Get Mystery Box with random crypto!

.. ከመብረቅ ወይስ ከሊቅ? (ከማዕበል ፈጠነ) ሊቀ ጳጳስ ሲሞት ጳጳስ የሚሆን ልጅ ተጸንሶ ያ | ኦርቶዶክሳዊ አእምሮ

.. ከመብረቅ ወይስ ከሊቅ?


(ከማዕበል ፈጠነ)
ሊቀ ጳጳስ ሲሞት ጳጳስ የሚሆን ልጅ ተጸንሶ ያድራል። ንጉሥ ከዙፋን ሲወርድ ንጉሥ ተወልዶ ያድራል። ሊቅ ሲሞት መጻኢው ሊቅ በማሕፀን ተቀርጾ ያድራል ይላሉ አበው በእሳት ዳር ወጋቸው።
"የኔ ሊቀ ሊቃውንት ግን ማን ሲሞት ተወልደው እንዳደሩ አላውቅም። ርሳቸውም ቀለም እንጂ የራቸውን ስዉር ምስጢር ሲናገሩ ሰምቼ አላውቅም።

የኔ ሊቅ ሆይ! ማን ሲያርፍ ተጸነሱ?
ባለ ቅኔው ክፍለ ዮሐንስ?
ያ ፍጹም ባሕታዊ ዮሐንስ ገብላዊ?
ወይስ ጠቢቡ ተዋነይ?
ዶሪ የቅኔው ፈጣሪ ?
ወይስ ግጨው መንክር?
ገብረ ሥላሴ ዘደብረ ኤልያስ? እረ ለመሆኑ በማን እግር ተወለዱ?
ልደትዎ ከሊቅ ወይስ ከመብረቅ?

.. ጊዜው ልጅ እያለሁ ነው። ከቅኔ ቤት ወደ ቅኔ ዘወር ዘወር ስል ድንገት ልቤ ኮበለለ። አውራ እንደ ሌለው ንብ በየደብሩ የተዝረከረኩ የቅኔ ሊቆች ጠቅጥቄ ወደ ትልቁ ሊቅ ወጣሁ። ደጋው ዝናም አዝሏል። የነፋሱ ፉጨት ጆሮ ይጋረፋል። ወደ ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው ቅኔ ቤት ደረስሁ። ጀንበር ጠልቃ ነበር። ወደ ማኅበር ቤቱ ጠጋ ብዬ ቆምሁ። ያ ሁሉ ወፈ ሰማይ ተማሪ ባንዲት ቅጽበት ጸጥ አለ። ወዲያው እንደ ነጎድጓድ የማያዝገመግም ድምፅ ሰማሁ። የደ ቤት ግስ ላይ ደርሰዋል።
አሐደ!
ነደ!
አለደ!
ፈቀደ!
የሚሉ ግሶችን በመብረቃዊ ድምፅ መገሰስ ጀመሩ።
ሊቀ ሊቃውንቱ ነበሩ!!
ድምፃቸው ከነጎጓድ ይቀዳል። ቀለማቱ ኩልልል ብለው በእግራቸው ሲሄዱ አየሁ። ወዲያው ቅኔ ተዘረፈ። ማኅበር ቤቱ ተናወጸ። ጩኽ ጩኽ አለኝ። ውስጤን የፍሥሓ ስሜት ወረረው።
እነሆ የምሽቱ ቅኔ በዚሁ አበቃ። አንድ ተማሪ በእንግዳ ወግ ተቀበለኝ።
በዚች ሌሊት ከሊቀ ሊቃውንት ቤት ታቦት ተሸክሜ ስወጣ አየሁ። ትርጉሙ ከበደኝ። ታቦት ክቡድ ነው። በቃ መሞቴ ነው ስል የልጅነት ሕልሜን ተረጎምሁት። ሕልም እልም ሆነ። እስከ አሁን በሕይወት አለሁ።
ከሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው እግር ሥር በዚህ መልኩ በቀልሁ።

ያን ጊዜ ጥሬ ድንጋይ ነበርሁ። ሊቁ ቀደምት ድንጋዮችን በምሥጢር ነበልባል ሲቀቅሉ የጢሱ ወላፈን ነካኝ። አሁን ላይ አያሌ ሊቃውንት በእውቀት እየቀረጹ ይገኛሉ። ጉባኤ ከተከሉበት ጀምሮ እስከ አሁንም ድረስ በዐሥር ሺ የሚቆጠሩ ሊቃውንትን በረቀቀ ቅኔ ወልደው አሳድገዋል። በሥጋም በቀለምም የወለዷቸው ደግሞ በእግራቸው ተተክተዋል።
በቀለምም በልደትም በኩራቸው የቅኔ በኩራችን
መ/ር ቅዱስ ያሬድ እነሆ አለልን!! ስለ እንቆ (ቆ) ባሕርይ ልደት እሱ ቢነግር ደግሞ የረቀቀው ይጎላል። የጎደለው ይሞላል።

በዚህ ቅኔ ቤት ዓመታት ቀርቶ አንዲት ሌሊት ብቻ ያደረ መጻኢ ሕይወቱ የቀለም ቀንድ ይሆናል። ውኃውን የቀመሰ ሕይወቱ ብሩህ ነው። ከዓመት እስከ ዓመት መወድስ የሚፈላበት የሊቀ ሊቃውንት ጥዑም አንደት አሁን ድረስ ይናቀኛል። ገና ዓለም በጨለማ ሳለ ጠቢባንን የወለዱ የሊቀ ሊቃውንት ልዕልና በአደባባይ ይነገር። በቃልም በጽሑፍ ሊቃውንት ይቅደሙ!!

ከሊቅ የተወለደ ሊቅ ሲሆን ከመብረቅ የተወለደ ግን መብረቅ ነው። የኔታ ሆይ! ልደትዎ ከሊቅ ወይስ ከመብረቅ!?

አንባቢያን ሆይ! ስለ የኔታ በፌስ ቡክ ልጽፍ አስብና የትልቁን ሊቅ ክብር እዳፈራለሁ እያልሁ ስፈራ እኖር ነበር። ዛሬ ግን ዝምታዬን ሰብሬአለሁ። እናንተም በገጻቸችሁ የምታውቋቸውን ሊቃውንት ዝክረ ታሪክ ወዲህ በሉ!!


https://t.me/OrthodoxAmero
https://t.me/OrthodoxAmero
https://t.me/OrthodoxAmero

Facebook Link   follow ያድርጉ
https://www.facebook.com/deaconezemarefitsume.kebed