2023-04-26 07:41:32
ሩካቤ ሥጋ የማይፈጸምባቸው_ጊዜያት
ሩካቤ ሥጋ፣ በምን ዓይነት ሥርዓት ሊፈጸም እንደሚገባው በሕገ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ተደንግጓል፤ እግዚአብሔር ሩካቤን ለሰው የሠራው ልጅ ለመውለድ ብቻ አይደለም፤ የማይወሰን የማይገታ የፈቲውን ፆር ለማራቅ ጭምር ነው እንጂ፡፡
አንድ ጊዜ የሚከለከሉበትን፣ አንድ ጊዜ ፈቃዳቸውን የሚፈጽሙበትን ሠራ፡፡ ነገር ግን አንድ ወንድ ለአንድ ሴት፣ አንዲት ሴት ለአንድ ወንድ ብለው ዘወትር ሊያደርጉት አይገባም፡፡
አጽዋማትን፣ በዓላትን፣ ኅርስን፣ ትክትን ለይቶ ሊያደርጉት ይገባል እንጂ፤” (ፍት.ነገ.አን.15፥፣ ቍ.
38-58)፡፡
ከላይ እንደ ገለጽነው ሩካቤ ሥጋ በሥርዓት የሚፈጸም እንደ መኾኑ የማይፈጽምባቸው ጊዜያትም አሉ፡፡
እነዚህም የሚከተሉት ናቸው ፦
የእርግዝና እና የንጽሕ ጊዜያት ሚስት በፀነሰችበት ወይም ባረገዘችበት ወቅት
በወር አበባዋ ጊዜ
በመውለጃዋ ጊዜ (ወንድ ከወለደች ከዐርባ ቀን ሴት ከወለደች ከሰማንያ ቀን በፊት) ሩካቤ ሥጋ መፈጸም አይገባም
ዘሌ. (8፥18)፡፡ ቅዱስ ባስልዮስም “በኅርሷ፣ በደሟ ወራት ሚስትህን አትድረስባት" ፡፡ ግቢህ ከመጽሐፍ ሥርዓት የወጣ እንዳይኾን” በማለት በፅንስ (እርግዝና) እና በንጽሕ ጊዜያት ማለትም በአራስነትና በወር አበባ ወቅት ግንኙነት መፈጸም እንደማይገባ አዝዟል (ፍት. ነገ. አን. 24፣ ቍ. ፷፬)፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የሚስት ፅንሷ ከታወቀ በኋላ ለመረዳዳት ካልኾነ በቀር ባሏ ሊቀርባት እንደማይገባ ተደንግጓል (አን. ፳፬፣ ቍ. ፰፻፴፰)፡፡
ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሔዱባቸው ቀናት እስራኤላውያን እግዚአብሔር ከሙሴ ጋር ሲነጋገር ከመስማታቸው (ሕጉን ከመቀበላቸው) ከሦስተኛው ቀን በፊት እንዲቀደሱ፣ ልብሳቸውን እንዲያጥቡና ሩካቤ እንዳይፈጽሙ ታዝዘው ነበር፡፡ ዛሬም በሐዲስ ኪዳን ባለ ትዳሮች ትምህርተ ወንጌል ለማዳመጥ፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል፣ ጠበል ለመጠመቅና ለመጠጣት፣ ወይም ለሌላ አገልግሎት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሔዱ ከሩካቤ ሥጋ እንዲከለከሉ ታዝዟል (ዘፀ. 19፥10-25 )፡፡ ከዚህም ሌላ በጥምቀት ክርስትና የሚያነሡ (የክርስትና እናት ወይም አባት የሚኾኑ ምእመናን) ክርስትና ከማንሣታቸው በፊትና በኋላ ለሁለት ቀናት ከሩካቤ ሥጋ መከልከል ይገባቸዋል፡፡
ይኸውም መንፈስ ቅዱስን ለማክበር ነው፡፡ ምሥጢረ ጥምቀት ጸጋን፣ ክብርንና ልጅነትን የሚያሰጥ ምሥጢር ስለ ኾነ፡፡ ካህኑ ዘካርያስ የቤተ መቅደሱን አገልግሎት ከፈጸመ ከሁለት ቀን በኋላ ከኤልሳቤጥ ጋር መገናኘቱም ለዚህ ትምህርት ነው፡፡ " ከሁለት ቀን በኋላም ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሉቃ. 1፥24፤ ፍት. ነገ. አን. 24፣ ቍ. 38)፡፡
በዓላት ቅዳሜ፣ እሑድና በዓበይት በዓላት ሩካቤ ሥጋ መፈጸም የተከለከለ ነው፡፡
ይኸውም በመንግሥተ ሰማያት ጋብቻና ፈቃደ ሥጋን መፈጸም አለመኖሩን ለማጠየቅ ነው፡፡ በዓላት፣ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌዎች ናቸውና ፡፡
“በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይኾናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡምም” እንዲል (ማቴ. 22፥23)፡፡
ሌላው ምክንያት ደግሞ “ንጹሕ የኾነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው … በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው” በማለት ቅዱስ ያዕቆብ እንደ ተናገረው (ያዕ. ፩፥፳፯)፣ በእነዚህ ዕለታት ወደ ቤተክርስቲያን በመሔድ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን መቀበልና ራስን መጠበቅ ተገቢ ስለ ኾነ ነው፡፡
ፈቃድህን በተቀደሰው ቀኔ ከማድረግ እግርህን ከሰንበት ብትመልስ፣ ሰንበትንም ደስታ፣ እግዚአብሔርም የቀደሰውን ‹ክቡር› ብትለው፣ የገዛ መንገድህንም ከማድረግ፣ ፈቃድህንም ከማግኘት፣ ከንቱ ነገርንም ከመናገር ተከልክለህ ብታከብረው፣ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፤ በምድርም ከፍታዎች ላይ አወጣሃለሁ፤ የአባትህንም የያዕቆብን ርስት አበላሃለሁ” ተብሎ ተጽፏልና (ኢሳ. 48፥13-14)፡፡
#አጽዋማት
“ጸዋሚ ሆይ፥ መላው አካልህ ይጹም፤ አፍህ ክፉ ከመናገር፣ አንደበትህ ከሐሜትና ከስድብ፣ ዓይንህ ሴቶችን ከማየት፣ ጆሮህም ዘፈንና ጨዋታ ከመስማት ይጹም” ተብሎ እንደተነገረን (ርቱዐ ሃይማኖት) ሩካቤ ሥጋም ሰውነት የሚደሰትበት ፈቃድ ስለ ኾነ በጾም ወቅት መታቀብ ይገባል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ባልና ሚስት በንስሓ አባታቸው የተሰጣቸዉን የንስሐ ቀኖና ወይም በራሳቸው ፈቃድ የገቡትን የጾም ሱባዔ እስከሚፈጽሙ ድረስ ከሩካቤ ሥጋ መከልከል ይገባቸዋል፡፡
በአጠቃላይ ባልና ሚስት በፅንስ፣ በአራስነትና በወር አበባ ወቅት፤ እንደዚሁም በበዓላትና በአጽዋማት ቀን ሩካቤ ሥጋ ማድረግ እንደማይገባቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡
ከዚህ በተረፈ ግን ሰይጣን የሚፈትንበትን ክፍተት እንዳያገኝ ባልና ሚስት ሊለያዩ አይገባም፡፡ “ለጸሎት ትተጉ ዘንድ ተስማምታችሁ ለጊዜው ካልኾነ በቀር እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን
እንዳይፈታተናችሁ ደግሞ አብራችሁ ኹኑ፤” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ (1ኛ ቆሮ. 7፥5)፡፡
ይህ የሐዋርያው ትምህርት "ሰውነታችሁን ንጹሕ አድርጋችሁ በምትጾሙበት፣ በምትጸልዩበት ጊዜ ነው እንጂ ሥራችሁን ከፈጸማችሁ በኋላ ግን ወደ ፈቃዳችሁ ተመለሱ ይላል፡፡
ይህም ትእዛዝ ባልና ሚስት፣ የጾም፣ የጸሎት፣ የበዓል ወቅት ካልኾነ በቀር ሳይለያዩ ፈቃዳቸዉን መፈጸም እንደሚገባቸው ያስገነዝባል፡፡
ለእርኩሰትና ለበደል ከሚፈፀም ሩካቤ ይጠብቀን።
ttps://t.me/OrthodoxAmero
https://t.me/OrthodoxAmero
https://t.me/OrthodoxAmero
Facebook Link follow ያድርጉ
https://www.facebook.com/deaconezemarefitsume.kebede
2.3K views£itsum, edited 04:41