2023-03-30 05:04:50
የጾም ህግጋት
በተውፊቅ ባህሩ
(ክፍል ሃያ)
============
ቀዷ እያለበት የሞተ
============
ጾም እያለበት የሞተ ሰው የተለያዩ ሁኔታዎች አሉት: ‐
⚀ በአሳማኝ ሸሪዓዊ ምክንያት ጾም አፍርሰው ቀዷ ማውጣት የሚያስችል ምንም አይነት ክፍተት ሳያገኙ በዚያው የሞቱ ሰዎች ምንም ዓይነት ቀዷም ሆነ ቤዛ መክፈል አያስፈልጋቸውም።
⚁ በሸሪዓዊ ፍቃድ ሰበብ ኖሮት ረመዳንን ሳይጾም ቀርቶ ቀዷ ማውጣት እየቻለ ቀዷውን ሳያወጣ ቀርቶ በዚያው የሞተ ሰው፤
⚂ ያለ አሳማኝ ምክንያት ጾሙን ፈትቶ ኖሮ በማንኛውም መልኩ ‐ቀዷ ማውጣት ችሎ በዳተኝነትም ይሁን በአሳማኝ ምክንያት ቀዷ መክፈል ሳይችል ቀርቶ‐ በዚያው የሞተ ሰው።…
እነዚህ ሁለቱ ሰዎች ቀዷ ሳያወጡ መቅረታቸው ማካካሻ የሚፈልግ እንደ ክፍተት የሚታይ ተግባር ነው።
ስለዚህ ትተውት ካረፉት ንብረት ላይ ተቀንሶ ባለባቸው ቀን ልክ ቤዛ ይከፈልላቸዋል። ቤዛው ለየእለቱ አንድ እፍኝ ወይም አምስት መቶ ግራም እህል ነው።
ቲርሚዚይ በዘገቡት ሐዲስ የአላህ መልክተኛ [ﷺ] እንዲህ ብለዋል: ‐ «የወር ጾም እያለበት የሞተ ሰው ለእያንዳንዱ ቀን አንድ ምስኪን ያበሉለታል።» ቲርሚዚይ ሐዲሱን ዘግበውታል፤ በዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር (ረዲየላሁዐንሁ) ላይ የቆመ "መውቁፍ" ሐዲስ መሆኑ ተመራጭ ነው ብለዋል።
ኢማም አል‐ማወርዲይ በዚህ ጉዳይ ላይ የዐሊሞች ሙሉ ስምምነት እንዳለ ጠቅሰዋል።
ለድኾች የሚሰጠው እህል አብዝሃኛው የሀገሩ ሰው የሚመገበው የእህል ዓይነት መሆኑ ወሳኝ መስፈርት ነው።
በቀድሞው የኢማም ሻፊዒይ ሃሳብ መሰረት የሟቹ ቤተሰብ "ወልይ" በእህሉ ፈንታ መጾምም ይችላል። በእርግጥ በአዲሱ ሃሳባቸው ላይ ሻፊዒይ የሟችን ቀዷ በጾም መክፈል መፈቀዱን በተከታዩ ሐዲስ ሶሒሕ መሆን እና አለመሆን ላይ አንጠልጥለው ትተውታል። ሐዲሱ ቡኻሪና ሙስሊም የዘገቡት ነው። የአላህ መልክተኛ [ﷺ] እንዲህ ብለዋል: ‐
«ጾም እያለበት የሞተ ሰው ወልዩ ይጾምለታል።»
በእርግጥም ሐዲሱ ሶሒሕ ሆኖ በመገኘቱ የሻፊዒይ አዲሱ (አል‐ቀውሉል‐ጀዲድ) መሠረትም በጾም መክፈል ይቻላል ማለት እንችላለን።
ወልዩ የሟችን ቀዷ የመክፈል ግዴታ አለበት?
ይህ በሚከተለው አስተውሎት የሚቃኝ ነጥብ ነው: ‐
ሟች ትቶት ያለፈው ኃብት ካለ ወልዩ ከሁለቱ አማራጮች አንዱን የማድረግ ግዴታ አለበት: ‐ እህል ማብላት ወይም መጾም።
ሟቹ ትቶት ያለፈው ኃብት ከሌለው ግን ወልዩ ከሁለቱ ነገሮች አንዱን ማድረግ ይወደድለታል፤ መጾም ወይም ማብላት።
ይህ አማራጭ የተሰጠው ሟቹ ሙስሊም ሆኖ ከሞተ ብቻ ነው። ሟች ከኢስላም አፈንግጦ (ሙርተድ ሆኖ) ከሞተ ግን ወልዩ ቀዷውን የሚከፍልለት በማብላት ብቻ ነው። መጾም አይፈቀድም።
ይህ ኢማም ረምሊይ "ኒሃየቱል‐ሙሕታጅ" የተሰኘው መፅሐፋቸው ላይ የተናገሩት እና ኢብኑ ሐጀር "ቱሕፋ" ላይ ያመላከቱት ሃሳብ ነው።
የትኛው ወልይ?
