2022-05-13 15:11:26
ኢትዮጵያ 90 በመቶ መድኃኒት ከውጭ እንደምታስገባ ተገለጸ
ግንቦት 5/ 2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ 90 በመቶ የመድኃኒት አቅርቦትን የምታስገባው ከውጭ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ከዚህ ውስጥ ከ85 በመቶ በላይ መሰረታዊ እና ህይወት አድን መድኃኒቶች ከውጭ የሚገባ ሲሆን 15 በመቶ ብቻ ደግሞ በሀገር ውስጥ ምርት የሚሸፈን ነው ተብሏል፡፡
መድኃኒትን ከውጭ ሀገር ታዞ ሀገር ውስጥ እስኪገባ ከ220 ቀናት በላይ እንደሚፈጅም ተገልጿል፡፡
“የፋርማሲዩቲካል አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍን በአዲስ ምዕራፍ ማጠናከር” በሚል መሪ ሀሳብ ከፋርማሲዩቲካል አምራቾች እና ባለድርሻ አካላት ጋር በዛሬው እለት ምክክር ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን የመድኃኒትና የህክምና ግብዓት በሀገር ውስጥ መሸፈን እንዳትችል ያደረጉ ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥን ያለመ ምክክር ነው የተካሄደው፡፡
በሀገሪቱ የመድኃኒትና የህክምና ግብአት የሚያመርቱ ድርጅቶች 28 ብቻ መሆናቸውም በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡
የህክምና ግብአትና የመድኃኒት አቅርቦትን በሀገር ውስጥ የሚያመርቱ እነዚህ ተቋማት ታዲያ የሀገር ውስጥ ፍጆታን መሸፈን ቀርቶ ምርታማነታቸውም እየቀነሰ መጥቷል ነው የተባለው፡፡
ለዚህ ደግሞ በዋነኝነት ጥሬ እቃን ከውጭ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ስላለባቸው ነው ተብሏል፡፡
በቀጣይ አራት ዓመታት 60 በመቶ በ8 ዓመት ውስጥ ደግሞ 80 በመቶ የመድኃኒት እና የህክምና ግብዓትን በሀገር ውስጥ ለማሟላት እቀድ መያዙ የተገለፀ ሲሆን በጥሬ እቃ ግዢ የሚስተዋለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ ጥሬ እቃ በሀገር ውስጥ የሚመረትበት ሥርዓት ለመፍጠር መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
ዘርፉን ለመደገፍም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሰራ ይገባልም ተብሏል፡፡
በትዕግስት ዘላለም
1.2K views12:11