2023-04-20 11:10:40
ክርስቲያኖች ምን ይመገቡ ?
ፍትሐ ነገሥት ክፍል ፲፯አ
ንቀጽ ፳፫ ለክርስቲያኖች ስለሚገቡ ምግቦች፣ ልብሶች፣ ስለ ቤት እና ስለ ተግባረ እድ ይናገራል።
፩) በወንጌል የተከለከሉ ምግቦች ደም፣ ጥሬ ሥጋ፣ ታንቆ የሞተውን፣ ለጣዖት የተሠዋውን፣ የአውሬውን ትራፊ፣ ሙቶ የተገኘውን፣ ሲያርዱ አንገቱን ቆርጠው የጣሉትን ናቸው። ለጣዖት የተሠዋውን አትብሉ የተባለበት ምክንያት ምእመናን ወደ ጣዖት አምልኮ እንዳይሳቡ ነው።
_
፪) ርኵስ ፍጥረት እንደሌለ እግዚአብሔር የፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ንጹሕ እንደሆነ ተጽፏል። መጽሐፍ ከከለከለው በቀር ከምግብ ሁሉ እንዳንከለከል መሆን ይገባናል።
_
፫) አእምሮ ወደማጥፋት የሚያደርስን ምግብ፣ አራቱን ባሕርያትን የሚያነዋውጽን ምግብ፣ አካል የሚያጎድልን ምግብ መብላት አይገባም። ይኽውም መርዝ እንዳላቸው እንስሳትና እፀዋት ያሉትን ነው።
_
፬) አትብሉት ከተባለው የምግብ ወገን ደህነኛውን የሚገድል ድውዩን የሚፈውስ ቢሆን ደህነኛው ከመብላት ይከልከል። ድውዩ ግን የሚያድነው ከመሆኑ የተነሣ መብላት ይገባዋል።
_
፭) ሁሉን ሊበሉት እንዲገባ የሚያምን ሰው ሁሉን ይብላ። የሚጠራጠር ሰው ግን እህል ይብላ። ሁሉን የሚበላ አረማዊም ሁሉን የማይበላ አይሁዳዊን ሃይማኖተ ግብዝ ብሎ አይንቀፈው። ሁሉን የማይበላ አይሁዳዊም ሁሉን የሚበላ አረማዊን ይህ ሁሉ በአፌ ብሎ አይንቀፈው።
_
፮) ለሰው ክፉ ነገር እየተጠራጠሩ መብላት ነው። በሃይማኖት የማይሠራው ሥራ ሁሉ ኃጢአት ነው። ለጣዖት የተሠዋውንኳ አምነው ቢበሉት ጉዳት አያመጣም።
_
፯) በመብል ምክንያት ወንድምህ የሚጎዳ ከሆነ የተፈቀደውን እንኳ ስለእርሱ ብለህ አትብላ።
_
፰) በገበያ የሚሸጠውን ሁሉ ብሉ። ፍጥረቱ ሁሉ የእግዚአብሔር ገንዘብ ነውና። እያመሰገኑ ቢቀበሉት ሁሉም በስመ እግዚአብሔር ይከብራል።
_
፱) ካላመኑ ሰዎች ወገን የጠራችሁ ሰው ቢኖር እና ልትሄዱ ብትወዱ ሳትመራመሩ ያቀረቡላችሁን ሁሉ ብሉ። ለጣዖት የተሠዋ ነው ቢላችሁ ግን አትብሉ።
_
፲) በቀለም ያስጌጧቸውን ልብሶች ከመልበስ መጽሐፍ ከለከለ። ቤተመቅደስ ገብተው እግዚአብሔርን ሲያገለግሉ የሚለብሱት ልብስ ነጭ ሊሆን ይገባል።
_
፲፩) ሴቶች የወንድ ልብስ አይልበሱ አለ። እጀ ሰፊ ቀሚስ፣ ሱሪ አይታጠቁ። አርዓያ መለወጥ ሥርዓት ማፍረስ ነውና። ወንዶችም የሴቶችን ልብስ አይልበሱ። ይኽውም እጀ ሰብስብ ቀሚስ አይልበሱ።
_