ለሟች ቀዷ የሚከፍለው ወልይ ወራሽ ባይሆንም ሁሉም ዘመድ ነው። እዚህ ላይ ወልይ ሲባል በገንዘብ ጉዳዮች ላይ ወልይ ተብለው የሚጠሩት ሟች ገንዘቡን ማስተዳደር በማይችልባቸው ተጨባጮች ኃላፊነት የሚሰጣቸው አባት እና አያት ብቻ አይደሉም። በውርስ ስፍራ ላይ "ዐሶባ" ተብለው የሚጠሩት ሁሉም በጾታ ወንዶች የሆኑት ጠቅላይ ወራሾችም አይደሉም። በዚህ ቦታ ላይ ''ወልይዋ'' ሴትም ልትሆን ትችላለች።
ሙስሊም በዘገቡት ሐዲስ አንዲት ሴት የአላህን መልክተኛ [ﷺ] «እናቴ የስለት ጾም እያለባት ሞተች። እኔ ልጹምላት ወይ?» በማለት ጠየቀች። እርሳቸውም: ‐ «ለእናትሽ ፁሚላት።» በማለት መለሱ።
"አል‐መጅሙዕ" የተሰኘው መፅሐፋቸው ላይ ኢማም ነወዊይ እንዲህ ብለዋል: ‐ «ይህ ሐዲስ [ከላይ ባለፉት ሐዲሶች ውስጥ] ወልይ ሲባል የገንዘብም ሆነ የውርስ ወልይን ለማለት እንዳልሆነ ያረጋግጣሉ። ምክንያቱም ሴት የዐሶባም ሆነ የገንዘብ ወልይነት የላትም።»
«ሴትየዋ ወራሽ ትሁን ወይም አትሁን የአላህ መልክተኛ ማብራሪያ አለመጠየቃቸው ደግሞ ገየዳዩ አጠቃላይ እና ገደብ የለሽ መሆኑን ያስረዳል። ለሟች ጿሚ የሆነው ሰው ወራሽም ይሁን ሌላ ከግምት እንደማይገባ ያሳብቃል።» ይህ ኢማም ረምሊይ ያሉት ነው።
ወልዮች በጋራ ቢጾሙ
ሰላሳ የሟች ቤተሰቦች በጋራ በአንድ ቀን ቢጾሙ ይበቃቸዋል። ይህ "አል‐መጅሙዕ" የተሰኘው መፅሀፋቸው ላይ ኢማም ነወዊይ የፈተሹት ሀሳብ ነው። ከነወዊይ ውጪ ያሉ ሌሎች ዐሊሞች ደግሞ ሰውየው የእስልምና ሐጅ፣ የስለት ሐጅ እና የቀዷእ ሐጅ ቢኖርበት እና ሦስት ሰዎች ተቀጥረው በአንድ አመት የሐጅ ክንውን ውስጥ በአንድ ጊዜ ቀዷውን ቢከፍሉለት ከሚሰጠው ብይን ጋር አመሳስለውታል። ኢማም ኢብኑ ሐጀር፣ አል‐ኸጢብ እና አር‐ረምሊይ የደገፉት ሃሳብ ይኸው ነው።
ቀዷውን ባዳ መክፈል ይችላል?
በሁለት ሁኔታዎች ከሟች ጋር የስጋ ዝምድና የሌለው ባዳ ቐዷውን መክፈል ይችላል: ‐
⚀ ሟች ባዳ የሆነው እገሌ የተባለው ሰው እንዲጾምለት ከተናዘዘ፤
⚁ የአዕምሮ ጤና ያለው፣ ለአቅመ አዳም የደረሰ ወልይ ባዳው ቀዷውን እንዲከፍልለት ከፈቀደ።
ከሁለቱ ሁኔታዎች ውጪ በራስ አነሳሽነት ባዳ የሆነ ሰው ለሟች ቀዳ ሊከፍል አይችልም፤ አያብቃቃውም። ምክንያቱም ይህንን የሚፈቅድ የሐዲስ መረጃ አልመጣልንም።
ባዳ የሆነ ሰው ያለማንም ፍቃድ ለሟች ሐጅ ቢያደርግለት ይበቃዋል። ቀዷውም ይከፈልለታል። ስለዚህ የጾም ቀዷንም ባዳ ያለማንም ፍቃድ ቢጾም ያብቃቃል ልንል ስለሚቻል ጉዳዩ ጥናት የሚፈልግ አስቸጋሪ ነገር ነው በማለት ኢማም አል‐አስነዊይ ተናግረዋል። ይህን እንዴት ታዩታላችሁ? ሊባል ይችላል።
ነገርግን ግርታውን የሚያስወግድ መልስ አለን። ሐጅ በጥብቅ ሁኔታ ከገንዘብ ጋር ቁርኝት ያለው ዒባዳ ነው። ስለዚህ የገንዘብ እዳን ከመክፈል ጋር ተመሳስሎ እናገኘዋለን። የማንኛውንም ሰው የገንዘብ እዳ ያለማንም ፍቃድ መክፈል እንደሚቻል ደግሞ በልሂቃን ዘንድ የታመነ ነው። ጾም ግን ንፁህ ወይም የገንዘብ ንክኪ የሌለው አካላዊ ዒባዳ ነው። ስለዚህ «ጾምን ከሐጅ ጋር ማመሳሰል አይቻልም» ይሉናል፤ አል‐ኸጢብ አሽ‐ሺርቢኒይ [ረሒመሁላህ]።
https://t.me/fiqshafiyamh
1.2K views02:04