2023-04-08 15:40:54
የበድር ዘመቻ እና የጀነት ናፍቆት
¨¨¨¨¨¨¨¨¨¨¨¨¨¨¨¨¨¨¨¨¨¨¨¨¨¨
ረመዳን 17 የበድር ድል ቀን ነው፡፡ ኢስላም በበደል ላይ ያነሳው የመጀመሪያው #ጦርነት የሚታሰብበት ዕለት ነው፡፡ የዘመቻውን መዋዕል ብዙዎች በተለያየ አጋጣሚ አንስተውታል፡፡ እዚያ ውስጥ መግባት አልሻም፡፡ ነገርግን ያንን ገድል የሰራውን ዋናውን ስሜት መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡ ከበድር ድል በስተጀርባ የነበረው ቀስቃሽ ኃይል የጀነት ናፍቆት ነበር!
፡
በጦር አውድማው ላይ የአላህ መልክተኛ (ﷺ) ሁሉም እንዲሰማቸው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፡- ‹‹ነፍሴ በእጁ በሆነው #ጌታ እምላለሁ ዛሬ ቀን በትእግስት፣ ምንዳውን ከአላህ ከጅሎ፣ ፊትለፊት ተጋፍጦ፣ ሳይሸሽ የሚዋጋቸውን ሰው #አላህ ጀነት ያስገባዋል፡፡››
:
እውነቱን ልንገራችሁ ብዙዎቻችን ጀነት ስለሚያስገቡ በርካታ ተግባራት በተደጋጋሚ እንሰማለን፡፡ ነገርግን ምን ያህላችን በዚህ ቃል ኪዳን ቀልባችን ተነክቶ ያለንን ሁሉ ለመሰዋት ተዘጋጅተናል?!
ሶሓባዎች ለጀነት የነበራቸው ናፍቆት ልዩ ነበር፡፡ ከጀነት ውጪ ልባቸውን ምንም ነገር ሊያነሳሳውና ጉልበታቸውን እና ጽናታቸውን ሊያበረታ አይችልም፡፡
ምክንያቱም ለዱንያ የተዋጋ ምናልባት አሁን ሲገደል ሁሉም ነገር ያበቃለታል፡፡ ለጀነት የተዋጋ ሰው ግን ለሞቱ ትርጉም የሰጠ ሰው ነው፡፡ እንደውም ሞት ለሱ ህይወት ነው፡፡ የሚናፍቃት #ጀነትን ለማግኘት ካገደው የዱንያ ህይወት የሚገላገልበት ምኞቱን የሚያሰምርበት እድሉ ነው፡፡ ሸሂድ ያለ ሒሳብ ጀነት ይገባል፡፡
:
ስለዚህ ከውጊያው በፊት የሶሐቦቹ ስሜት ይህ ነበር፡- ‹‹ከሞትን ጀነት እንገባለን፡፡ ስለዚህ ሞትን ናፋቂዎች ነን!››
:
ሰዎች ሞትን ይጠላሉ፤ ይፈራሉ፡፡ የጀነት ትርጉም ለገባው ደግሞ የምኞቱ ጣሪያ ሞቱ ነው፡፡ የአላህ መልክተኛ (ﷺ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ጀነት ውስጥ አላህ በመንገዱ ለሚታገሉ ሰዎች ያዘጋጀው አንድ ደረጃ አለ፡፡ በርሱና ከርሱ ውጪ ባለው ደረጃ መሀል ያለው ልዩነት በሰማይና በምድር መካከል ያለውን ርቀት ያክላል፡፡›› ቡኻሪ ዘግበውታል፡፡
:
