2022-05-15 18:22:12
በቦቆጂ ለመጀመሪያ ጊዜ ታላቁ ሩጫ ተካሄደ
ግንቦት 7/2014 (ዋልታ) "ኢትዮጵያ ትሮጣለች” በሚል መሪ ቃል በአርሲ ዞን ቦቆጂ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ታላቁ ሩጫ ተካሄደ።
በመርኃ-ግብሩ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት፣ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሰዓዳ ኡስማን ጨምሮ የተለያዩ የዞንና የከተማ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በአዋቂዎች 7 ኪሎ ሜትር ሩጫ፣ 15 ኪሎ ሜትር ብስክሌት ውድድርና የህጻናት ሩጫ ተካሂዷል።
በአዋቂ ወንዶች የ7 ኪሎ ሜትር ውድድር አትሌት ደጀኔ ኃይሉ በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ አትሌት ቱሉ አበበ ሁለተኛ፣ አትሌት ብርሃኑ ቱሉ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።
በሴቶች 7 ኪሎሜትር ውድድር ደግሞ አትሌት መሰረት ሂርጳ በአንደኝነት አጠናቃለች።
ቀነኒ ዲቻ እና ሃዊ ጉደታ እንደየ ቅደም ተከተላቸው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ጨርሰዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት፤ የውድድሩ ዓላማ የስፖርት ቱሪዝምን ለማበረታታት መሆኑን ተናግረዋል።
በቆጂ ኢትዮጵያን በተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ውድድሮች ያስጠሩ ጀግኖችን ያፈራች ከተማ መሆኗን አስታውሰው ውድድሩ መካሄዱ ከተማዋን የበለጠ ለማስተዋወቅና የቱሪዝም ተጠቃሚነት ለማሳደግ ይረዳል ብለዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ መርኃ-ግብሩ ቱሪዝምን ከማሳደግ በተጨማሪ ታዳጊ ስፖርተኞችን የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
ታላቁ ሩጫ በቦቆጂ ሲደረግ የመጀመሪያ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ በየዓመቱ ለማካሄድ እንደታቀደም ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
2.4K views15:22