2023-05-01 08:21:51
[ሚያዝያ 23 ዕረፍቱ የኾነው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋድሎ በኢትዮጵያ ሊቃውንት]
በመጋቤ ሐዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ
❖ የዚኽም ቅዱስ አባቱ በቀጶዶቅያ መስፍኑ አንስጣስዮስ ሲኾን እናቱ ቴዎብስታ ትባላለች፤ የተወለደውም በልዳ በሶርያ ፍልስጥኤም በ፪፻፹ ዓ.ም. ነው፤ ታናሽ ኾኖ ሳለ አባቱ ዐርፏል፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን ፈረስ ግልቢያን ተምሮ ኻያ ዓመት በኾነው ጊዜ ቢሩት ሀገር በመኼድ በዚያ ሀገር ይመለክ የነበረውን መንፈሰ ሰይጣን ያደረበትን የመኰንኑን ልጅ እንዲበላት የተሰጠውን ዘንዶ በክርስቶስ ስም ከገደለው በኋላ እጅ መንሻ ይዞ ወደ ንጉሠ ፋርስ ኼደ፡፡
❖ በዚያ ሀገር ግን ነገሥታቱ ጣዖታትን በማምለክ ክርስቲያኖችን ሲያሳድዷቸው አይቶ ዐዘነ፤ ልቡም በክርስቶስ ፍቅር ነድዶ ወደ ሀገሬ አልመለስም ስለ ክርስቶስ ስም እሞታለኊ አለና “ክርስቲያናዊ አነ ወአአምን በእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ” (እኔ የክርስቲያን ወገን ነኝ እምነቴም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው) በማለት መሰከረ፡፡
❖ ከዚያም ንጉሡ ልብሱን ገፍፈው በዕንጨት ላይ እንዲሰቅሉት፤ ዳግመኛ የዘንባባ እሾኽ የመሳሰሉ ፸ የብረት ችንካሮች ሠርተው በነዚያ እንዲቸነክሩትና ዐጥንቱን ኹሉ እንዲቀጠቅጡት አዘዘ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን በትዕግሥት በመኾን “እፎ ኢይኄሊ ከመ አምላኪየ ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅለ ዲበ ዕፀ መስቀል” (ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል እንደተሰቀለ እንዴት አላስብም) አለ፡፡
❖ ዳግመኛም በውስጡ ረዣዥም ችንካሮች ያሉበት የብረት ጫማን ባጫሙት ጊዜ “ሠጠቅዎ ወመተርዎ ዐሥራዊሁ እስከ ውኅዘ ደሙ ዲበ ምድር ከመ ማይ ወሶበ ስዕነ ሠጊረ ድቡተ ሖረ” ይላል ችንካሮቹ ደሙ እንደ ውሃ በምድር ላይ እስኪፈስስ ድረስ እግሩን ዘልቀው ሥሩን በጣጠሱት፤ መኼድም ባልቻለ ጊዜ አጐንብሶ ኼዷል፤ ከዚያም የፈላ የብረት ጋን ውስጥ ከትተው ሰውነቱ በደም እስኪጥለቀለቅ ድረስ ራሱን በመዶሻ ሲመቱት ወደ ጌታችን ጸለየ፤ ያን ጊዜ “ጊዮርጊስ ሆይ ከአንተ ጋር ነኝና ጽና” የሚል ቃል ከሰማይ መጣለት፤ ቅዱስ ሚካኤልም ተገልጾ ከሕመሙ ፈውሶታል፡፡ ይኽነንም ባዩ ጊዜ ብዙዎች በጌታችን አመኑ፡፡
