Get Mystery Box with random crypto!

#የሚያዝያ #ድርሳነ #ገብርኤል አብ ቢወልድ ቢያሠርፅ እንጂ የማይወለድ የማይሠርፅ መሆኑን ዐውቀን | ኦርቶዶክሳዊ አእምሮ

#የሚያዝያ #ድርሳነ #ገብርኤል

አብ ቢወልድ ቢያሠርፅ እንጂ የማይወለድ የማይሠርፅ መሆኑን ዐውቀን ወልድ ቢወለድ እንጂ የማይወልድ የማያሠርፅ መሆኑን ተረድተን መንፈስ ቅዱስም ቢሠርፅ እንጂ የማይወልድ የማያሠርፅ መሆኑን ተገንዝበን የጌቶች ጌታ የነገሥታት ንጉሥ መላእክት የሚያመሰግኑት ስልጣናት ሁሉ የሚገዙለት የቅዱሳንን አማላጅነት ተቀብሎ የልመናቸውን ዋጋ የሚሰጥ አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም በማመን #በሚያዝያ_19 #ቀን #የሚጸለይ የሚነበብ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም #የቅዱስ #ገብርኤል #ድርሳን #ይህ #ነው።

ረድኤቱ ከሁላችን ጋር ለዘለዓለሙ ይኑር አሜን።

ብርሃናዊው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል የጌታን ትንሣኤ ለቅዱሳት አንስት ያበሠራቸው እሱ ነው። አራቱም ወንጌላውያን እንደ ጻፉት ከሳምንቱ በመጀመሪያይቱ ቀን እሑድ ማለዳ በጌታ ህማምና ሞት ልባቸው በሀዘን የጠቆረ እመቤታችን ድንግል ማርያም፣ ማርያም መቅደላዊት እና ሌሎችም ሴቶች መቃብሩን ሊጎበኙ ሥጋውንም ሽቱ ሊቀቡ መጡ።

ያን ጊዜ ብርሃናዊው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል እንደ በረዶ ነጭ የሆነ ልብስ ለብሶ በመቃብሩ አጠገብ ተቀምጦ ታያቸው፤ እነርሱም ባዩት ጊዜ እጅግ ፈሩ። ይህ ቅዱስ መልአክ ፍርሃትን አርቆ ደስታን የሚያጎናጽፍ መልአክ ነውና፥ እነዚህን ቅዱሳት አንስትና እመቤታችንን “እናንተስ አይዟችሁ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ አውቃለሁና እነሆ ተነሥቷል ለደቀ መዛሙርቱ ሂዳችሁ ንገሩ” ብሎ ነገራቸው።

ይህን የደስታ ቃል በሰሙ ጊዜ በፍጹም ደስታ በፍጥነት ሄደው ለደቀ መዛሙርቱ ነገሩአቸው። (ማቴ. 28፥1-8፣ ማር. 16፥1-8፣ ሉቃ. 24፥1-5፣ ዮሐ. 20፥1-18) እንግዲህ ይህ ቅዱስ መልአክ ሀዘንና መከራ የመላውን ልቡና በደስታ የሚመላ በጭንቀትና በፍርሃት ላሉት ሰላምን መረጋጋትን የሚሰጥ የሰላምን የደስታን ዜና ሁልጊዜ ወደሰዎች ይዞ የሚገሰግስ ስለሆነ በጸሎቱ ለተማጸንን በአማላጅነቱ ለተማመን ለፍጹም ሃዘናችን ደስታን ለፍርሃታችን ሰላምን ይስጠን አሜን።

የምሥጢረ ትንሣኤው መልእክተኛ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር በወደደውና በመረጠው በዚህ በመላእክት አለቃ በቅዱስ ገብርኤል ልመና ለኛም ይህን የመሰለ ደስታንና የምስጋና በረከት ለማግኘት ያብቃን።

ጸሎቱ በረከቱ ከሁላችን ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን፤ አሜን።

ምንጭ፦
ትንሿ ድርሳነ ገብርኤል እና መልክአ ገብርኤል በመጋቤ ብሉይ ያሬድ ካሣ፣ 1999ዓ.ም፣ ገጽ 26 – 28


https://t.me/OrthodoxAmero
https://t.me/OrthodoxAmero

Facebook Link   follow ያድርጉ
https://www.facebook.com/deaconezemarefitsume.kebede