Get Mystery Box with random crypto!

~ ተአምረ ማርያም ያጽናናዋል ~ ተአምርዋን የሰማ ሥጋ ወደሙን እንደተቀበለ ይሆንለታል’ የሚለው | ኦርቶዶክሳዊ አእምሮ

~ ተአምረ ማርያም ያጽናናዋል ~


ተአምርዋን የሰማ ሥጋ ወደሙን እንደተቀበለ ይሆንለታል’ የሚለውን ቃል በመጥቀስ ‘እንዴት የክርስቶስ ሥጋና ደም ከተአምረ ማርያም ጋር ሊተካከል ይችላል?’ የሚል ጥያቄ ነው፡፡ ይህም ጥያቄ ከፕሮቴስታንት አቅጣጫ መነሣቱ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ እኔ መረጃ አጥሮኝ ካልሆነ በቀር ከመቼ ወዲህ ነው አንድ ፕሮቴስታንት የሥጋ ወደሙ ተቆርቋሪ የሆነው? የአስተምህሮ ለውጥ ተደርጎ እንደሆነ አላውቅም፡፡ በብዙ ለዘመናት ጸንቶ እንደተቃወመው ግን ፕሮቴስታንቲዝም በክርስቶስ ሥጋና ደም አማናዊነት ጨርሶ አያምንም፡፡ ጌታችን ‘ይህ ሥጋዬ ነው ይህ ደሜ’ ነው ብሎ የሠጠውን ምሥጢረ ቁርባንም ‘አብሮ ከሚበላ የመታሰቢያ ማዕድነት ያለፈ ፋይዳ የለውም’ በሚል አቋም የፕሮቴስታንቱ ዓለም ከካቶሊክና ኦርቶዶክሱ ዓለም ጋር ሲሟገት የአምስት መቶ ዓመት ዕድሜውን እንዳሳለፈ ሁላችን የምንስማማባቸው የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ እነርሱ እንደሚሉት ሥጋ ወደሙ ተራ የመታሰቢያ ማዕድ ከሆነ ደግሞ እውነትም ከመብላት መስማት የተሻለ ጥቅም አለውና ይህንን ቃል ሊቃወሙ የሚችሉበት መሠረት አይኖራቸውም፡፡

የተአምረ ማርያም መቅድም ግን ጉዳዩን የሚጀምረው ተአምርዋን መስማት ምንኛ ከሥጋ ወደሙ ያነሠ መሆኑን በመግለጽ ነው፡፡ ሰው ‘ሥጋውንና ደሙን ይቀበል ፤ ሥጋ ወደሙን ለመቀበል የሚከለክል የታወቀ ምክንያት ከገጠመው ግን ተአምርዋን ሰምቶ ይሒድ’ የሚለው ንግግር ሥጋ ወደሙን ለመቀበል የማይችል ሰው ተአምርዋን መስማት እንደሚችል ያስረዳል፡፡ ተአምረ ማርያም ከሥጋ ወደሙ እኩል ቢሆን ኖሮ ሰውዬውን ሥጋ ወደሙን ከመቀበል የከለከለው ምክንያት ተአምርዋንም ከመስማት ይከለክለው ነበር፡፡ ለምሳሌ ‘በአካል መጥተህ እንድታገኘኝ ነገር ግን በአካል ለመምጣት ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ባትችል ቢያንስ በስልክ ደውልልኝ ፤ ከደወልህልኝ እንደ መጣህ እቆጥረዋለሁ’ ብለህ ለወዳጅህ ነገርኸው፡፡ ይህ ዓረፍተ ነገር በአካል መምጣትና በስልክ መደወልን እኩል ያደርጋል ማለት አይደለም፡፡

በአጭሩ ዓረፍተ ነገሩ ሥጋ ወደሙን ዘወትር በመቀበል ሕይወት የሚኖርን ክርስቲያን የሚመለከት ቃል ነው፡፡ ይህ ክርስቲያን ፍጹም መንፈሳዊ ሕይወትን እየኖረ እንዳለ ምስክር የሚሆነው ሥጋ ወደሙን ከመቀበል የሚከለክለው ደዌ ወይም የታወቀ ምክንያት እንጂ አልቆርብም የሚል የኃጢአት ሰበብ አይደለም፡፡ እንዲህ ላለው ትጉሕ ቆራቢ ሰው ሁልጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን እየገሠገሠ መቁረብ ልማዱ ነውና አስቀድሶ አለመቁረብም ኀዘን ይሆንበታል፡፡ ለዚህ ሰው መቅድመ ተአምረ ማርያም ያጽናናዋል፡፡ ‘የታወቀ ምክንያት ወይም ሕመም ስለከለከለህ ባለመቁረብህ አትዘን ቢያንስ ተአምርዋን ሰምተህ ሒድ ፤ በዚያ ዕለት ልትቆርብ ተመኝተሃልና ሰምተህ በመሔድህ ያን ቀን ብትቆርብ የምታገኘውን በረከት አላስቀርብህም’ ነው፡፡ ይህ ግን ንስሓ አልገባም አልቆርብም ተአምርዋን ሰምቼ ይበቃኛል የሚል ብልጣ ብልጥ ትዕቢተኛ ሰው የሚሠራ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ይህንን ዓይነቱን ሰው ከመቁረብ የሚከለክለው ‘የታወቀ ምክንያት ወይም ደዌ ሳይሆን’ የኃጢአት ፍቅር ነው፡፡



ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

+ ተአምረ ማርያምና አንዳንድ ጉዳዮች +
(ክፍል አንድ)

የተወሰደ ።