2023-04-14 16:20:13
ዘካቱል‐ፊጥር
=========
ለጾም ፍቺ የሚሰጥ ዘካ ስለሆነ ዘካቱል‐ፊጥር ይባላል። እንደሌሎች ዘካዎች በሀብት ላይ ሳይሆን በጾመኛ አካል ላይ የሚያርፍ ዘካ በመሆኑ ደግሞ ዘካቱል‐በደን ይባላል።
:
ከሂጅራ በኋላ በሁለተኛው ዓመት ላይ የተደነገገ የዘካ ዓይነት ነው። የረመዳን ጾም በተደነገገበት ዓመት ማለት ነው። ዘካቱል‐ፊጥር ግዴታ መሆኑ በበርካታ ሐዲሶች ተረጋግጧል።
ከአቡ ሰዒድ አል‐ኹድሪይ [ረዐ] እንደተዘገበው: ‐ «የአላህ መልክተኛ [ﷺ] በመካከላችን እያሉ ዘካቱል‐ፊጥርን እንሰጥ ነበር።» ብለዋል።» ሙስሊም ዘግበውታል።
ከኢብኑ ዐባስ [ረዐ] እንደተዘገበው "የአላህ መልክተኛ [ﷺ] ዘካቱል‐ፊጥርን ግዴታ አድርገው ደንግገውታል።" አቡዳዉድ እና ሌሎችም ዘግበውታል።
:
የድንጋጌ ጥበብ
==========
ዘካቱል‐ፊጥር የተደነገገው በጾም ላይ የተከሰቱ ጉድለቶችን ለመጠገን እና በዒድ ቀን ድሆችን ከልመና ለመጠበቅ ነው። የአላህ መልክተኛ [ﷺ] ዘካቱል‐ፊጥር የተደነገገበትን ምክንያት ሲገልፁ እንዲህ ብለዋል: ‐ "ለጾመኛ ንፅህና ለምስኪን ምግብ እንዲሆን የተደነገገ ነው።" ኢብኑ ዐባስ (ረዐ) ዘግበውታል።
በሌላ ሐዲስ ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል: ‐ "[ድኾቹን] በዚያን እለት ለልመና እንዳይዞሩ አብቃቋቸው።"
ዘካቱል‐ፊጥር በሶላት ውስጥ ለሚከሰቱ አንዳንድ ስህተቶች እንደተደነገገው ሰጅደቱ‐ሰህዉ (የመርሳት ሱጁድ) የሚታይ ነው። ሰጅደቱ ሰህው ሶላትን እንደሚጠግነው ዘካቱል‐ፊጥርም ጾምን ይጠግናል።
ዘካቱል‐ፊጥር በማህበረሰቡ መሀል የመተባበርና የመረዳዳት መንፈስን ያሳድጋል። መተዛዘን እንዲሰፍን፣ የሀዘን እና የደስታ ስሜትን የሚጋራ ህዝብ ለመፍጠርና የማህበረሰብ ትስስርን ለማጥበቅ ያግዛል።
:
ግዴታ የሚሆነው በማን ላይ ነው?
