2022-01-26 22:22:19
"ድምቀት ወ ፅልመት"
አርብ 'ለት ነበር ፣ 12:00 ሰአት አካባቢ፣ ቀኑ ቀን አልመስል እያለኝ ወደቤቴ ለመሄድ መንገድ ላይ ሳለው አብዶ ይሁን ፣ እያበደ ይሁን ግራ የሚያጋባ ሰው ድንገት በመንገድ ላይ ያገኘኝና ልክ የዘመናት ጓደኛው እንደሆንኩ ያክል ያወራኝ ጀመር።
" አየሀት ያቺን ጀንበር? ....... ፣ ገና እያጎጠጎጠች ያለች ቆንጆ ሴት ትመስላለች ፣ ልክ እንደ አንዲት ሴተኛ አዳሪ ፣ ልክ እንደ አዲስ ፍቅረኛሞች....፣ ግን ፈጣሪ ለምንድነው ይሄን ያክል የምታሳሳ ልጅ ያስመሰላት?............. ግን አንተ ምን ይታይሀል?....... " አለኝ ። እየተከተለኝ ይሁን መንገዳችን ተገጣጥሞ በምታጠፍበት እየታጠፈ ፣ ጀንበሯን አዘቅዝቆ እያየ ይጠይቀኛል።
" እኔ እንኳን ስራ ፈትቼ እሷን የማይበት ጊዜ የለኝም " አልኩት ። እንዲተወኝ ፈልጌ እንጂ ሳላያት ቀርቼ አልነበረም።
" ተፈጥሮ ለማን የተፈጠረ ይመስልሀል ?"
" ያው ለራሱ መሰለኝ " አልኩት ጥያቄው ስላልገባኝ ።
" ተፈጥሮ ሁሉ ለሌላ ጠፈጥሮ ነው የተፈጠረው ፤ ሰው እንኳን ለሌላ ሰው ነው የተፈጠረው " አለኝ አይኑን ከጀንበሯ ሳይነቅል።
"እና ምን ነበር ይታየኛል ያልከኝ" አለኝ ምንም እንዳላልኩት እያወቀ።
" እኔ እንኳን ቆንጆና ደማቅ ጀንበር ናት ምትታየኝ" አልኩት ፣አስተውዬ ለማየትም አልሞከርኩም ምክንያቱም ሰውየው እብድ ይሁን ጤነኛ እርግጠኛ አልነበርኩም።
"አንድጊዜ ቆንጅዬ ልጅ መንገድ ላይ አየሁና መከተል ጀመርኩ" አለኝ ያቺ ቆንጆዋ ልጅ ጀንበሯ አንደሆነች ያክል ወደ ጀንበሯ እያፈጠጠ።
"እሺ......." አልኩት
"ተከተልኳት ተከተልኳት ተከተልኳት....."
"እሺ ከዛስ.." ደገምኩት
"ተከተልኳት ተከተልኳት ተከተልኳት...."
ሳቄ እንደ ትንታ አመለጠኝና ወዲያው ዝም አልኩኝ።
"ተከተልኳት ፣ እንደዚ ቆንጆ ሆና ግን ማንነቷን የሽማግሌ ኪስ ወስጥ አገኘዋለው ብዬ አላሰብኩም ነበር" አለኝ እንደማዘን ብሎ።
"ሌባ ነበረች?"
" ሌባ ህሊናውን ይሸጥ ይሆናል እንጂ አካሉን አይሸጥም ፣ ይቺ ቆንጆ ሰው....ነቷን ሁሉ ነው የሸጠችው ፣ እኔ እሷን መከተሌ ድካም ነው ያተረፈልኝ ፣ አንተም የጀንበሯን ውበት ብቻ ማየትህ የት እንደሚያደርስህ አላውቅም " አለኝና ለትንሽ ጊዜ ዝም አልን። ግን ምን ማለት እንደፈለገ ማወቅ እንዳለብኝ ተሰማኝ።
"አንተ ምንድን ነው ሚታይህ?" አልኩት።
" ታሳዝነኛለች" አለና እንባው እንደቀልድ መውረድ ጀመረ "በጣም ታሳዝነኛለች ፣ ስልጣኑ ቢኖረኝ እንደዚ እንዳማረባት ዘላለም ባቆያት ደስ ይለኛል ፣ ልብ ብለህ እያት ፣ መንገዷን ተመልከት ፣ ቅድም ስንገናኝ የነበረው ውበቷ አሁን የለም ፣ አሁን ያለው ውበቷ ከደቂቃዎች ቡኋላ አታገኘውም ፣ መንገዷም መጨረሻዋም የከፋ ነው " አለና ጣቱን ወደጀንበሯ እየጠቆመ ፣
" አንቺ ጀንበር ተጠንቀቂ ፣ ቀን ወደነበርሽበት ተመለሺ !!" አለና ሳይሰናበተኝ በመጣንበት መንገድ ተመለሰ።
ምን ሊነግረኝ ፈልጎ ነው? ፣ ማንስ ነው የላከው ?፣ ጀንበሯ ማነች? ፣ ቀንስ ምን ነበረች ?፣ አሁንስ ምን ልትሆን ነው? እያልኩኝ እራሴን ስጠይቅ ያቺ ገና እያጎጠጎጠች ያለች ቆንጆ ሴት የምትመስለዋ ፣ ልክ እንደ አንዲት ሴተኛ አዳሪ የምትመስለዋ ፣ ልክ እንደ አዲስ ፍቅረኛሞች የምታስቀና የነበረች ጀንበር አሁን የለችም ፣ ምድሪቱን ጨለማ ወርሶታል ፣ እኔም ከነጥያቄዎቼ ወደ ቤቴ ገባሁ ።
(ቤካ)
@wegoch
@wegoch
@paappii
592 viewsDAVE / PAPI, 19:22