2022-05-13 12:52:23
ህጻን አግቶ ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረገው ግለሰብ በ25 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጣ
ግንቦት 5/2014 (ዋልታ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ ታዳጊ ህጻንን በማገት ህይወቱ እንዲያልፍ በማድረግ ወንጀል የተከሰሰው ግለሰብ በ25 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ የተወሰነበት መሆኑን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡
የቅጣት ውሳኔው የተላለፈው በጭልጋ ወረዳ የቤዛሆ መቀነት ቀበሌ ነዋሪ በሆነው አበበ ዳኘው ላይ መሆኑን የፍርድ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ማስተዋል ወርቁ ተናግረዋል።
ግለሰቡ ድርጊቱን የፈጸመው በወረዳው የአይከል ከተማ ነዋሪ የሆነውን የ15 ዓመት ታዳጊ ህጻን ጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም ከመኖሪያ ቤቱ አፍኖ በመውሰድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለህጻኑ ወላጆች ስልክ በመደወል 100 ሺሕ ብር ከፍለው ልጃቸውን እንዲወስዱ፤ ብሩን ካልከፈሉ ግን ህጻኑን እንደሚገድለው ሲዝት እንደነበር ባለሙያዋ ገልጸዋል።
በዛተውም መሰረት ህጻኑን በወረዳው ፋይና ገብ ተብሎ በሚጠራው ገደል ውስጥ በመክተት ህይወቱ እንዲያልፍ ማድረጉ በሰውና በሕክምና ማስረጃ መረጋገጡንም አስረድተዋል፡፡
ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠ ሲሆን፤ ተከሳሹ በእምነት ክህደት ቃሉ ወንጀሉን አልፈጸምኩም ሲል ክዶ ተከራክሯል፡፡
ይሁን እንጂ ተከሳሹ በአቃቢ ሕግ የቀረበበትን ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻሉ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 149/1/ መሰረት ጥፋተኛ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
ግለሰቡ የቤተሰብ አስተዳዳሪና ከዚህ ቀደም የወንጀል ሪከርድ የሌለበት መሆኑን በቅጣት ማቅለያነት የተመለከተው ፍርድ ቤቱ የ25 ዓመት ጽኑ እስራት ውሳኔ እንዳስተላለፈበት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዋ ገልጸዋል።
356 views09:52