2022-02-10 22:46:44
አንድ ወፈፌ ወንደላጤ ጎረቤት አለኝ። ቀን ቀን ፍፁም ሰላማዊ ሰው ነው። አንገቱን ሰብሮ ሰላምታ ሲሰጥ በከንፈሩ አፈር ቅሞ ለመመለስ ትንሽ ነው የሚቀረው :)
እንደውም አከራያችን እትዬ ዘነብ አንዳንዴ "ልጄ ተው እንዲህ አለቅጥ አታጎንብስ ዲስክህ ይንሸራተታል " ይሉታል።
እሱ ፈገግ ብሎ በሀፍረት ያቀረቅራል ። ጭራሽ የሆነ ጊዜ ላይ ቤቱ ቡና አፍልቶ ጠራን !
በጠባብ ክፍሉ ውስጥ እንደ በግ ኮኮር ተራርቀው የሚገኙ የቤት እቃዎቹን እየገረመመን ተሰየምን።
እትዬ ዘነብ ደግሞ እንደ ሀረር ሰው ቀጥታ ነው ንግግራቸው...ያ ሁሉ የግቢው ሰው በተሰበሰበበት
"አንተ ምነው እቃህን በወግ ብትሰድረው?... " አሉት ... ትንሽ ቆየት ብለው ደግሞ...
"እግዚኦ ያ ምንድነው ሀይላንድ ውስጥ ያለው?" ብለው ጮኹ!
ናደው በድንጋጤ "የቱ ?" ብሎ መለሰ። ሀይላንዱን እኮ አፍጦ እያየው ነው !
"ሀይላንድ ላይ ነው እንዴ የምትሸናው?"
ደነገጥን!
እትዬ ደግሞ አንዳንዴ የሆነ ነገር አይተው ላሽ ቢሉ ምናለበት?
" ኸረ ቢራ ነው እትዬ! ኸረ እንደውም ልቅዳሎት " ብሎ ተነሳ...
እትዬ ሀይላንዱን ሰገራ እንደነካው እንጨት ተጠይፈው ...
"አንተ ሂድ ! ምን ያለው ሰላቶ ነው ባካችሁ?
ላስቲኩን እየው እስቲ? ጎዳና ተዳዳሪ መስሏል እኮ! "
እኛ ለሱ ተሸማቀቅን።
ናደው ወሬውን ለማስቀየስ መሰል... ጀበናውን በእጁ እንደያዘ.. ."አህ ...ህ " ብሎ አቃሰተ ።
"ምነው?" አልኩት እሱ በቀደደው አዲስ ወሬ ለማፈትለክ ...
"ብርድ መቶኛል መሰለኝ..አንዳንዴ ትከሻዬን ይወጋኛል "
"በዚህች ስስ አንሶላ ተሸፍነህ እየተኛክ እንኳን ብርድ መጋኛም ስላልመታህ ፈጣሪን አመስግን " ብለው ቀጠሉ እትዬ.. .
"ስማ ምነው እኔ ቧንቧ ቆጠረብኝ አልኩህ እንዴ? ኣንሶላህን ለቅለቅ አድርግ እንጅ!
አሁን ይሄ አንሶላ ነው ወይስ መሀረብ? ኤድያ!
ከዛች ቀን በኃላ ናደው በማለዳ ተነስቶ አዲስ አልጋ ልብስ ገዝቶ መጣ ... ከሾላ ገበያ ገዝቷት የመጣውን አልጋ ልብስ ለግቢው ተከራይ ሁሉ እያዟዟረ አሳየን።
ሽንጉርጉር አንሶላውን ለሞራሉ ስንል አደነቅንለት ...
