2022-12-21 19:24:16
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር ያላትን ግንኙነት ልታቋርጥ እንደምትችል ገለጸች።
ታኅሣሥ 12 ቀን 2015 ዓ.ም (ተ.ሚ.ማ/ አዲስ አበባ)
ከሰዓታት በፊት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ እንደሚሰጥ መግለጻችን ይታወሳል። ነገር ግን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤትና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊና የኒውዮርክና አካባቢው አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቢገኙም ጉባኤው ሳይካሄድ ቀርቷል።
ከመግለጫው መቅረት በኋላ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ብፁዕ አቡነ አብርሃም እና ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ መግለጫ ሰጥተዋል።
የጉባኤውን መቅረት አስመልክቶ በትናንትናው ዕለት በተካሔደው በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ስብሰባ ተገኝተው የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ እንደገለጹት የውይይቱ አጀንዳ 'በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየተካሔደ ያለው ሃይማኖታዊ ማኅበራዊና ታሪካዊ ጥቃት ' በሚል እንደነበር የጠቀሱ ሲሆን በዛሬው ዕለት ታኅሣሥ 12 ቀን 2015 ዓ.ም በጉባኤው በላይ ጠባቂ አባቶች በወቅታዊ ጉዳይ የሰላም ጥሪና መግለጫ እንዲሰጥ ወስነው እንደነበር አስረድተዋል።
ነገር ግን በዛሬው ስብሰባ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ተወካይ በቀር እስልምናን ጨምሮ የማንም ቤተ እምነት ተወካዮችአልተገኙም። በዚህ ምክንያት መግለጫው ሳይሰጥ ቀርቷል ብለዋል።
አክለውም ይህ የቤተ ክርስቲያንን ኅልውና የሚፈታተን ሆኖ አግኝተነዋል ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ።
ብፁዕ አቡነ አብርሃም በበኩላቸው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሥራው ሃይማኖቶች ሌላውን ሳይተቹ በጋራ በፍቅር ለአንዲት ሀገር የሚቆሙበትን መንገድ ለመፍጠር የእንደሆነ ጠቅሰው የተደረገው ድርጊት እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።
ቤተ ክርስቲያን ብዙ ፈተና ቢያደርሱባትም እንደእናት እየታገሰች እስከዛሬ ድረስ ጥራለች ሲሉም አክለዋል።
ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት በአንድ አይነት ድምፅ ተናብበው በመቅረታቸው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ያዩበት ዐይን ጤናማ እንዳልሆነ ተገንዝበናልም ብለዋል።
በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ቤተ ክርስቲያን ከሀይማኖት ተቋማት ጋር ያላት ግንኙት ይቋረጣል። ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያንን ክብር ከምንም አላዩትም ያሉት ብፁዕ ሥራ አስኪያጁ ቤተ ክርስቲያን ሲፈልጉ የሚያከብሯት ሌላ ጊዜ ደግሞ የሚያዋርዷት ቤተ ክርስቲያን እንድትሆን አንፈልግም ሲሉም ጠቅሰዋል።
በመጨረሻሞ ወጣቶች ጉዳዩ ስሜታዊ ቢያደርግም ሰዎች በሚፈልጉት መንገድ እንዳንጓዝ ያስፈልጋል። ቤተ ክርስቲያን ጸብ እንድታጭር የሚፈልጉ አሉ ስለዚህም መጠንቀቅ ያሻል ሲሉም አሳስበዋል።
ምንጭ
ተዋሕዶ ሚዲያ ማዕከል
እውነተኛ የተዋሕዶ ድምፅ
2.0K views✞£iŧsûm✞, 16:24