2023-02-24 06:00:52
አምነንበታል!
ስለጌታ ኢየሱስ አዳኝነት መመስከር ካባድ ነውን?
ስናነብ ካገኘናቸው
እኔ ለሲዖል ያለኝን መረዳት የሚገልጽልኝ፦ ሰይጣን ከሰማይ አምጾ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ ዳግም ጌታ ኢየሱስ እስኪመጣ ለሰራው ጥፋት፣ ክፋት፣ አመጽ (የሰይጣንን ወንጀል መጠን አስቡት) ይገባዋል የተባለ ስፍራ ነው።በእርግጥ ተመጣጣኝ ቅጣት ነው። ትክክለኛ ፍርድና ዋጋ!
ሲዖል ለሰው ዘር የተዘጋጀ ስፍራ አይደለም!
"ለሰይጣንና ለመላአክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ" ማቴ 25፡41
ጌታ ኢየሱስ የሰማይና የምድር ፈጣሪ የጌቶች ጌታ የነገሥታት ንጉስ ኃያል አምላክ ዙፋኑን ክብሩን ትቶ ሰው ሆኖ የባሪያን መልክ ይዞ ወደ ምድር መምጣቱ፣ ሰዎች ሲዖል እንዳይገቡ የከፈለው ዋጋና የተቀበለው መከራ የሲዖልን አደገኛነትና ዘግናኝነት በግልፅ የሚያሳይ ነው! "የሰው ልጅ የጠፋውን ለማዳን መጥቶአልና" ማቴ 18፡11
ሲዖል ቀላል ስፍራ ቢሆን ኖሮ ወይም ለሰውም የተገባ የተዘጋጀ ቢሆን ኖሮ አምላክ ሰው ባልሆነ በፈጠረው በሰው እጅ የርጉም ሞት ባልሞተ ነበር!
ለማንም ሰው ሲዖል አይገባም።
ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስ ለሰው ዘር ሁሉ መዳን የኃጢአትን ዋጋ ከፍሎአል፤ በቂና ብቁ ሥራ ሠርቷል!
የሰዎች መዳን ወይም አለመዳን ከአማኞች (ከእኔ፣ ከአንተ፣ ከአንች) ምስክርነት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፦ "እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?" ሮሜ 10፡14
ያለ አንተ ምስክርነት እንዴት ይሰማሉ? የእኛ ዝምታ በሰዎች ላይ የሲዖል ፍርድ መፍቀድ ነው።
ወንጌልን መናገር ለአማኞች የተተው ድርሻ ነው።
ወንጌል መናገር የመላእክት ተግባር አይደለም። መላእክት የራሳቸው የሥራ ድርሻ አላቸው። በእርግጥ በዚህ ተልእኮ ውስጥ እንደ ጌታ ፈቃድ ያግዙናል። ነገር ግን አማኞች በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ የሥራ ድርሻ ይኖረን ዘንድ ቀጥታ ለእኛ የተመደበ ሥራ ነው።
ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ሲዖል የተዘጋጀው ለሰይጣን ከሆነና ለማሰብ እንኳን የሚከብድ ስፍራ ከሆነ፤ ጌታ ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ሁሉ የሚያድን ሙሉ ሥራ ከሠራና ከኃጢአተኛውም የጌታ ኢየሱስን አዳኝነት አምኖ ለመቀበል ወንጌልን መስማት ግድ ከሆነ በጨለማ ላሉ ወንጌል መናገር የእኛ አንገብጋቢ ተግባር ነው።
ወዳጆቼ እስቲ ቆም ብለን እናስብ ላልዳኑ ወገኖች
"ኢየሱስ ያድናል!" "ጌታ ኢየሱስ ይወድሃል!" "የኃጢአት እዳህን ኢየሱስ ከፍሎልሃል!" ብሎ መመስከር እስከዚህ በእርግጥ ካባድ ነውን??
የሰው ልጅ መክፈል የማይችለውን ከባድ ዋጋ ጌታ ኢየሱስ መስቀል ላይ ከፍሎል!
ከእኛ የሚጠበቀው ማድረግ የምንችለው ቀላል በጨለማ ላሉ ወንጌልን ማወጅ ነው!
የተደረገልንን መመስከር ማድረግ የማንችለው ካባድ ነውን?
የቀመስነውን ፍቅር መመስከር ያሳፍራልን?
ታሪካችንን የለወጠ ከጨለማ ያወጣን ጌታ መልካምነት ዝም ያሰኛልን?
በጌታ በኢየሱስ ስም አዚምና ድንዛዜ ከላያችሁ ይነሳ! አሁን በያለንበት "እብድ ብሆን ለክርስቶስ ነው!" የሚያስብል ዝም የማያሰኝ ታላቅ እሳት ያግኛችሁ!