እኔ በተለይ ከሱሳ ሱስ አስተርፎ ባዘጋጃት ገንዘብ ይሄን በማድረጉ አሳዘነኝ።
ናደው ቀን ቀን ሰላማዊ ይሁን እንጅ ምሽት ላይ ፍፁም ሌላ ሰው ነው ። ጫቱን ቅሞ.. .አረቄውን መጦ.. .ሀሽሹን በልዞ ሲመጣ ያስፈራል።
ቀን ለሰላምታ መሬት ካላስኩኝ የሚለው ልጅ ምሽት ላይ ደረቱን ገልብጦ የሰማይ ከዋክብትን ልግመጥ ይላል ።
ብቻውን እያወራ ይንገዳገዳል.. .ትንሽ ራመድ...ራመድ ይልና የቤቱን ደረጃ በእንፉቅቁ ይወጣል ።
ለዛን ቀንም ... ለገዛት አንሶላ የፍንጥር ራሱን ሊጋብዝ ፀሀይ ከማዘቅዘቋ በፊት ሹልክ ብሎ ወጣ ።
ከሰዓታት በኋላ እንደልማዱ ደረቱን ገልብጦ መጣ...ደረጃውን በዳዴ ወጥቶ የጠባብ ክፍሉን ቁልፍ ከፈተ ።
ከበሩ በስተግራ ያለችውን ማብሪያ ማጥፊያ በመከራ ተጭኖ አንፖሉን ለኮሰ....
ቤቱ በብርሀን ተሞላች ።
በቅፅበት እሪታውን አቀለጠው ....
"ነብር ...ነብር ....ነብር አልጋዬ ላይ ኡ....ኡ....ኡ..... "
የግቢው ተከራይ ንቅል ብሎ ወጣ ። ይሁንና ከእትዬ በስተቀር የሱን ክፍል የተጠጋ ሰው የለም።
ናደው በተዓምር ይሁን በአስማት የግቢውን አጥር ዘሎ ወጣ ...
እኔ ክፍሌ ውስጥ ሆኜ ድምፄን አጠፋሁ ። ድካም ተጫጭኖኝ ስለነበር.. .ግርግሩን እየሰማሁ እንቅልፍ ይዞኝ እብስ አለ ። ማልዶ
"አሁኑኑ ቤቴን ለቀህ ውጣልኝ!" የሚለው የእትዬ ጩኸት እስኪያባንነኝ ድረስ የት እንዳለሁ አላውቅም።
"ሰውኮ ይሳሳታል እትዬ "
የቤቴን መስኮት ከፍቼ የሁለቱን ግብግብ አያለሁ ... እነ አስኩቲ ጥግ ላይ ሆነው አፋቸውን በመዳፋቸው ሸፍነው ይስቃሉ ።
ሰው ሊባረር ሲል እንዴት ደስ ይላቸዋል? የሚል ንዴት ውስጤን እያንገበገበኝ ነበር ።
እነሱም እኮ ተከራይ ናቸው!
ይሄ በእትዬ የተመዘዘ ሰይፍ ነገ እነርሱ ላይ እንደማያርፍ ምን ዋስትና አላቸው? እያልኩ ተብሰከሰኩ.. .
"ስማ ሚኪያስ !" አሉኝ እትዬ ወደ መስኮቴ ተጠግተው.. .
"ሰላም አይደለም እንዴ እትዬ?"
"ምን ሰላም አለ ? ይሄ ቀውስ ማታ የሰራውን አልሰማህም?"
"ኸረ እንደውም! " ... ካድኩኝ...
"ኸረ እንኳን ያልሰማህ። ይሄ ምናምኑን አጭሶ መጣና ቀን የገዛውን አልጋ ልብስ ዘንግቶት ..."
"አልጋ ልብሱን ረስቶ ምን?"
"አልጋ ልብሱ ላይ ያለውን የነብር ምስል አይቶ አልደነበረ መሰለህ?
አልጋዬ ላይ ነብር ብሎ አንባረቀ እኮ!
ደግሞ እንደ ጤነኛ ሰው አንገት ይሰብራል...አንገቱን ነበር መስበር።
@wegoch
@wegoch
@paappii
#Mikael aschenaki
692 viewsDAVE / PAPI, 19:46