2023-05-15 09:43:21
በደል ያጠፋል፣ ፍትህ ይክሳል!
ሀገራችን ባለፉት አመታት ካሳለፈችው አስከፊ ጦርነት ተላቃ በጦርነቱ ሳቢያ የተመሰቃቀሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ለማስተካከል ብዙ ሸክም ይጠብቃታል::
ይህ ከባድ ሸክም በመንግስት ላይ ብቻ ሳይሆን ይበልጡኑ በህዝቡ ላይ ጫናው የበረታ ነው:: በኑሮ ውድነት፣ በብልሹ አሰራር እና በፖለቲካ ሴራዎች ህይወትን መግፋት ከባድ እየሆነበት ላለው ህዝብ አግባብነት በሌላቸው ውሳኔዎች እና የግል ፍላጎቶች ዜጎች እንዲማረሩ እየተደረገ ይገኛል:
መንግስት ለዜጎቹ ጥላ እና ከለላ መሆን ሲገባው መጠለያ እና ከለላ ነሺ ከሆነ፣ በመግባባት እና በመተማመን መፈታት የሚገባቸውን የማህበረሰብ ችግሮች ኃይልን ብቻ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለመፍታት ከተሞከረ፣ አቅመ ደካሞችን እና ድሆችን አቅፎ ከችግራቸው ለማላቀቅ ከመልፋት ይልቅ በችግር ላይ ችግር በእነሱ ላይ መጨመር አማራጭ ተድርጎ ከተያዘ፣ የዜጎች በሰላም ወጥተው የመግባት መብታቸው አደጋ ውስጥ ከወደቀ፣ በፈለጉት የሀገሪቷ ቦታዎች ተዟዙሮ የመኖር እና የመስራት ህጋዊ መብቶች ከተነፈጉ፣ ከህግ አግባብ ውጪ በታጣቂዎች እና በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች የሚወሰዱ የዘፈቀደ እስር እና ግድያዎች መበራከት፣ የእምነት ተቋማት እየተደፈሩ በግብረሀይል የሚወድሙ ከሆኑ፣የሀይማኖት ነፃነትን በሚጋፋ መልኩ ሀይማኖታዊ አለባበሶችን የሚገድቡ አመራሮች እዚህም እዛም መኖራቸው፣ በህዝብ እና በመንግስት መካከል ያለው የመተማመን ስሜት እንዲጠፋ እና እንዲሸረሸር ያደርጋል::
ዜጎች የሚደርስባቸውን በደል እና ግፍ ለማስቆም ስሞታቸውን ሲያሰሙ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ መጓዝ፣ የበላይ አመራሮች እና ሀላፊዎችም የህዝብን እሮሮ አድምጠው የማስተካከያ እና የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ አፋጣኝ አቅጣጫ ከመስጠት ይልቅ ዳተኛ መሆናቸው ሀገሪቷን ለሚመራው መንግስትም ትልቅ ዕዳ ይዞ መምጣቱ አይቀርም::
በደል መጨረሻው ውርደት እና ጨለማ ነው:: ከግለሰብ አንስቶ እስከ ማህበረሰብ በጅምላ የሚፈፀሙ በደሎች እና ግፎች ድምር ውጤታቸው በበዳዮች ላይ ኪሳራን እንጂ አይጨምርላቸውም::
ጌታችን አላህ ሱወ በቅዱስ ቃሉ ይህን ይለናል
"አላህንም በደለኞች ከሚሠሩት ግፍ ዘንጊ አድርገህ አታስብ፡፡ የሚያቆያቸው ዓይኖች በእርሱ እስከሚፈጡበት ቀን ድረስ ብቻ ነው" (ሱረቱል ኢብራሂም:42)
ስልጣን ህዝብን ማገልገያ መሳሪያ ነው:: ይህን ትልቅ ሃላፊነት የተረከበ አመራር ሃላፊነቱን ለመወጣት ቃለመሀላ ሲፈፅም ለህዝብ ታማኝ ሆኜ በቅንነት ላገለግል ቃል እገባለው ያለውን መዘንጋት የለበትም::ሃላፊነቱን በመረከቡ ትልቅ ተጠያቂነትም ይኖርበታል:: ከታችኛው የመንግስት መዋቅር ሲያጠፋ የላይኛው አመራር ተጠያቂነትን እንዲሰፍን ካላደረገ ህዝብን ወደ ምሬት ማስገባቱ አይቀርም::
ህዝብን በእኩልነት እና በፍትህ ማስተዳደር በበደል የጎበጡ ትከሻዎችን እና የቆሰሉ አካሎችን ይጠግናል:: በደልን የሚጠየፍ መሪ ከተጠያቂነትም ይድናል:: ሁሉም ባለድርሻ አካላት ባሉበት የሀላፊነት ደረጃ እኩልነትን፣ ፍትህን እና አገልጋይነትን መርሃቸው አድርገው ሊጓዙ እንደሚገባ ለማሳሰብ እወዳለሁ
Ustaz abubeker ahmed
https://t.me/fethababora
https://t.me/fethababora
https://t.me/fethababora
134 views06:43