=====================
ዘካቱል‐ፊጥር ማውጣት የእያንዳንዱ ሙስሊም ግዴታ ነው። ወንድን ከሴት፣ ህፃንን ከዐዋቂ፣ እብድን ከጤነኛ አይለይም። ዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር [ረዐ] እንደዘገቡት: ‐ "የአላህ መልክተኛ [ﷺ] የረመዳን መግደፊያ ዘካን ግዴታ አድርገዋል። መጠኑ አንድ ቁና ተምር ወይም አንድ ቁና ገብስ ነው። ባሪያም ሆነ ጨዋ፣ ወንድም ሆነ ሴት፣ ህፃንም ሆነ ዐዋቂ በሙስሊሞች ላይ ሁሉ ግዴታ ተደርጓል።" ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።
ኢብኑል‐ሙንዚር እንዲህ ብለዋል: ‐ "ዘካቱል‐ፊጥር ግዴታ መሆኑ ላይ የምናውቃቸው ዐሊሞች በሙሉ ተስማምተዋል።"
:
የግዳጅ መስፈርቶች
============
ዘካቱል‐ፊጥር ግዴታ ይሆን ዘንድ መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች ተከታዮቹ ናቸው: ‐
❶ ሙስሊም መሆን: ‐ ሙስሊም ያልሆነ ሰው ዘካቱል‐ፊጥር ቢያወጣ ተቀባይነት የለውም። አላህ እንዲህ ብሏል: ‐ «ልግስናዎቻቸውን ከነሱ ተቀባይ የሚያገኙ ከመኾን እነሱ በአላህና በመልክተኛው የካዱ… መኾናቸው እንጂ ሌላ አልከለከላቸውም፡፡»
❷ ችሎታ: ‐ በዒድ ሌሊትና በቀኑ ላይ ከራሱና ከቤተሰቡ ቀለብ እና መሰረታዊ ወጪ የተረፈ ገንዘብ መኖር።
:
ሰውየው ከራሱ በተጨማሪ ወጪያቸውን ሸፍኖ ማኖር ግዴታ የሚሆንበትን ሰዎች ዘካ መስጠትም ግዴታ አለበት። የህፃናት ልጆቹን፣ የሚስቱን እና [በርሱ ስር የሚተዳደሩ] ወላጆቹን ማለት ነው።
:
ኢብኑ ዑመር [ረዐ] በዘገቡት ሐዲሰ የአላህ ነቢይ [ﷺ] እንዲህ ብለዋል: ‐ «ለምትቀልቧቸው ሰዎችም ዘካቱል‐ፊጥር አውጡላቸው።» ዳረቁጥኒ ዘግበውታል።
:
አንዲት ሴት ባሏ ዐቅም ከሌለው ዘካቱል‐ፊጥር ማውጣት በርሷ ላይ ግዴታ በመሆኑ ላይ የዐሊሞች ልዩነት አለ። ዘካዋን በራሷ መክፈል ግዴታ ይሆንባታል የሚለው ሃሳብ ግን የአብዝሃኞቹ ዐሊሞች ነው።
ሰውየው በዕዳ የተያዘ ሰው መሆኑ ዘካቱል‐ፊጥርን ለመተው ምክንያት አይሆንም።
:
ግዴታ የሚሆንበት ጊዜ
==============
ዘካው ግዴታ የሚሆንበት ጊዜ የሚጀምረው በዒድ ዋዜማ ፀሀይ ከመጥለቋ አንስቶ ነው። ምክንያቱም ዘካቱል‐ፊጥር የተደነገገበት ምክንያት ጾም ነበር። እርሱ ደግሞ ፀሀይ በመጥለቋ ምክንያት አብቅቷል። ይህ የኢማም ሻፊዒይና የኢማም አሕመድ ሃሳብ ነው።
በዚህ መሰረት የዒድ ሌሊት ፀሀይ በምትጠልቅበት ሰዓት ዘካቱል‐ፊጥር ግዴታ ከሚሆንባቸው ሰዎች መካከል ሆኖ የተገኘ ዘካውን የመስጠት ግዴታ ይኖርበታል። ፀሀይ ከጠለቀች በኋላ ወዲያው ቢሞትም ግዴታው እንዳለ ነው። በተቃራኒው ፀሀይ ከመጥለቋ ከደቂቃዎች በፊት የሞተ ሰው ዘካ የለበትም።
