2023-05-08 21:48:22
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል በሀገራችን ኢትዮጵያ ብሔራዊ በዓል ሆኖ ሊከበር እንደሚገባ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ሊቀ ጳጳስ አስታወቁ!
ብፁዕ አቡነ ሔኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል እና የኢቲ አርት ሚዲያ የበላይ ጠባቂ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን የልደት በዓልን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል!
"ወሶበ አኮ እግዚአብሔር ጸባኦት ዘአትረፈ ለነ ዘርዐ ከመ ሰዶም እምኮነ ወከመ ገሞራ እመሰልነ ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ፥ እንደ ሰዶም በሆንነ እንደ ገሞራም በመሰልነ ነበር።”
— ኢሳይያስ ፩፥፱
በመላው ዓለም የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ምዕመናንና ምዕመናት
በባሕርዩ ሞት በመንግስቱ ሽረት የሌለበት ቅዱስ እግዚአብሔር አምላካችን በንጽሕና በቅድስና ያጌጠች ፣ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ያልነካት፣ የድኅነታችን ምክንያት ፣ የንጽሕናችን መሠረት ንጽሕት የሠርግ ቤት ለሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ልደት እንኳን አደረሰን አደረሳችሁ !
አዳም በኃጢአት ከወደቀ በኋላ ፣ ንስሐ በገባ ጊዜ እግዚአብሔር አምላካችን የድኅነት ቃል ኪዳን ገባለት፡፡
አዳም አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም የሕይወት ምክንያት የሆነች የልጅ ልጁ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከአብራኩ ከተከፈሉ ቅዱሳን ልጆቹ የምትወለድበትን ቀን ተስፋ እያደረገ ኖረ።
ለድኅነተ ሰብእ ምክንያት የሆነች እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ከቅዱስ ኢያቄም እና ከቅድስት ሐና ነሐሴ ፯ ቀን ተፀንሳ ግንቦት ፩ ቀን ተወልዳለች፡፡
እርስዋም ስትፀነስ ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ ከአዳም የውርስ ኃጢአት (ጥንተ አብሶ) ጠብቋት የአዳም አበሳ አልነካትም፡፡ ይህንንም ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ፈጽሞ በኃጢአት በተከበበ፣ መርገም በሞላበት ዓለም ውስጥ ከኃጢአት ከበደል ተለይታ ንጽህት መሆኗን ሲያስረዳ "የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር (ኢሳ ፩፡፱)" በማለት ተናግሯል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን
ምዕመናንና ምዕመናት
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መዝሙረኛው ዳዊት እንደተናገረ "መሠረቶቿ የተቀደሱ ተራሮች ናቸው (መዝ ፹፮ ፥ ፩) እንዳለ ከቤተ መንግስት እና ከቤተ ክህነት የተቀደሱ ተራሮች ከተባሉት ከእሴይ ሥር እና ከአሮን ወገን የተገኘች ናት።
ይህች ዕለት በሊቃውንቱ አንደበት ትልቅ ሕንፃ የታነጸበትና ፍጡር የፈጣሪ ማደሪያ ለመሆን የተዘጋጀባት ዕለት መሆኗ ይነገራል (ቅዱስ እንድርያስ እንደተናገረ)። ይኸውም የሆነው ከሞት ወደ ሕይወት ከጥፋት ወደ ድኅነት መንገድ ለመጓዝ በበጉ በክርስቶስ ደም ለመታጠብ እና ምድር ከዚህ የጨለማ ሕይወት እንድትወጣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም መወለድ አስፈላጊ ስለሆነ ነው።
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ሐዋርያትና ሐዋርነ አበው እንዳስተማሩን የንጽሕናችን መሠረት ወላዲተ አምላክ እናታችን ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፥ ከሥሩም ቍጥቋጥ ያፈራል (ኢሳ ፲፩፥፩) ተብሎ ትንቢት የተነገራለትን እመቤት የድንግል ማርያምን በዓለ ልደት በፍፁም ደስታ እና በልዩ ሥነ ሥርዓት ታከብረዋለች።
የእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መወለድ የነቢያቱ ትንቢት የተፈፀመበት ፣ የብሉይ ኪዳን ማብቂያ የሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ ናትና ልደቷ ለሰው ልጆች ሁሉ ታላቅ የደስታ ቀን ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም የቅድስት ድንግል ማርያምን ልደት የምታከብረው ከዚህ ታላቅ በዓል በረከት ረድኤትን እንድናገኝበት ነው፡፡
በመሆኑም በመላው ዓለም የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ልጆቻችን በዓሉን በፍፁም ደስታ ካለንበት የትንሣኤ በዓል ጋር ሊያከብሩት እና ልናከብረው ይገባል።
በተለይም ደግሞ በዓሉ እንደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ብሔራዊ በዓል ሆኖ የሚከበርበት እና የአበውን ትውፊት በጠበቀ መልኩ እንደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓትም በየአቢያተ ክርስቲያናቱ በልዩ ልዩ ሥነ ሥርዓት ከማክበር በተጨማሪ በማዕከል ደረጃ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሀገር በሚጠቅም መልኩ የሚከበርበት ሁኔታ እንዲመቻች የሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ተነሳሽነት እና የጉዳዩን አስፈላጊነት መረዳት በእጅጉ ያስፈልጋል።
በመጨረሻም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን የልደት በዓል በምናከብርበት ወቅት የሰላም አለቃ የተባለ ክርስቶስን የወለደች (ኢሳ ፱፥፮) እመቤታችን መሆኗን በመረዳት በሀገራችን ኢትዮጵያ የራቀንን ሰላም እና ፍቅር በወንድማማችነት እና በመተሳሰብ መንፈስ ላይ ተመሥርተን ልንመልሰው እና በየአካባቢው የሚታየውን ጭካኔ የተሞላበት የመጠፋፋት አካሄድ ቆም ብለን ልናስብበት እና ወደ ውይይት መመለስ እና ሰላምን ለማጽናት ቁርጠኛ መሆናችንን በማረጋገጥ ሊሆን ይገባል። እንዲሁም ለተራቡ እና ለተቸገሩ ወገኖቻች ቸርነትን በማድረግ ክርስትናችንን በተግባር በመግለጽ ጭምር በዓሉን ማክበር እንደሚገባ እናሳስባለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አሜን !
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ይባርክ
አባ ሄኖክ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ የተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከልና የኢቲ አርት ሚዲያ የበላይ ጠባቂ
ሚያዝያ ፴ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
#Ethiopia
#Tewahedo_Media_Center
#TMC_Addia_Ababa
ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል
እውነተኛ የተዋሕዶ ድምፅ
https://t.me/OrthodoxAmero
https://t.me/OrthodoxAmero
https://t.me/OrthodoxAmero
Facebook Link follow ያድርጉ
https://www.facebook.com/deaconezemarefitsume.keb
2.8K views£itsum, edited 18:48