2023-05-04 09:12:13
ለሁሉም ኦርቶዶክሳውያን በሙሉ
‹‹በመምህር አምላክ ክፍል ሁለት››
ለሁሉም ኦርቶዶክሳውያን በሙሉ በዚህ ዓመ ሢመተ ጵጵስና እንዳይደረግ ስለመጠየቅ
ደፋሮች ከመብዛታቸው የተነሳ ቤተ ክርስቲያንን ሳይቀር መዳፈር ከጀመሩ ውለው አድረዋል፤ ጉዳዩ ከሕዝብ ሳይደርስ ይፈታል በሚል ተስፋ ብዙ ዓመታት ታግሰን ቆይተናል፡፡ ዘንድሮ ግን ችግሩ ሊሰወር ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሶ እንደ ተራራ ላይ መንደር፤ መቅረዝ ላይ እንዳለ መብራት ለሁሉ የሚታይ ሁኗል ከዚህ በኋላ እንደ ቀድሞው በዝምታ ማለፍ ግን ለተመልካቹ ምእመን ይህ ስህተት ትክክል ነው ብሎ እንደ ማስተማር የሚቆጠር ድፍረት ስለሆነ እውነትና ሐሰቱን በአደባባይ ለመናገር ተገደናል፡፡
ባለፈው ጽሑፌ አሁን ለጵጵስና ሲመት አጣዳፊ ሁኔታ እንደሌለ እና ሢመቱም ከተፈጸመ ቤተ ክርስቲያን ወደማትወጣው ከባድ ችግር እንደምትገባ ለመጠቃቀስ ሞክሬ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ሹመት ይገባናል ባይች ምን እያደረጉ እንደ ሆነ ምእመናን አውቀው ለቤተ ክርስቲያን ዘብ እንዲቆሙ ለማነቃቃት ተመልሻለሁ፡፡ ሹመት ፈላጊ መነኰሳት ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ሀገር ተሰባስበው በጠቅላይ ቤተ ክህነት እና በየሀገረ ስብከቱ ግቢ ገንዘባቸውን ማፍሰሱን ተያይዘውታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከየገዳማቱ ከየመናኞቹ ይሆናል ያለችውን በጸሎት እና በሕጋዊ ምርጫ መምረጥ እንዳትችል በሴት ወይዘሮ፣ በወንድ መኰንን፣ በአማላጅ በአጓዳጅ፣ ለመሾም የሚደረገውን ሩጫ ለተመለከተ ሰው ውነትም ከዘመኑ መጨረሻ ደርሰናል አሰኝቶ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡
ለመሆኑ እነዚህ ግለሰቦች ይህንን ሹመት ምን ሊሠሩበት አስበው ነው የሚሽቀዳዳሙለት?
ገንዘብ ያልጠገቡት ገንዘብ እናገኝበታልን ብለው፤
አንዳንዶቹ ሃይማቱ ሳይኖራቸው ቤተ ክርስቲያንን የፖለቲካ ማስፈጸሚያ ለማድረግ የተመለመሉ ናቸው፡፡
ገንዘብ የሞላቸው ምድራዊ ርካሽ ክብር (ስብሓት ብጡል) እናገኝበታልን ብለው ነው፡፡ እንጂ እንጸድቅበታልን ቤተ ክርስቲያንን እናግዝበታለን ብለው እንዳል ሆነ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ምክንያቱም እንጸድቅበታለን ባዮቹ፤ ቤተ ክርስቲያንን እንረዳበታለን ባዮቹ ሹመቱ ፈልጎ ተማጽኖ ያገኛቸዋል እንጂ እነ አርሱ ሹመቱን ሲፈልጉት አይገኙም ይገባናል ብለውም አያስቡም፡፡
ማስጠንቀቂያ ለምእመናን
በሀገር ልጅነት፣ በግል ትውውቅ፣ በመንፈሳዊ አባት እና ልጀነት፣ ወይም በሀብታችሁ በሥልጣናችሁ ታዋቂ ስለሆናችሁ ወደየጳጳሳቱ ለሹሙልን ምልጃ የምትሄዱ ቤተ ክርስቲያንን ከሚያቃጥሉት ሰዎች እኩል እየበደላችሁ መሆኑን ዕወቁ፡፡
በተጨማሪም በየአካባቢያችሁ የመንግሥት ባለሥልጣናትን፤ ታዋቂ ግለሰቦችን፣ አድባራት እና ገዳማት፣ ማኅበራትን፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶችን ሽምግልና እየላኩ ለመሾም የሚሞክሩ ሰዎችን አይታችሁ እና ሰምታችሁ ዝም ካላችሁ(የማታጋልጡ ከሆን) ቤተ ክርስቲያን ስትዘረፍ፣ እሳት ሲለኮስባት፣ ቅርሷ ሲወድም አይቶ ዝም ከማለት ጋር እኩል ስለሆነ እንዲህ አይነት ግለሰቦችን ለማጋለጥ ተዘጋጁ፡፡
በመጨረሻም መታወቅ ያለበት ጉዳይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከ1600 ዓመታት በላይ በአንድ ጳጳስ የኖረች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ አሁን ከ50 በላይ ጳጳሳት አሉ፡፡ ችግራችንም የጳጳሳት ቁጥር ማነስ ሳይሆን ያሉት እንደሚገባ አለማገልገል እንደሆነ ባለፈው በችግሩ ጊዜ ከጳጳሳቱ አንደበት ሰምተናል፤ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያንን ወደባሰ ችግር የሚወስድ ስለሆነ በአሁኑ ሰዓት ለፖለቲካ ማስፈጸሚያ የሚካሄደው የጵጵስና ሹመት አያስፈልግም የሚለውን ከሊቅ እስከ ደቂቅ በአንድነት ማስተጋባት እና ቤተ ክርስቲያንን ማስከበር የዛሬ ሥራችን ነው፡፡
‹‹በመምህር አምላክ በሚመጣው ግንቦት ሢመተ ጵጵስና እንዳይፈጸምብን››
መ/ር ኀይለ ማርያም ዘውዱ ዘቦሩ ሜዳ
ሚያዝያ 25/2015 ዓ ም
https://t.me/OrthodoxAmero
https://t.me/OrthodoxAmero
https://t.me/OrthodoxAmero
Facebook Link follow ያድርጉ
https://www.facebook.com/deaconezemarefitsume.kebed
4.2K views£itsum, edited 06:12