፲፪) ወንዶች ከጣታቸው ቀለበት አያግቡ የምንዝር ጌጥ ነውና። ሴቶች በወርቅ የተጌጠ የሚያስመካ ልብስ አይልበሱ። ሹማምንት ግን ያጌጠ ልብስ ቢለብሱ ይገባቸዋል።
_
፲፫) መነኮሳት ከፀምር ወገን ደጓሳ ልብስ ይልበሱ።
_
፲፬) ማንኛውም ሕዝብ የወደደውን መልበስ ይገባዋል። ዘመን ያስገኘውን መልበስ ዘመን ባስገኘው ማጌጥ ይገባቸዋል። ከሕዝባውያን ወገን ብዙዎቹ ሰዎች ያገኙትን መልበስ ይገባቸዋል።
_
፲፭) ካህናት የወታደር ልብስ አይልበሱ። ካህናት የአናፂ ልብስን አይልበሱ።
_
፲፮) ወጠቢብኒ ቅዱስ ባስልዮስ ይቤ ይደሉ ለነ ከመ ንሥራዕ ልብሰነ በዘንከድን ዕርቃነነ። ዕርቃናችንን እንሠውር ዘንድ ልብስ መሻት ይገባናል። ወንድኃን እምቍር ወዋዕይ። ከቀን ሐሩር ከሌሊት ቁር ለመዳን ልብስ ያስፈልጋል [ቁጥር ፰፻፲፬]።
_
፲፯) ለሚኖሩበት ሰዎች ይጠቅም ዘንድ፣ ይሠውራቸው ዘንድ፣ ምግባቸውን ንብረታቸውን ያስቀምጡበት ዘንድ፣ ይሰበሰቡበት ዘንድ፣ ቤት መሥራት ይገባል።
_
፲፰) ጌታ ለወልደ እጓለ እመሕያውሰ አልቦቱ ኀበ ያሰምክ ርእሶ ተብሎ እንደተነገረው ቤት እንዳልነበረው ሁሉ ለባሕታውያንም በዚህ አብነት ቤት የላቸውም።
_
፲፱) የእንግዳ መቀበያ ይሆን ዘንድ ቤት ያስፈልጋል።
_
፳) ከሥራይ፣ ከጥንቆላ፣ ጣዖትን ከመሥራት፣ ከመዝፈን፣ ከተውኔት በስተቀር ክርስቲያን ሥራን ሁሉ መሥራት ይገባል።
_
፳፩) አንጥረኛ ሁሉ ጣዖት ከመሥራት ይከልከል። ከአመነ ከተጠመቀ በኋላ ይህን የሚያደርግ ቢኖር ንስሓ ይግባና ይተወው።
_
፳፪) ለጣዖት በገና የሚደረድር፣ የሚዘፍን ቢኖር በቀኖና ይለይ። ያም ባይሆን በውግዘት ይለዩ።
_
፳፫) ለክርስቲያኖች የሚገቡ ሥራዎች ግብርና፣ ማስገር፣ ልብስ መስፋት፣ ልብስ መሥራት፣ ቤት መሥራት፣ ሕክምና፣ አንጥረኝነት፣ ጠራቢነት፣ ጸሓፊነት፣ እንጀራ ጋጋሪነት ወጥ ሠሪነት፣ መምህርነት፣ ነጋዴነት፣ መርከብ መሥራት እና የመሳሰሉት ናቸው። ንግድ ከአንዱ ሀገር ያለውን ወደ አንዱ ሀገር ለመውሰድ በግድ ያለውድ ያሻል [ቁጥት ፰፻፳፬]።
_
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
ክፍል ፲፰ ይቀጥላል
መ/ር በትረማርያም አበባው
https://t.me/OrthodoxAmero
https://t.me/OrthodoxAmero
https://t.me/OrthodoxAmero
Facebook Link follow ያድርጉ
https://www.facebook.com/deaconezemarefitsume.kebede
3.7K views£itsum, edited 08:10