመጠበት ተስፈንጥሮ ተነስቶ
"ቆይ ቆይ ታዲያ ህሉ በህይወት ካለች ባባ አንቺጋ ምን ይሰራል? እ ...እ ... በፍፁም! ህሉ ትንፋሿ እያለ ልጇን አሳልፋ አትሰጥም!" ተቁነጠነጠ። የተፈጠረውን ነገር ስነግረው ጭንቅላቱን በእጆቹ ይዞ ጀርባውን ሰጥቶኝ ቆመ። ምልስ ብሎ
"አንቺ ውሸት አትችዪበትም። እውነቱን ንገሪኝ! ትድናለች?" ሲለኝ የእኔ እንባ ምን ቤት ነው ከእርሱ ቀድሞ የተዘረገፈው?
"አላውቅም!! ሀምሳ ሀምሳ ነው የመንቃት እድሏ ነው ያሉት ሀኪሞቹ።"
እዚህ ደቂቃ ላይ ስለራሴ ምንም እንደማልጠይቀው አወቅኩ። ጥያቄዎቼን መልሼ አዝያቸው ልሄድ ወሰንኩ። ቤተሰብ ለእሱ ዓለሙ ነው። ዓለሙ ፈርሷል። የእኔን ህመም እርሱ ካለበት ሁኔታ ጋር ማነፃፀር አልፈለግኩም። ዝም አልኩ።
"ከሞተች። (ሲቃ እያነቀው ቃሉን ሲለው እንደዘገነነው ያስታውቃል።) ለልጄ እናቱ እንደሞተች አትንገሪው። ሲቆይ ይረሳታል። "
"እንዴ?" ብዬ ጮህኩኝ ሳላስበው።
"ልግባ?" አለኝ ለመሄድ ፊቱን እያዞረ። ግራ ገባኝ። እንዲህ ሁሉ ነገር እጄ ላይ ጥሎ እንዴት ነው የሚገባው? ባባን ምን ላድርገው? እሺ ልጄንስ ምን ልበላት? እሺ ሚስቱን የገጨበትን ሰው በህግ ልጠይቀው በሽማግሌ? እሺ ሚስቱንስ ምን ላድርጋት? ዥውውውው አለብኝ። ይሄን ሁሉ መከራ እላዬ ላይ ጥሎማ አይገባም! ግን የቱን አስቀድሜ የቱን እንደማስከትል እንጃ!
"አዎ እያንዳንዱን ቀን ወድጄሽ ነበር።" አለኝ ለመሄድ እየተንቀሳቀሰ። ማለት የምፈልግ የነበረው ብዙ ነበር። ለምን ብዬ የምጠይቃቸው እልፍ ጥያቄዎች ነበሩ። ፊቱ ላይ ካለው ስቃይ ጋር ሲነፃፀር የእኔ ጥያቄ ገለባ ሆነብኝ። መርዶ ይሁን የምስራች ሳይገባኝ
"እርጉዝ ነበርኩ። ያኔ ..... " ብዬ 'ትተኸኝ ስትሄድ' ልል ነበር። የምጎዳው ነገር መሰለኝና ሌላ የሚተካው ቃል ስፈልግ....
"እና? " አለኝ። ሊሄድ ከነበረበት ተመልሶ በጉጉት
"15 ዓመቷን ባለፈው ሰኔ 6 አከበረች::" አልኩት። ሳቅና ለቅሶ ፊቱ ላይ ተሳከረበት። ወደፊት ወደኋላ ከዛ ወደጎን ተንቆራጠጠ። እጁን አንዴ ጭንቅላቱ ላይ አንዴ ወደኋላ አንዴ ጉንጩ ላይ ያቅበዘብዘዋል።
"ታውቂያለሽ ....." ብሎ ዝም አለ
"አውቃለሁ። ብታውቅ ልጅህን ያለአባት እንድታድግ አታደርጋትም። ልነግርህ ነበር። ልነግርህ ስመጣ አንተ ሄደሃል።" አልኩት። ልክ እንደቅድሙ መሬቱ ላይ ዘጭ ብሎ ተቀመጠ። ግን እንደቅድሙ ለቅሶ ብቻ አይደለም። ፈገግ እያለ ነው የሚያለቅሰው። ቅስስ ብሎ ከመሬቱ ላይ ተነሳ መደሰት ይሁን ማዘን ያለበት ግራ የገባው ይመስላል።
"አባቷ ?...." ብሎ እንዴት መጠየቅ እንዳለበት ግራ ሲገባው
"ታውቃለች። እውነቱን ነው የነገርኳት። የአሁኑን እንዴት እንደምነግራት ነው ግራ የገባኝ።"
ሰዓታችን ማለቁን ደጋግመው እየገገሩን ነው። እንደማሰብ ካለ በኋላ ...... እስከአሁን የሆነውን መሆን እንዳልሆነ ...... ክፉ ዜና እንዳልሰማ ...... ምንም ዝንፍ ያለ ነገር እንዳልተፈጠረ ..... ተረጋግቶ ከፊቱ ላይ እንባውን ካበሰ በኋላ በሰከነ ዝግተኛ ድምፅ