❖ ንጉሡም ይኽነን ባየ ጊዜ እጅግ የሚያስጨንቅ መንኰራኲር ለ፵ ቀን አሠርቶ ለቅዱስ ጊዮርጊስ “እመሰ ትሠውዕ ለአጵሎን ትነሥእ ጌራ መንግሥት ወእመሰ ኊልቊ አንተ ከመ ትትልዎ ለክርስቶስ ነጽር ዘንተ መንኰራኲረ ዘግበርኩ ለከ ከመ እግድፍ በውስቴታ ታማስን ሥጋከ” (ለአጵሎን ብትሠዋ የመንግሥትን ዘውድ ትቀዳጃለኽ፤ ግን ክርስቶስን ለማገልገል የቈረጥኽ ብትኾን ሥጋኽን ትፈጭ ዘንድ በውስጧ ልትጣልባት ያዘጋጀኋትን መንኰራኲር ተመልከት) አለው፤ ይኽ ሲኾን ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈጣሪው ክርስቶስን አመሰገነ፡፡
❖ እነርሱም ወደ መንኰራኲሩ በመወርወር ፵ ሰዎች ያዞሩት ዠመር ከዚያም ሰውነቱ ለዐሥር ክፍል ተከፋፈለ፤ እነርሱም ሥጋውን በጒድጓድ ውስጥ ቀበሩት፤ ክብር ይግባውና ጌታችን መላእክትን አስከትሎ በመምጣት እንደገና ከሞት አስነሣውና ባረከው፡፡
❖ ርሱም ከሞት ተነሥቶ እንደገና ወደ ከተማ ገብቶ ስለ ክርስቶስ አምላክነት መሰከረ፤ እነርሱም እጅግ ለመስማት የሚከብዱ መከራዎችን አደረጉበትና ሰውነቱን ጨምቀው አንጀቱን ዘረገፉት፤ ከዚያም ሥጋውን አቃጥለው በዕንጨት ቀፎ በማድረግ ይድራስ ወደተባለ ተራራ ወስደው ዐመዱን በትነውት ተመለሱ፤ ክብር ይግባውና ጌታችን መላእክትን አስከትሎ በመውረድ አራቱን ነፋሳተ ምድር የተበተኑትን የቅዱስ ጊዮርጊስን ሥጋዎች እንዲሰበስቡ አዝዞ እንደገና ከሞት አስነሥቶታል፤ ይኽነንም ባዩ ጊዜ ብዙዎች በክርስቶስ አምነው የሰማዕትነትን አክሊል ተቀዳጅተዋል፡፡
❖ በመጨረሻም ብዙ ተጋድሎዎችን ለሰባት ዓመታት ከፈጸመ በኋላ ንጉሡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ራስ በሰይፍ እንዲቈረጥ አዝዞ ወደ መሰየፊያው ቦታ ሲኼድ እሳት ከሰማይ ወርዶ ፸ውን ነገሥታት ያቃጥላቸው ዘንድ መከራውም ከክርስቲያኖች ጸጥ ይል ዘንድ ጸለየ፤ ወዲያውኑም እሳት ከሰማይ ወርዶ ፸ውን ነገሥታት አቃጥሏቸዋል፤ ከዚያም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ብዙ ቃል ኪዳንን ከሰጠው በኋላ በክብር ወደ ሰማይ ወጣ፤ ከዚያም ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ ራሱን ዘንበል አድርጎ ሚያዝያ ፳፫ በሰይፍ ቈርጠውት የሰማዕትነትን አክሊል ተቀዳጅቷል፡፡
❖ ከአገልጋዮቹ የቀሩት ሥጋውን ወስደው በንጹሕ ልብስ ጠቅልለው ወደ ሀገሩ ልዳ በመውሰድ ቤተ ክርስቲያን ሠርተው በውስጡ አኖሩት፤ ከርሱም ቊጥር የሌላቸው ብዙዎች ድንቆች ተአምራት ተገልጠዋል፡፡
❖ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም፦
"ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወላዕሌነ ይኩን ምሕረት በጸሎተ ጊዮርጊስ ዐቢይ ሰማዕት ወማርያም ወላዲተ አምላክ"
