2023-04-06 14:46:33
ሶላቱት‐ተሳቢሕ
ሶላቱት‐ተስቢሕ ለብዙዎቻችን እንግዳ ይመስለኛል። እንግዳ የሆነው ከአላህ ጋር የሚያገናኙን የአምልኮ ተግባራትን በራቅንበት እና ለዒባዳ በሰጠነው አነስተኛ ትኩረት ልክ መሆኑ እርግጥ ነው። ለማንኛውም ጊዜው ረመዳን ከመሆኑ አንፃር ለአኺራችን ስንቅ ይሆነን ዘንድ በዚህ የሶላት ሁኔታ ዙርያ ጥቆማ መስጠት እሻለሁ፤ ተከታተሉኝ።
* * *
«ሶላቱት‐ተስቢሕ አቡዳዉድ፣ ኢብኑ ማጀህ፣ ኢብኑ ኹዘይማ፣ ጦበራኒይ እና ሌሎችም እጅግ በርካታ በሆኑ ዘገባዎች፣ ከብዙ ሶሓባዎች የተገኘ ሶላት ነው።» ይላሉ ኢማም አል‐ሓፊዝ ኢብኑ ሐጀር [ረሒመሁላህ]።
ከነዚህ ዘገባዎች ውስጥ ዒክሪማ ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስን [ረዲየላ ሁዐንሁ] ዋቢ በማድረግ የዘገቡት ተጠቃሽ ነው። የአላህ መልክተኛ [ﷺ] ለአጎታቸው ዐባስ ኢብኑ ዐብዱል‐ሙጦሊብ ተከታዩን ተናግረዋል ይሉናል:‐
«…በየእለቱ አንድ ጊዜ መስገድ ከቻልክ አድርገው። ይህንን ካልቻልክ በሳምንት አንድ ጊዜ ስገደው። ይህንን ካላደረግክ በአመት አንድ ጊዜ ስገድ። ይህንን ካላደረግከው በእድሜ ልክህ አንዴም ቢሆን ስገደው።»
ይህንን ሐዲስ በርካታ ዐሊሞች "ሶሒሕ" አድርገውታል። ኢማም ነወዊይ "አል‐አዝካር" በተሰኘው መፅሐፋቸው ላይ ጠቅሰውታል። አስከትለውም ቀጣዩን የኢማም ቲርሚዚ [ረሒመሁላህ] ቃል አስፍረዋል: ‐
«በሶላቱት‐ተሳቢሕ ዙርያ ከነቢዩ [ﷺ] በርካታ ሐዲሶች ተዘግበዋል። በርካታዎቹ "ሶሒሕ" አይደሉም። ዐብዱላህ ኢብኑ ሙባረክ እና ብዙዎቹ የዒልም ሰዎች ትሩፋት ያሏት ሶላት መሆኗን ያምናሉ።»
ከዚያም ቲርሚዚይ አቡራፊዕ የዘገቡትን የዐባስ ሐዲስ ጠቀሱና ሐዲሱን "ገሪብ" (በአንድ ዘጋቢ የተወራ) ብለውታል።
የቲርሚዚ የሐዲስ መድብልን ማብራሪያ (ሸርሕ) የሰሩት ኢማም አቡበክር ኢብኑል‐ዐረቢይ [ረሒመሁላህ] በበኩላቸው "አል‐አሕወዚይ ፊ ሸርሒት‐ቲርሚዚይ" ላይ ተከታዩን ይላሉ: ‐
«የአቡ ራፊዕ ሐዲስ ዶዒፍ ነው። ለሶሒሕነትም ሆነ ለሐሰንነት የሚያበቃ ጥንካሬ የለውም።»
አቡል‐ፈረጅ ኢብኑል‐ጀውዚይ የሶላቱት‐ተሳቢሕ ሐዲሶችን ከሰነዳቸው ጋር ሰብስበው ሲያበቁ ዶዒፍ ናቸው ብለዋል።
