2022-05-13 19:11:06
ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አገራዊ ምክክር ስኬታማ እንዳይሆን ካደረገው ችግር መማር አለባት ተባለ
ግንቦት 5/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አገራዊ ምክክር ስኬታማ እንዳይሆን ካደረገው የአካታችነት ችግር ትምህርት መውሰድ እንዳለባት በጁባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ፣ ሰላምና ጸጥታ ረዳት ፕሮፌሰር አብርሃም ኮኣ ንዮን መከሩ።
አገራዊ ምክክሩ ተዓማኒነትና ግልጸኝነት እንዲኖረው የመገናኛ ብዙኃን ለአጠቃላይ ሂደቱ ሽፋን ሊሰጡት እንደሚገባም ነው ያመላከቱት።
ደቡብ ሱዳን እ.አ.አ በ2011 ነጻነቷን ከተቀዳጀች በኋላ ከገባችበት የእርስ በእርስ ጦርነት ለመውጣት የተለያዩ የሰላም አማራጮችን ተከትላለች።
ከእነዚህም መካከል አ.አ.አ በ2017 ወደ ሥራ ያስገባችው አገራዊ ምክክር አንዱ ሲሆን ምክክሩም የተጠበቀውን ያህል ውጤት ማምጣት አልቻለም።
ለዚህም ደግሞ ምክክሩ የአካታችነት ችግር ያለበት መሆኑን ነው የተለያዩ መረጃዎች የሚያሳዩት።
ይህንን ሃሳብ የሚጋሩት የጁባ ዩኒቨርሲቲው አብርሃም ኮኣ ንዮን ኢትዮጵያም አካታችነት ላይ ጥንቃቄ ልታደርግ ይገባል ብለዋል።
የደቡብ ሱዳኑ ምክክር የተካሄደው የጸጥታ ችግር በነበረበት ወቅት እንደነበር አስታውሰው፤ በምክክሩ የተወሰኑ ሥፍራዎች ሳይካተቱ መቅረታቸውን ነው የገለጹት።
በተጨማሪም በአገራዊ ምክክሩ የተነሱትና በመጨረሻም ለውሳኔ የቀረቡት ምክረ-ሃሳቦች ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ አለመሆናቸውም ሌላኛው ችግር እንደነበር መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት ተመሳሳይ ስህተት እንዳይፈጽም የመከሩት ረዳት ፕሮፌሰሩ ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳንን ተሞክሮን በደንብ ማጤን አለባት ብለዋል።
1.0K views16:11