(በሰማያት ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፤ አምላክን በወለደች በማርያምና በታላቁ ሰማዕት በጊዮርጊስ ጸሎት በእኛ ላይ ምሕረት ይኹን) ይላል፨
❖ ኢትዮጵያዊዉ ሊቅ አባ ጽጌ ብርሃን በማሕሌተ ጽጌ ድርሰታቸው ላይ፦
“ክበበ ጌራ ወርቅ ጽሩይ እምዕንቈ ባሕርይ ዘየሐቱ
ዘተጽሕፈ ብኪ ትእምርተ ስሙ ወተዝካረ ሞቱ
አክሊለ ጽጌ ማርያም ለጊዮርጊስ ቀጸላ መንግሥቱ
አንቲ ኲሎ ታሰግዲ ሎቱ
ወለኪኒ ይሰግድ ውእቱ”
(የስሙና የሞቱ መታሰቢያ ባንቺ የተጻፈብሽ የሚያበራ ከኾነ ዕንቈ ባሕርይ ይልቅ የጠራ ወርቅ ክበብ ያለው የራስ ቊር የተባለ የጊዮርጊስ የመንግሥቱ የራስ ልብስ ጌጥ ሽልማት የአበባ አክሊል ማርያም ሆይ አንቺ ለርሱ ኹሉን ታሰግጅለታለሽ (ታንበረክኪለታለሽ) ርሱ ግን ላንቺ ይሰግዳል) ይሉታል፨
❖ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቁ አርከ ሥሉስም የሊቀ ሰማዕታት የቅዱስ ጊዮርጊስን ተጋድሎ፡-
“ሰላም ለከ ሰርዌ ሰማዕታት አእላፍ
ዘሞገሰ ስምከ በጽሐ መንገለ ኲሉ አጽናፍ
በቅድመ ፀሓይ ብሩህ ዘኢየዐርብ ለዘልፍ
ሕማምየ ዝሩ ነሢአከ ወጸዊረከ እስትንፋሰ አፍ
ጊዮርጊስ ቀሊለ ክንፍ ከራድዮን ዖፍ”
(ዘወትር በማይጠልቅ በብሩህ ፀሓይ ፊት በምድር ዳርቻዎች ኹሉ የስምኽ ባለሟልነት የደረሰ የአእላፍ ሰማዕታት አለቃቸው ሰላምታ ለአንተ ይገባል፤ ክንፈ ፈጣን ከራድዮን ዖፍ የተባልኽ ጊዮርጊስ ሆይ የአፍ እስትንፋስን ተቀብለኽና ተሸክመኽ ሕማሜን በትን) እያለ ተማፅኖታል፡፡
❖ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በተአምኆ ቅዱሳን መጽሐፉ ላይ፦
“ሰላም ለጊዮርጊስ ሰማዕት ዘፀሓየ ጽድቅ
ዘተአምሪሁ ከመ ኆጻ ባሕር
ዘኢይትኌለቊ ኮከበ ክብር
ዘማእከለ ሰማይ ወምድር
ዘአርአየ ኀይለ በዲበ ሰሌዳ መንበር
ብእሲ አዛል ወመስተጋድል
ኀያል ዝሕዙሐ ገድል”፡፡
(ገድሉ የበዛ የተትረፈረፈ ኀያል፤ ተጋዳይ ጐልማሳ (ብርቱ) ሰው፤ በተዘረጋ ዙፋን ላይ ኀይልን ያሳየ፤ በሰማይና በምድር መኻከል ያለ የማይቈጠር የክብር ኮከብ፤ ተአምሩ እንደ ባሕር አሸዋ የበዛ የኾነ፤ የፀሓየ ጽድቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ሰማዕት ለኾነ ለጊዮርጊስ ሰላምታ ይገባል) ይለዋል፨
❖ የስብሐተ ፍቁር ዘጊዮርጊስ ደራሲ ኢትዮጵያዊዉ ሊቅ፦
"እምብሩር ወወርቅ ይትበደር ሞገሱ
ለጊዮርጊስ ቅዱስ በዲበ ጸዐዳ ፈረሱ
ለረዲኦትነ ይምጻእ ወያንሶሱ"
(ከወርቅና ከብር ይልቅ ሞገሱ የሚበልጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ በነጭ ፈረሱ እኛን ለመርዳት ይምጣ፤ ይመላለስም) ይለዋል፨
[ከመጋቤ ሐዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ] [በድጋሚ ፓስት ያረኩት)
2.6K views£itsum, 05:21