:
አቡ ሐኒፋ እና ማሊክ በበኩላቸው ግዳጁ የሚጀምረው ንጋት ከቀደደ አንስቶ ነው ባይ ናቸው። ምክንያቱም ዘካቱል‐ፊጥር የተደነገገበት ምክንያት ዒዱ ነው። ስለዚህ እንደማናቸውም የዒድ ቀን ድንጋጌዎች፣ እንደ ኡድሒያ፣ እንደ ጁሙዐ ሶላት ድንጋጌዎች… ከእለቱ ቀድሞ ግዴታ ይሆንም።…
:
የሚሰጥበት ጊዜ
===========
ዘካውን የዒድ ሶላት ከመሰገዱ አስቀድሞ ማውጣት ይወደዳል። ሻፊዒዮች ዘንድ በዒዱ ቀን ፀሀይ እስከምትጠልቅ ድረስ መስጠት ግን ይፈቀዳል። አብዝሀኞቹ ዐሊሞች ደግሞ ከሶላት በኋላ ማውጣት ይጠላል ብለዋል። አንዳንድ ዐሊሞች ከሶላት በኋላ አዘግይቶ መስጠት ሐራም ነው ይላሉ። እለቱን ማሳለፍ ግን ያለ ልዩነት ሐራም ነው። ነገርግን ቀኑ ቢያልፍም ዘካው ከሰውየው ጫንቃ ላይ አይነሳም። ጫንቃውን ከድሆች ሐቅ ለማፅዳት መቼም ቢሆን ዘካውን መክፈል አለበት። ከዚያም ማዘግየቱ የአላህ ሐቅን መጣስ በመሆኑ አላህን ምህረት መለመን አለበት።
:
አቡ ሰዒድ አል‐ኹድሪ [ረዐ] እንዲህ ብለዋል: ‐ "በአላህ መልክተኛ [ﷺ] ዘመን በዒዱል‐ፊጥር ቀን አንድ ቁና እህል እንሰጥ ነበር።"
ከኢብኑ ዑመር [ረዐ] እንደተዘገበው የአላህ መልክተኛ [ﷺ]: ‐ "ዘካቱል‐ፊጥር ሰዎች ለሶላት ከመውጣታቸው አስቀድሞ እንዲሰጥ አዘዋል።"
የዘካው ዓላማ ድሆች ከሀብታም ጎረቤቶቻቸው ጋር የዒዱን ቀን በደስታ እንዲያሳልፉ ከመሆኑ አንፃር በጠዋት ከሶላት በፊት መስጠቱ ተገቢ ነው።
:
ዘካውን ሳይሰጥ የዘገየው በአሳማኝ ምክንያት ከሆነ ግን ችግር የለውም። ለምሳሌ: ‐ ሰውየው የሚሰጠው ነገር በሌላ ቦታ ላይ እያለ የዘካው ጊዜ ከደረሰበት፣ ዘካ የሚቀበል ተገቢ አካል ሳያገኝ በመቅረቱ ካዘገየው፣ የዒዱ አዋጅ በድንገት ተነግሮ ከሶላት በፊት ዘካ ለማውጣት የሚመች ጊዜ በማጣቱ፣ ሌላ ሰው ዘካውን ያወጣልኛል ብሎ ተዘናግቶ ባለበት ሰውየው ከረሳው ወ.ዘ.ተ. ዘካውን ያለ ምንም ችግር ከዒድ በኋላም መስጠት ይችላል። ምክንያቱም በነዚህ ሁኔታዎች በሙሉ ሰውየው ምክንያታዊ ነው።
:
ማስቀደም
======
ሻፊዒዮቹ ዘንድ ከረመዳን አንደኛው ቀን ጀምሮ ግዴታ ከመሆኑ አስቀድሞ ዘካውን መስጠት ይፈቀዳል። ምክንያቱም ዘካው በሁለት ምክንያቶች የተደነገገ ዘካ ነው። አንደኛው ጾም ሲሆን ሌለኛው ፊጥር ነው። ረመዳን አንድ ሲል አንዱ ምክንያት ተገኝቷል። ስለዚህ ዘካውን ከረመዳን አንድ ጀምሮ መስጠት ይቻላል።
ኢማም ማሊክ እና አሕመድ ዘንድ ደግሞ ከሁለት ቀን አስቀድሞ መስጠት ይቻላል። አንዳንዶቹ ሦስት ቀን ማስቀደም ይፈቀዳል ይላሉ። ሐንበሊዮች በከፊሉ ከረመዳን አጋማሽ ጀምሮ አስቀድሞ መስጠት ይቻላል ይላሉ። ነገሩ ሰፊ ነው። የፈለጉትን ዐሊም ሀሳብ ተንተርሶ መፈፀም ይቻላል።
824 views13:20