2023-04-19 08:15:54
ዘካቱል‐ፊጥር ወደ ሀገርቤት መላክ
=======================
በሻፊዒያ መዝሀብ መሰረት የገንዘብ ዘካንም ሆነ ዘካቱል‐ፊጥርን ከወጀበበት ሀገር ወደ ሌላ ሀገር መውሰድ አይፈቀድም። ይኸውም ከወጀበበት ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ዘካውን ማዛወር የሚያስፈቅድ አሳማኝ ምክንያት እስከሌለ ድረስ ነው።
የዚህ ሃሳብ አስረጂ የሙዐዝ ኢብኑ ጀበል [ረዲየላሁ ዐንሁ] ሐዲስ ነው። ሰይዲና ሙዐዝ ወደ የመን በተላኩ ጊዜ ነቢዩ [ﷺ] እንዲህ አሏቸው: ‐
«ከኃብታሞቻቸው ተወስዶ ለድኾቻቸው የሚካፈል ምፅዋት (ዘካ) እንዳለባቸው አሳውቃቸው።» ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።
በዚያ ላይ የገንዘቡ ምንጭ የሆነው ሀገር ድኾች በዘካው ላይ ተስፋ ጥለው በጉጉት እየጠበቁ ሳለ ዘካውን ወደሌላ ቦታ መውሰድ መከፋት ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል። የሚኖርበት ሀገር ድኾች በዘካ ሰጪው ላይ መጥፎ ስሜት እንዲያድርባቸውም ያደርጋል።
ነገርግን በዘካው ሀገር ላይ ዘካ የሚገባው ሰው ከታጣ ወይም የሰውየው ዘካ ከሀገሩ ባለ መብቶች ፍላጎት በላይ ሆኖ ከተገኘ ወይም ዘካውን የሚያከፋፍለው የሀገር መንግስት ከሆነ ዘካን ከባለ ዘካው ሀገር (በለዱል‐ዉጁብ) ወደ ሌላ አካባቢ መውሰድ ይቻላል።
ይህ ሀሳብ ከሻፊዒዮቹ በተጨማሪ ከማሊኪዮቹ በብዛት የተዘገበ መዝሀብ ነው። ኢብኑ ቁዳማ "አል‐ሙግኒ" በተሰኘው መፅሀፋቸው ላይ እንደጠቀሱት ኢማም አሕመድም ሶላት ማሳጠር የሚፈቀድበት ርቀት ያክል ዘካን ማዘዋወር ይከለክላሉ።
* * *
ኢማም ሐሰን አል‐በስሪይ፣ ኢማም አን‐ነኸዒይ እና ሐነፊዮቹ ደግሞ ዘካን ከወጀበበት ሀገር ወደ ሌላ ሀገር ማዘዋወር በቀላሉ የሚጠላ (ከራሃቱ አት‐ተንዚህ) ነው ይላሉ። ይህንን ያሉበት ምክንያት የባለ ዘካውን ጎረቤቶች መብት በማሰብ ነው።
ነገርግን በእነዚህ የዐሊሞች ቡድን መሰረት ሰውየው ዘመዶቹን አስቦ ከገንዘቡ ሀገር ዘካውን ያዛወረ ከሆነ ከቶውንም አይጠላም ባይ ናቸው። እንደውም እንደነርሱ ከሆነ ተገቢው ለዘመዶቹ መላክ ነው። "ሙጅመዕ አዝ‐ዘዋኢድ" በተሰኘው መፅሀፍ ላይ በተከታዩ ሐዲስ የአላህ መልክተኛ [ﷺ] እንዲህ ማለታቸው ተዘግቧል: ‐
«የዝምድና ቅጠላውን (ድጋፉን) የሚሹ ዘመዶች ያሉትን ሰው ምፅዋት አላህ አይቀበልም።»
በሌላ ሐዲስም የአላህ መልክተኛ [ﷺ] እንዲህ ይላሉ: ‐
«ሶደቃ ለምስኪን ሲሰጥ ምፅዋት ብቻ ነው። ለዘመድ ሲሰጥ ግን ምፅዋት እና ዝምድና መቀጠልም ነው።»
በተጨማሪም ነቢዩ [ﷺ] የዐረብ ዘላኖችን (አዕራቦች) ዘካ ሰብስበው ለመዲና ሙሀጂር እና አንሷሮች ያካፍሉ እንደነበር በሰፊው ተዘግቧል።
እንደውም በተጠቀሰው እና በሌሎችም መረጃዎች የተደገፈውን የሐነፊዮቹን ሃሳብ ከቀደምቶቹም ሆነ ከቅርቦቹ (ሙተኣኺር) ሻፊዒዮች መካከል በርካቶች ተጠቅመውበታል። አል‐ቀልዩቢይ "አልሓሺያ ዐላ ሸርሒል‐ሚንሃጅ" በተሰኘው መፅሐፋቸው ላይ እንዲህ ይላሉ: ‐
«…ሁለተኛው ሃሳብ: ‐ «ዘካን ከቦታው ማዛወር ይፈቀዳል፤ ያብቃቃል» ይላል። ከሻፊዒይ አንጋፋ ባልደረቦች (አስሓብ) በርካቶች ይህንን ሃሳብ መርጠዋል። ኢብኑ ሶላሕ፣ ኢብኑል‐ፈርካሕ እና ሌሎችም ከነርሱ ይጠቀሳሉ።
ሸይኻችን (ጀላሉዲን አል‐መሐሊይ) ሸይኻችን [ኢማም] ረምሊይን ዋቢ አድርገው እንደጠቀሱት: ‐ «ሰውየው ለግሉ በዚህ ሃሳብ መስራት ይችላል። ልክ እንደዚሁ በማናቸውም ህግጋት ላይ የሚታመኑትን ኢማሞች ተከትሎ መስራት ይችላል። ድጋፍ ባለው ሃሳብ (ሙዕተመድ) መሰረት እንደ አል‐አዝረዒይ፣ ሱቡኪይ፣ አል‐ኢስነዊይን እና ሌሎቹንም መከተል ይፈቀድለታል።»
በመሆኑም በተለይም ከሀገር ውጪ ሆነው ዘካቸውን ወደ ሀገር ቤት መላክ የሚሹ ሰዎች ይህንን መዝሀብ ቢከተሉ መልካም ነው የሚል ጥቆማ እንሰጣለን። በተለይም ሀገራችን አሁን ላይ እያሳለፈችው ባለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውጥንቅጥ አንፃር ለወገን የመድረስ እና ህይወትን የመታደግ ያክል ስለሚሆን ጉዳዩ አሳሳቢ ይሆናል። ከሀገራችን ችግረኞች የቀደመ ተገቢነት ያለው ሌላ አካል ይኖራል ተብሎም አይገመትም።
በተረፈው መጠኑን ሰውየው በሚኖርበት ሀገር ተመን መሰረት ዘካውን ያሰላዋል እንጂ ዘካውን ማዛወር በፈለገበት ሀገር ዋጋ አያሰላውም።
ኢማም ነወዊይ [ረሒመሁላህ] "አል‐መጅሙዕ" በተሰኘው መፅሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል: ‐
«ከፊል ገንዘቡ በአንድ ሀገር ላይ ሆኖ ከፊሉ በሌላ ሀገር ቢሆን እንኳን ያለ ምንም (የሻፊዒዮች) ልዩነት ዘካቱል‐ፊጥሩን የሚሰጠው እርሱ በአካል ባለበት ሀገር ነው።»
አላሁ አዕለም!
http://t.me/fiqshafiyamh
1.1K viewsedited 05:15