ኢብኑ ዓቢዲን እንዲህ ይላሉ: ‐ «የሶላቱት‐ተሳቢሕ ሐዲሶች ደረጃ "ሐሰን" ነው። ይኸውም እጅግ በርካታ የዘገባ መንገዶች ስላሉት ነው። ዶዒፍ ነው ያለ ተሳስቷል። በውስጡም የማያልቁ ምንዳዎችን ይዟል። በዚህ ምክንያት አረጋጋጭ (ሙሐቂቅ) የሆኑ ዐሊሞች እንዲህ ይላሉ: ‐ «ታላቅ ትሩፋቷን ሰምቶ የሚተዋት ሰው በዲን ላይ የሚሳነፍ ሰው ብቻ ነው።»
ኢማም ነወዊይ እንዲህ ብለዋል: ‐ «እንደ አል‐በገዊይ፣ አር‐ረወያኒይ እና ዐብዱላህ ኢብኑል‐ሙባረክ ያሉ እጅግ በርካታ ልሂቃን ሶላቷ ተወዳጅ መሆኗን ገልፀዋል። ሰውየው በተለያዩ ጊዜያት እንደ ለምድ ሊይዛት ይገባል። መዘናጋት የለበትም።»
አል‐ሓፊዝ አል‐ሙንዚሪይ እጅግ በርካታ ሐዲሶች ከጠቀሱ በኋላ ዘገባዎቹ አንዳንዶቹ ሶሒሕ እንደሆኑና የበርካታ ልሂቃን ልዩነት እንዳለባቸው ገልፀዋል።
* * *
ይህ ስለሶላቱት‐ተስቢሕ የተገኙ ዘገባዎችን በተመለከተ የልሂቃን ሃሳብ ምን እንደሚመስል በጥቅል ምልከታ ለመጠቆም ያክል ነው። ሐዲሶቹ በሶሒሕ እና በዶዒፍ መካከል የሚመላለሱ ዘገባዎች ናቸው። ነገርግን በማንኛውም መንገድ ሶላቱት‐ተሳቢሕ ተወዳጅ ሶላት መሆኗን የሚያግድ መረጃ የለም። ምክንያቱም በርካታ (ሁሉም ላለማለት ነው) ልሂቃን በመልካም ሥራዎች ትሪፋት ላይ የተነገሩ ሐዲሶች ዶዒፍ ቢሆን እንኳን እንደሚሰራባቸው ተስማምተዋል።
ሶላቱት‐ተሳቢሕ እንደማንኛውም ሶላት የሶላት ዓይነት ናት። ተጨማሪ ዚክሮችን ይዛለች እንጂ ከመደበኛ የሶላት አሰጋገድ ጋር የሚጋጭ ምንም ዓይነት ልዩነት የላትም። ተጨማሪ ተስቢሕ መኖሩ ከሌሎች ሶላቶች የተለየ ህልውና እንዲኖራት አያደርጋትም። በግብርም ከሌሎች ሶላቶች አይለያትም። በመሰረቱ ሶላት የተደነገገው በራሱ ተስቢሕን አካቶ እንዲይዝ ተደርጎ ነው። ተስቢሕ በጧትም ሆነ በማታ ያለ ምንም ገደብ የታዘዘ ተግባር ነው። ሶላትም ምርጡ የዒባዳ ዓይነት ነው። በዚያ ላይ በርካታ ዐሊሞች ተወዳጅነቱን ያፀደቁት እንደመሆኑ ሶላቱን መቃወም እና ማጣጣል ተቀባይነት የለውም።
የሶላቱት‐ተሳቢሕን ትሩፋት በተመለከተ በአቡዳዉድ፣ በ
ኢብኑ ማጀህ እና ኢብኑ ኹዘይማ ዘገባ የዐባስ [ረዲየላሁዐንሁ] ሐዲስ ላይ የሰፈረው እንዲህ ይላል: ‐