ወንጌል እንዳንመሰከር የሚያደርጉ እንቅፋቶች፦
1. የተደረገልንና ያገኘነውን የዘላለም ሕይወት ዋጋ አለመረዳት
2. መንፈሳዊ አይን አለመከፈት (የሲዖልንና የመንግሥተ ሰማያትን ልዩነት አለመረዳት)
3. በውስጣችን ላለው ለመንፈስ ቅዱስ ኃይል እውቅና አለመስጠት (የባዶነት ስሜት) በእውነተኛ አማኞች ሁሉ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ አለ።
4. ክርስቶስ በጨለማ ላሉ ያለውን ርህራሔ መጠን አለመረዳት
5. ለሰዎች መዳን ሸክም ማጣት
6. ራስ ወዳድነት ለምድራዊዉ (ለራሳችን) ጉዳይ ብቻ ትኩረት መስጠት
7. ወንጌል መመስከርን ብዙ እውቀት እንደሚጠይቅ ማሰብ (በየትኛውም እምነትና እውቀት ደረጃ ያለ አማኝ መናገር ይችላል። ሳምራዊቷን ሴት ማሰብ በቂ ነው ዮሐ 4፡7)
8. ዛሬም ወንጌል ያለውን መለኮታዊ የመሥራት (የመለወጥ) ኃይል አለመረዳት
9. በእኛ ምስክርነት (ንግግር) ውስጥ ያለውን ጉልበት አለመረዳት (የእኛ ምስክርነት እምነት የመፍጠር ኃይል አለማስተዋል)
10. በጨለማ ያሉ ሀብታም ይሁን ድሃ እንዴት ያለ
ተስፋ ቢስ ሕይወት ውስጥ እንዳሉ አለመረዳት
11. ሰይጣን በምን ያህል ትጋትና ቁጣ እየሰራ እንዳለ አለመረዳት
12. ሰዎች ድካማቸውን ብቻ ማየት ፀጋውን አለማሰብ (ከድካም ስወጣ ስለወጥ እመሰክራለሁ አትበል ስትመሰክር ከድካም ትወጣለህ)
13. የሰዎች አመለካከት ይለውጥብኛል ብሎ መፍራት (ይሉኝታ)
14. ቤተክርስቲያን ለምስክርነት ትኩረት ሰጥታ አለማስተማሪና አለመሥራት (ምሳሌ የሚሆኑ የሚያበረታቱ አማኞች በዙሪያችን ማነስ)
15. አሁን በሚታዩ ሁኔታዎች ተስፋ መቁረጥና ሕይወቴ ይመስክር ብሎ ማሰብ (መልካም ሕይወት መልካም ነው! ነገር ግን በአንደበታችን መመስከር ግድ ነው። ጌታ የሌላቸውም መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው ብዙ ሰዎች እንዳሉ ማስታወስ)
16. መመስከር ለሚገባን በጨለማ ላሉ ሰዎች (ሐይማኖት ተቋማት) እንደማይቀበሉ ያለን የተሳሳተ ግምት (ሐናንያ ስለሳውል (ስለሐዋርያው ጳውሎስ) የነበረው መረጃ ተቃዋሚ አሳዳጅ እንደ ነበረ ያለው መረጃው እንቅፋት ሆኖበት ነበር ሐዋ 9፡13)
17. ወንጌል በተለያየ መንገድ በበቂ ሁኔታ እየተሰበከ ነው (በሚዲያዎች በኮንፈረንሶች...) ወንጌል ያልሰማ የለም ብሎ ማሰብ (መቼም ለእኔ ከዚህ በላይ ስህተት ያለ አይመስለኝም።) በሀገራችን እንኳ ገና ከ80% በላይ ሕዝብ እውነተኛ ወንጌል ያስፈልገዋል። ሌላው ለአንድ ሰዉ እስከ መቼ ነው መመስከር ያለብን? መልሱ እስኪድን ድረስ ነው!
18. አለመመስከራችን በመጨረሻው ቀን ተጠያቅነት ጸጸትም እንዳለበት መዘንጋት ...
ከዚህ በላይ ብዙ ምክንያት መዘርዘር ይችላል ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ያለው አንድም ምክንያት የለም። ወንጌል ላለመስከራችን እግዚአብሔር ምክንያትን አይቀበልም።
ስለዚህ መፍትሔው አማኞች ሁላችንም በትጋት መመስከርና መመስከር ብቻ ነው!
ለመመስከር ከወሰንን፣ ራሳችንን ከሰጠን፣ የመዳን ዋጋ ከገባንና ፈቃደኞች ከሆንን አሁን በዚህ ሰዓት እንኳን በአጠገባችን ላሉ ሰዎች ወይም ወደሚገኙበት ወጣ ብለን ወይም ቴክኖሎጂውን (ሶሻል ሚዲያ) ተጠቅመን መመስከር እንችላለን።
ወንጌልን መመስከር ቀላል ነው! ይቻላል!
ምክንያቱም የተደረገልንን ያገኘነውን ሕይወት የቀመስነውን ፍቅር የምንወደውን ጌታ መመስከር ስለሆነ!
ማስታወስ ያለብን እኛ ለመመስከር ፈቃደኞች ከሆንን የምንናገረውን ቃልና ኃይል የሚሰጠን መንፈስ ቅዱስ ነው።
እስከዛሬ በሚገባ ባለመመስከራችን ሊድኑ የምችሉ (የሚገባቸው) ጌታን ሳይቀበሉ ስንቶች አልፈው ይሁን?
እርግጠኞች እንሁን በሚገባ ባለመመስከራችን ጌታን አሳዝነናል።
እግዚአብሔር ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ በተገኘንበት ሁሉ ሁልጊዜ መመስከራችንን ይፈልገዋል።
ላለፉት ብዙ ዓመታት ውስጤ ያለ ጥያቄ ነው ወንጌል መመስከር እስከዚህ ከባድ ነውን? ለምንድነው በሚገባ ወንጌል የማንመሰክረው??
መልሳችን (ምክንያታችን) ምን ይሁን ምን ተቀባይነት የለውም። መፍትሔዉ መመስከር መጀመር ብቻ ነው።
ጌታ ኢየሱስ እኛ መክፈል የማንችለውን የኃጢአት እዳ በመስቀል ላይ ከፍሎልናል። ነገር ግን ቀላል እኛ መክፈል የምንችለው ወንጌል የመናገር የፍቅር እዳ አለብን።
"ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ...
ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና" ማቴ 11፡29
716 viewsEjob @ JS, 03:00