2022-07-22 14:38:02
የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ወደ ትግራይ የሚጓጓዝ ስድስት ሺ ቶን ማዳበሪያ ለFAO ማስረከቡን አስታወቀ
የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በትግራይ ክልል ላሉ አርሶ አደሮች የሚላክ ከስድስት ሺ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ማስረከቡን አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ በብቸኝነት ማዳበሪያን ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባው ኮርፖሬሽኑ፣ ማዳበሪያውን ለፋኦ፣ ያስረከበው ከአንድ ወር በፊት የግብርና ሚኒስቴር፣ ፋኦ ከኮርፖሬሽኑ ማዳበሪያ እንዲገዛ የሰጠውን ፈቃድ ተከትሎ ነው፡፡
ኮርፖሬሽኑ በየዓመቱ ‹‹ከአቅም በላይ የሆነ አጥረት እንዳይፈጠር›› በሚል ከሚይዘው መጠባበቂያ ላይ በመቀነስ ይኼንን የማዳበሪያ መጠን ለፋኦ ማስረከቡን የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማሪያም ተናግረዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ለፋኦ ካስረከበው የአፈር ማዳበሪያ ግማሽ ያህሉ ኤንፒኤስ (NPS) ማዳበሪያ ሲሆን ቀሪው ዩሪያ ነው፡፡ ፋኦ ኤንፒኤስ ማዳበሪያን ከኮርፖሬሽኑ ወስዶ መጨረሱንና ዩሪያ ማዳበሪያን እያጓጓዘ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡
ፋኦ ወደ ትግራይ የሚያጓጉዘውን ተጨማሪ ስድስት ሺ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ለመረከብ፣ ጥያቄ ማቅረቡን የተናገሩት አቶ ክፍሌ፣ ድርጅቱ ተጨማሪውን ለመግዛት አስፈላጊ ሒደቶችን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንደሚያስረዱት ኮርፖሬሽኑ አሁን ያስረከበውንም ሆነ በቀጣይ ለድርጅቱ የሚሸጠውን የማዳበሪያ ሽያጭ ክፍያ ተረክቦ የሸጠውን ያህል ማዳበሪያ ወደ መጠባበቂያው ይተካል፡፡ የመጀመሪያውን ስድስት ሺ ቶን ሽያጭ ክፍያ ለመቀበል በሒደት ላይ ሲሆን፣ ፋኦ ሁለተኛውን ስድስት ሺ ቶን የአፈር ማዳበሪያ እንደሚገዛ የመጨረሻ ማረጋገጫ ሲሰጥ ለመተኪያው የግዢ ሒደት እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡
ለመተኪያ የሚሆነው ማዳበሪያ ግዢ የሚፈጸመው ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መሆኑንና በአምስት ቀናት የመርከብ ጉዞ ጅቡቲ ወደብ መድረስ እንደሚችል አቶ ክፍሌ ተናግረዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ፣ የመጀመሪያ ዙር የሆነውን 262 ቶን የአፈር ማዳበሪያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር ወደ ትግራይ ክልል ማስገባቱን አስታውቋል፡፡ ፋኦ በመግለጫው በመጀመሪያው ዙር ወደ ትግራይ ክልል ያስገባው ማዳበሪያ፣ በክልሉ ያለውን የምግብ ዋስትና ዕጦት አደጋ ለመግታት ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ማግኘት የቻለው 19,300 ቶን ማዳበሪያ አካል መሆኑን ገልጿል፡፡
በመጪዎቹ ሳምንታት ከአጋር አካላት ጋር በመሆን 60,000 ቶን ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ማቀዱን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡ ድርጅቱ በክልሉ ያለውን የማዳበሪያ አቅርቦትና ፍላጎት ለማሟላት የ53 ሚሊዮን ዶላር ጉድለት እንዳለበት አስታውቋል፡፡
[ዘገባው የ‹‹ሪፖርተር›› ጋዜጣ ነው]
467 views11:38