«አጎቴ ሆይ! ስጦታ አልሰጥህም!? [መልካም ነገርን] አልለግስህም?! ልዩ ነገርን አላድልህም?! ዐስር ዓይነት ወንጀሎችህን የሚያስምሩልህን ነገር አላስተምርህም?! አንተ የሰራህበት ከሆነ የመጀመሪያውን፣ የመጨረሻውን፣ ቀደምቱን፣ አዲሱን፣ በስህተት የፈፀምከውን፣ አውቀህ የሰራኸውን፣ ትንሹን፣ ትልቁን፣ ምስጢሩን፣ ይፋ የሆነውን ወንጀልህን ሁሉ አላህ ይምርሃል። [እነዚህ] ዐስር ነገሮች ናቸው። የማስተምርህ ስራ አራት ረከዐ እንድትሰግድ ነው።…»
በአቡዳዉድ እና በቲርሚዚይ ሌላ ዘገባ ደግሞ: ‐ «ኃጢኣትህ "ዓሊጅ" የሚሰኘው (አሸዋማ) ስፍራን አሸዋ የመሚያህል ቢሆን እንኳን አላህ ይምርሃል።» የሚል እናገኛለን።
በእርግጥበሶላቱት‐ተሳቢሕ የሚማሩት ወንጀሎች ቀላል ወንጀሎች (ሶጋኢር) ብቻ ናቸው። ከባባድ ወንጀሎች (ከባኢር) ምህረት ያገኝ ዘንድ ንፁህ ተውበት ማድረግ የግድ ነው። ልክ እንደዚሁ ማናቸውም ምህረት ይገኝባቸዋል በማለት የተዘገቡ ሶላቶች በሙሉ ተመሳሳይ ብይን አላቸው።
* * *
አ͟ሰ͟ጋ͟ገ͟ዱ͟
ሶላቱት‐ተሳቢሕ አራት ረከዐ ነው። በመጀመሪያው ረከዐ ላይ ፋቲሓ እና ሱራ መቅራት ነው። ቂርኣቱን ከጨረስክ በኋላ በቆምክበት አስራ አምስት ጊዜ «ሱብሓነላህ፣ ወል‐ሐምዱሊላህ፣ ወላኢላሀ ኢል‐ለላህ፣ ወል‐ላሁ አክበር» ትላለህ። ከዚያም ሩኩዕ ታደርጋለህ። ሩኩዕ ላይ ሆነህ ዐስር ጊዜ «ሱብሓነላህ፣ ወል‐ሐምዱሊላህ፣ ወላኢላሀ ኢል‐ለላህ፣ ወል‐ላሁ አክበር» ትላለህ። ከዚያም ቀና ትልና ዐስር ጊዜ እንደዚያው ትላለህ። ከዚያም ሱጁድ ታደርጋለህ። በሱጁድ ውስጥም ዐስር ገዜ እንደዚያው ትላለህ። ከዚያም ከሱጁድ ትነሳና በተቀመጥክበት ዐስር ጊዜ እንደዚያው ትላለህ። ከዚያም ደግመህ ሱጁድ ትወርድና እንደዚያው ትላለህ። ከዚያም ከሱጁድ ስትነሳ በምትቀመጣት ጊዜ (ጀልሰቱል‐ኢስቲራሓ) ዐስር ጊዜ እንደዚያው ትላለህ። የዚህ ድምር ሰባ አምስት ተስቢሕ ይሆናል። በአራቱም ረከዓ ተመሳሳይ ታደርጋለህ። በድምሩ ሦስት መቶ ተስቢሕ ይሆንልሃል።
በአንደኛው እና በሦስተኛው ረከዓ ላይ ከሁለተኛው ሱጁድ ሲነሳ "ጀልሰቱል‐ኢስቲራሓ" ላይ ሆኖ ተስቢሑን ያደርጋል። ስለዚህ ከሱጁድ መነሳት ሲጀምር የመነሻ ተክቢራውን ያደርግና ተስቢሑን ያስከትላል። ከጀልሳዋ ሲነሳ ግን ተክቢራ ማድረግ አያስፈልገውም።
ከሁለተኛው ሱጁድ በኋላ ተሸሁድ በሚያደርግባቸው ሁለተኛው እና አራተኛው ረከዓ ላይ ደግሞ ከተሸሁዱ በኋላ ተስቢሑን ያደርጋል።
በተጠቀሰው ተስቢሕ ላይ "ላ ሐውለ ወላ ቁው‐ወተ ኢል‐ላ ቢል‐ላሂል‐ዐዚም" መጨመር ይወደዳል።
784 views11:46