2023-04-16 22:24:52
ዘካተል‐ፊጥርን በውክልና
================
ዘካቱል‐ፊጥር ላይ ገዝቶ የማከፋፈል ሥራውን ለሌላ ሰው ማወከል ይፈቀዳል። በሻፊዒያ መዝሀብ ውስጥ ኺላፍ የለም።
ኢማም ነወዊይ "መጅሙዕ" ላይ እንዲህ ይላሉ: ‐
«ዘካ ዒባዳ ከመሆኑ ጋር ውክልና የተፈቀደበት ምክንያት የሰው እዳን ከመክፈል ጋር የሚያመሳስለው ነገር በመኖሩ ነው። በተጨማሪም የዘካ ገንዘቡ ከዘካ አውጪው በመራቁ እና መሰል ምክንያቶች በውክልና መስራት እጅግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱም ነው።»
የሻፊዒይ መዝሀብ ልሂቅ የሆኑት ሸይኽ ሰዒድ አል‐ጃቢሪይ እንዲህ ይላሉ: ‐ «ሰውየው በራሱ በቀጥታ ዘካውን መስጠት የተሻለ ነው። የዘካ በረከቱ ቤት ውስጥ ያለውን ሁሉ ያካልል ዘንድ ቤት ውስጥ ሰፍሮ መስጠቱ መልካም ነው። በዚህ ቤተሰቦቹ ስለ ዘካቱል ፊጥር ይማሩበታል። መጠኑን ለይተው ያውቃሉ።
በውክልና በመስጠት ግን በጊዜ ሂደት ከበርካታ ሰዎች አእምሮ ውስጥ የዘካ ግንዛቤ ሊጠፋ ይችላል። ዝርዝር ሑኔታዎቹን የማያውቅ ትውልድ ሊፈጠርም ይችላል።»
ኢማም ነወዊይ እንዲህ ይላሉ:‐ «ታላላቆቹ የሻፊዒይ ባልደረቦች እንዲህ ብለዋል: ‐ «በገዛ ራሱ ዘካቱል‐ፊጥሩን ማከፋፈል በውክልና ከማከፋፈል ይበልጣል። ይህ ልዩነት የሌለበት ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ዘካው በትክክል መከፋፈሉን ማረጋገጥ የሚችልበት ሁኔታ ይህ ነው። ወኪል ግን ሊከዳ (ሊያታልል) ይችላል የሚል ስጋት አለበት። በዚያ ላይ ከዘካ አውጪው ጫንቃ ላይ ዘካው አይነሳለትም። ምክንያቱም የወኪሉ እጅ እንደ ዘካ አውጪው እጅ የሚቆጠር ነው። ለድኾቹ ገንዘቡ እስካልደረሰ ድረስ የባለቤቱ ጫንቃም ከዘካ ግዳጅ አይፀዳም።»
ስለዚህ በዚህ መሰረት አንድ ሰው ገንዘቡን ለዘካ አሰባሳቢ ድርጅት መስጠቱ ብቻውን ጫንቃውን አያፀዳለትም። ወኪል ድርጅቱ ለሚገባቸው ሰዎች ማድረሱ የግድ ነው። በመሀል ገንዘቡን በግፍ ከበላው ወይም መሰጠት ካለበት ወቅት ካዘገየው፣ ለማይገባው ሰው ከሰጠው [ወዘተ] ወኪሉን በወንጀል ሊያስጠይቀው ከመቻሉ ጋር ዘካ አውጪውም ይህንን እስካወቀ ድረስ ሊያስጠይቀው ይችላል። በዚያ ላይ ለተገቢዎቹ ሰዎች እስካልደረሰ ድረስ የዘካ አውጪው ጫንቃም በምንም መልኩ ከተጠያቂነት አይድንም።
በመሆኑም ዘካቱል‐ፊጥራችሁን በተለያዩ አይነት ውክልናዎች የምታከፋፍሉ ሰዎች ዘካችሁ ከዒድ ሶላት በፊት ለተገቢዎቹ ሰዎች መድረሱን አጣሩ! በወኪላችሁ እጅ ላይ እንዳይከርምና ቀኑ እንዳያልፍባችሁ ተጠንቀቁ!
አላሁ አዕለም!
http://t.me/fiqshafiyamh
870 viewsedited 19:24