"ጥያቄዎችሽን ሁሉ ብመልስልሽ : የሆነውን ሁሉ አንድ በአንድ ባስረዳሽ ደስ ይለኛል። ምናልባት እድሉን ካገኘሁ የሆነ ቀን ያደረግኩትን ለምን እንዳደረግኩ እነግርሻለሁ። ያ ማለት አንቺ ያ ይገባሻል ማለት አይደለም። እመኚኝ አንቺን ከጎዳሁሽ በላይ ባሰብኩሽ ቁጥር እቀጣበታለሁ። ይገባኛል ብዬም አይደለም የምጠይቅሽ ግን በዓመታት ብዛት ሊከፋ የማይችል ደግ ልብ እንዳለሽ አውቃለሁ። ልጄ ቤተሰብ እንዲኖረው እፈልጋለሁ። ካንቺ የተሻለ ብዙ ፍቅር ያለው ሰው አላውቅም!! እኔ የኖርኩትን ህይወት እንዲኖር አልፈልግም። የተፈረደብኝ ቀን ለሄሉ ድንገት የማትወጣው ነገር ውስጥ ከገባች ላንቺ እንድትደውልልሽ ነገርኳት። ታውቂያለሽ ሁለታችንም ቤተሰብ የለንም። 'በህይወት እያለሁ አላደርገውም ድንገት እኔ የሆነ ነገር ከሆንኩ ግን ልጄ በፍቅር የሚያድግበት ቤተሰብ ያስፈልገዋል።' አለችኝ:: ለዛ ነው መታወቂያዋ ላይ ያንቺ ስም የኖረው። "
ከዚህ በላይ መቆየት አይችልም ነበር። "እሺ አደጋ ያደረሰባትን ሰው ......" ብዬ ሳልጨርስ
"ምን እንደምታደርጊ አንቺ ታውቂያለሽ!! ካንቺ የተሻለ ምክንያታዊ ሆኖ የሚወስን ሰው አላውቅም !" አለኝ ፊቱን አዙሮ እየሄደ።
በቃ! ??? ስመጣ የሆነ ከባድ ሸክም ላራግፍ ...... የሆነ የሚስጥር መፍቻ ቁልፍ ላገኝ ........ የሆነ ያልኖርኩትን መኖር ልጀምር ....... የሆነ ከበሽታዬ የምፈወስ ........ የሆነ ጥያቄዬ ሁሉ የሚመለስ ዓይነት አልነበር የነበርኝ ስሜት?
ጥያቄዬ ግማሹ እንኳን መልስ ሳያገኝ ይባሱኑ ልሸሸው እንደማልሞክር የማውቀውን ሀላፊነት አሸክሞኝ ገባ! ተገተርኩ ለደቂቃ! ልክ እሱ መሬቱ ላይ ዘጭ ብሎ እንደተቀመጠው ንጥፍ ማለት አማረኝ። ራሴን ምን ውስጥ ነው የከተትኩት? ምኑን ከምኑ ነው የማዛምደው? ጭራሽ ልጠይቀው ያላሰብኩት ጥያቄ ትዝ አለኝ። ምን አድርጎ ነው የታሰረው? ምን ያህል ዓመት ይሆን የሚቆየው? ለልጄ እውነቱን ከነገርኳት ቢያንስ ይሄን ማወቅ አለብኝ። እንደገባኝ ከሆነ የግሩም አባት መረጃዎችን በአቋራጭ የማግኘት መክሊት አለው። እግሬ መሬቱ ላይ የተተከለ ይመስል ከተገተርኩበት ተስፈንጥሬ አጠገባቸው ደረስኩ። እንደሆነ ሊፈነዳ እንደተቀባበለ መዓት የምለውን ለመስማት ጠበቁኝ።
"አንድ ውለታ ዋሉልኝ!" ስላቸው ሁለቱም ግራ ገብቷቸው ያዩኛል።
"የታሰረበትን ምክንያትና ምን ያህል እንደተፈረደበት ማወቅ አለብኝ!" ስላቸው ፍፁም የጠበቁት ጥያቄ አለመሆኑ ያስታውቅባቸዋል። አባትየው ከድንጋጤው መለስ ብሎ
"ስልኮች እደዋውላለሁ። " አለኝ።
ወደአዲስአበባ እየተመለስን ጭንቅላቴን የጨመደደው ሀሳብ የታሰረው ክፉ ነገር አድርጎ ቢሆን ለልጄ እንዴት ብዬ እንደምነግራት ነበር። በመስኮቱ አሻግሬ እያየሁ ውስጤ ያለው ስሜት ቅድም ስሄድ የነበረው ዓይነት እንዳልሆነ ገባኝ ..... ምን አጊንቼ ነው የቀለለኝ??
"እርቦኛል:: የሆነ ቦታ ምግብ እንብላ?" አልኩኝ
693 viewsDAVE / PAPI, 07:35