ከአነስ (ረ.ዐ.) እንደተዘገበው የአላህ መልክተኛ (ﷺ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹በጧት ወይም ከከሰዓት በኋላ በአላህ መንገድ ለትግል መውጣት ዱንያና በውስጧ ካለው ይበልጣል፡፡ በጀነት ውስጥ ደጋን [ቀስት ማስወንጨፊያ] የሚያክል ስፍራ ዱንያና በውስጧ ካለው ሁሉ ይበልጣል፡፡ ከጀነት ሴቶች አንዷ ወደ ምድር ብቅ ብትል ዱንያን በሙሉ በብርሃን ታፈካት ነበር፡፡ በሰማይና በምድር መሀል ያለውን ሁሉ በመልካም መዓዛዋ ታውደው ነበር፡፡ በጭንቅላቷ ላይ ያለው ሻሽ ዱንያና በውስጧ ካለው ሁሉ ይበልጣል፡፡››
:
በእውነተኛው ነቢይ ልሳን በሚነገረው በዚህ እውነተኛ ቃል እርግጠኛ የሆነ ሰው ይችን ሀገር መናፈቁ አይቀሬ ነው! ስለዚህ በበድር ያሸነፈው ኃይል ልክ እኛ ህይወትን እንደምንወደው ሞትን የሚወድ ኃይል ነው፡፡ ከሁለት መልካም ውጤቶች አንዱን እንደማያጣ ተማምኖ ሜዳ ላይ የተሰለፈ ሰራዊት ነው፡፡ ድል ወይም ሞት፡፡ ድል ወይም ጀነት!
:
የአላህ መልክተኛ (ﷺ) ስለ 'ገለባው' ትውልድ ተናግረዋል፡፡ የዚያን ገለባ ትውልድ ማንነትም ‹‹ድክመት›› ያለበት ትውልድ ብለው ገልጸውታል፡፡ ‹‹ድክመቱ ምንድን ነው?›› ሲባሉም፡- ‹‹ዱንያን ማፍቀርና ሞትን መጥላት!›› በማለት መልሰዋል፡፡
የጀነት ፍቅር የሙስሊሞች የድል ቁልፍ ነው፡፡ ጀነትን ሲናፍቁ ድልም ጀነትም ያገኛሉ፡፡ የጀነት ናፍቆት ከቀልባቸው ሲጠፋ ድልንም ሆነ ጀነትን ያጣሉ፡፡
:
የድል መጀመሪያው ፍርሀትን ድል መንሳት ነው፡፡ ስለዚህ ሞትን የሚመኝ፣ ሞትን ፈልጎ የወጣ፣ ለሞት የተዘጋጀ፣ ላይመለስ ኑዛዜውን ጽፎ ከቤቱ የወጣ፣ እንደውም አለመሞትን የሚፈራ ሰው ምንን ሊፈራ ይችላል?! እንዲያፈገፍግ የሚያደርገው ኃይልስ ይኖራል ወይ?!
:
ጉዳዩ የእምነትና የፍላጎት ነው፡፡ የኒያ ጉዳይ ነው፡፡ የህልም ጉዳይ ነው፡፡ የናፍቆት ጉዳይ ነው፡፡
አንተስ ጀነትን ትፈልጋለህ?! ጀነትን ትናፍቃለህ?!…
ጀነትን የምር ከፈለግከው በሰላሙ ጊዜም አታጣውም፡፡ የአላህ መልክተኛ (ﷺ) እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ሸሂድ መሆንን በእውነት አላህን የለመነ ሰው በፍራሹ ላይ እንዳለ ቢሞትም አላህ የሸሂዶችን ደረጃ ያደርሰዋል፡፡››
ጉዳዩ የኒያ ነው! ከአላህ ጋር የተጋባኸው እውነተኛ ቃልኪዳን!
:
ወደ ኋላ እንመለስ!
የጀነት ፍቅር #በድር ላይ ምን ሰራ?!
አንድ ክስተት ብቻ ላንሳ።
ዑመይር ኢብኑል-ሑማም ከአላህ መልክተኛ [ﷺ] አጠገብ ነበር፡፡ የአላህ መልክተኛ (ﷺ) ‹‹ስፋቷ ሰማያትና ምድርን ለምታህለዋ ጀነት ተነሱ!›› አሉ፡፡
ይህ ቃል በቁርኣን ውስጥ ያለ ቃል ነው፡፡ ደጋግመን ቀርተነዋል፡፡ ደጋግመን ሰምተነዋል፡፡ ነገርግን ስንት ጊዜ ሰርተንበታል?! ስንት ጊዜ ጀነትን ናፍቀንበታል?! ምንም ወይም ጥቂት!!
