2022-05-16 20:23:01
አምባሳደር ዲና ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም ከፍተኛ የሕይወት ዋጋ ከፍላለች አሉ
ግንቦት 8/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም ከፍተኛ የሕይወት ዋጋ የከፈለች እና በቀጣይም ለሀገሪቷ ዘላቂ ሰላም ከአዲሱ መንግሥት ጎን የቆመች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።
አምባሳደር ዲና ፤ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ትብብር በማጠናከር ለአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት የሚኖራትን ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡
አገራቱ የቆየ ዲፕሎማሲያዊ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ያላቸው አገሮች መሆናቸውን በማስታወስ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ ትብብር እንዲሁም የልማት ትስስራቸው ጠንካራ መሠረት ያለው መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በጎረቤት አገር ሶማሊያ ዘላቂ ሰላም እንዲኖር የኢትዮጵያ ድጋፍ እና እገዛ እስካሁንም የዘለቀ መሆኑን ጠቅሰው ሶማሊያ ሰላማዊ ምርጫ እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ያካሄደችውን የስልጣን ሽግግር ኢትዮጵያ ታደንቃለች ብለዋል።
የሶማሊያ ሰላማዊ የምርጫ ሂደት እና የስልጣን ሽግግር ለሶማሊያውያን ኩራት ሲሆን ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ በአዲሱ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሞሐሙድ ከሚመራው መንግሥት ጋር በቅርበት እንደምትሰራም አረጋግጠዋል።
በተጨማሪ ድህነትን በመዋጋት እና ድርቅን በመከላከል እንዲሁም በቀጣናው የልማት ትስስርን በማጎልበት ሽብርተኝነት በጋራ እንዋጋለን ብለዋል።
በኢኮኖሚ ውህደት፣ በንግድ፣ በመሠረተ-ልማት ትስስር እና የሁለቱን አገራት ሕዝቦች በሚጠቅሙ ፕሮጀክቶች ላይ በጋራ መስራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
2.3K views17:23