ዘር መሬት መርጦ እንደሚያፈራው መልእክቱም ልብን መርጦ ያብባል፡፡ ዑመይር ኢብኑል-ሑማም ይህንን ቃል ሰማ፡፡ በልቡ ነው የሰማው፡፡ ገረመው፡፡ ‹‹ስፋቷ ሰማያትና ምድርን የሚያህል!›› አለ፡፡
የኮንዶሚኒየም ቤት ባለቤት መሆን ምን ያህል እንደሚያለፋ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ዘልዓለማችንን ደክመንም ላይሳካ ከመቻሉ ጋር ማለት ነው!
ጀነት ግን የአላህ ቃል ነው፡፡ አምኖ ኒያውንም ለአላህ አጥርቶ ሳይሸሽ የታገለ ሰው ጀነት ይገባል!
ዑመይር በአግራሞት ጠየቀ፡- ‹‹ስፋቷ ሰማያትና ምድርን ያህላል!?››
‹‹አዎን!›› አሉት፤ በአጭሩ፡፡ ማብራሪያና ዝርዝር ውስጥ ሳይገቡ፡፡
ዑመይርስ? እሱም በእርግጠኝነት ንግግሩን ተቀብሏል፡፡ አልተከራከረም፤ አላንገራገረም፤ ማብራሪያ አልጠየቀም!
‹‹እሰይ እሰይ!›› አለ፤ በመደነቅ፡፡
‹‹እሰይ! እሰይ! ያልከው ለምንድን ነው? በንግግሬ ተጠራጥረህ ነው?›› አሉት፤ የአላህ መልክተኛ ﷺ፡፡
ዑመይር በፍጥነት እንዲህ አለ፡- ‹‹የአላህ መልክተኛ ሆይ በፍጹም! እሰይ ያልኩት የጀነት ሰው መሆንን ተመኝቼ ነው!›› አለ፡፡
እርሳቸውም ‹‹አንተ የጀነት ሰው ነህ!›› አሉት፡፡
ዑመይር የጀነት ሰው ነው! በዱንያ ውስጥ ህይወቱ በስጋው ላይ እያለም ይህንን ያውቃል! ጀነት ከመግባት ያገደው ደግሞ አለመሞት ነው!
ሱብሐነላህ!
ከዚህ በኋላ ግን ለአፍታም ቢሆን በምድር ላይ በህይወት መቆየት አልፈለገም፡፡ በውጊያው ላይ ብርታት ይሆነው ዘንድ እየተመገባቸው የነበሩ ጥቂት የተምር ፍሬዎች በእጁ ላይ ነበሩ፡፡ ለአፍታ አሰበ፡፡
ለምንድን ነው ይህንን ተምር በእጄ የያዝኩት!?
የጀነት ፍሬዎች የት ሄደው ነው ይህንን የምመገበው!?
የጀነት አዕዋፋት፤ የጀነት መጠጥ፤ የአላህ መልክተኛ ሐውድ የት ሄዶ!?…
…እያለ ማሰብ ጀመረ፡፡
በእጁ የነበሩትን ተምሮች ጣለና በወርቅ ቀለም መመዝገብ የሚገባው አስደናቂ ቃሉን ተናገረ፡— ‹‹እነዚህ የተምር ፍሬዎችን እስጨርስ በህይወት ከቆየሁ ረዥም ሕይወት ነው!›› አለ፡፡
ጀነትን ሲናፍቅ የተምር ፍሬዎችን ለመብላት መቆየት እንኳን ረዘመበት፡፡
ለህይወቱ ሳይሳሳ ጠላት መሀል ዘሎ ገባ!
1.2K views12:40