2023-06-07 17:52:11
በአላህ ስም እጅግ በጣም አዛኝ እጅግ በጣም ሩህሩህ በሆነው
በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ እና የእምነት ቤቶችን
የማውደም ሂደት በመቃወም በአውሮፓ ካሉ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊም ማህበራት
የተሰጠ የአቋም መግለጫ
በአስቸኳይ የሚወጣ
ጁን 06፣ 2023
በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ-ኢትዮጲያ ሙስሊሞች በትውልድ
አገራችን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አስመልክቶ ውይይት በማድረግ የገመገምን ሲሆን በተለይም መንግስት
ከባለፈው ረመዳን (አፕሪል 2023) ወር መግቢያ ጀምሮ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን መጠለያ አልባ
ያደረገ የቤቶች ፈረሳ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የእስልምና እምነትን እና የእምነቱ ባልተቤቶችን ክብር
ባራከሰ መልኩ መስጂዶችን እና ቅዱስ መጻህፍቶቻችንን ያወደመበት ሂደት እጅጉን አዛንኖናልም፤
አስቆጥቶናልም።
መንግስት በተዋረድ እስከ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ድረስ ያሉ የሙስሊሙ
ወካይ ድርጅቶች ችግሩን በውይይት ለመፍታት ያቀረቡትን ተከታታይ አቤቱታ ትኩረት በመንፈግ
ባለፉት ሁለት ጁመዓዎች ላይ ያለምንም ትንኮሳ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በአንዋር መስጊድ
በተሰባሰቡ ምዕመናን ላይ ባካሄዱት የሽብር ዘመቻ የበርካታ ወጣቶች ህይወት ተቀጥፏል። በዚህም
የአገራችን እና የህዝባችን እጣ ፈንታ ከመቸውም በላይ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መድረሱን ተገንዝበናል።
ከዛሬ አምስት አመት ገደማ አገኘን ላልነው ለውጥ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ያደረገው እልክ አስጨራሽ
ትግል መሸጋጋገሪያ ሆኖ እንዳገለገለ የሚካድ አይደለም። ሆኖም ግን ለዝህባችን ሰላምን፣ እድገትን እና
ነጻነትን ያመጣል ብለን ያመነው ሂደት ራሱ ለዜጎች ኑሮ መመሳቀል እና መሰረታዊ ለሆነው ሰላም ማጣት
ምክንያት መሆን የለበትም ብለን እናምናለን። ለልማት የሚደረግ የትኛውም እንቅስቃሴ እና የሚወሰድ
እርምጃ ቅድሚያ ለዜጎች ደህንነት እና መብት መከበር ሊሰጥ ይገባል። በነጻነት የማምለክ እና
እምነታቸውን ማደራጀትና ማስፋፋት ደግሞ የዚህ መሰረታዊ የዜጎች መብት አካል ነው። ስለዚህ
በየትኛውም መልኩ በልማት ስም መስጂዶችን በማን አለብኝነት እስከ ማፍረስ የተሄደበት አካሄድና
የዜጎችን የማምለክና በሰላም የመቃወም መብትን በመጣስ ዉድ ህይወትን እስከመቅጠፍ የተወሰደው
እርምጃ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው።ስለሆነም
1. በልማት ስም በሸገር ከተማ እየተደረገ ያለው የመስጂድ ፈረሳ በአስቸኳይ እንዲቆም።
2. መንግስት ይህን አይነት ዜጎችን ከፍተኛ ለሆነ ምስቅልቅል የዳረገ እርምጃውን ቆም ብሎ እነዲያጤንና
አስፈላጊውን ማስተካከያ እንዲያደርግ።
3. የሸገር ከተማ አስተዳደር የእምነት ቦታዎችን እስከማውደም የሄዴበትን ሂደት መንግስት
ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤቶች ጋር በመተባበር እንዲመረምር እና ዘለቄታ
ያለው የመፍትሄ አርምጃዎችን በአስቸኳይ እንዲወስድ።
4. በአንዋር መስጊድ ተሰብስበው የመስጊድ ማፍረስ ዘመቻውን ተቃውመዋል በሚል መንግስት
ለወሰደው የህይወት መጥፋት፣ የአካል መጉደል እና የንብረት መውደም በአጠቃላይ በሙስሊሙ
ህብረተሰብ ላይ ለከፈተው የሽብር ዘመቻ ሃላፊነቱን እንዲወስድ። በድርጊቱ ላይ ተሳታፊ አካላትን
በመለየት እርምጃ እንዲወስድ። በእስር ላይ የሚገኙ ንጹሃንን በአስቸኳይ እንዲለቅ።
5. መንግስት የእምነት ጉዳይ የዜጎች ቀይ መስመር መሆኑን በመገንዘብ ወደፊት በልማትም ይሁን ለሌላ
ጉዳይ ሃይማኖትን እና የእምነት ቦታዎችን የሚመለከት እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ከሚመለከታቸው
የእምነቱ ተከታዮችና ድርጅቶቻቸው ጋር መግባባት ላይ እንዲደርስ እናሳስባለን።
ለአገራችን ልማትና እድገት ያለን ቀና አስተሳሠብ፣ ለስኬቱም እና ለቀጣይነቱ የምናደርገው ርብርብ
እንዳለ ሆኖ በእምነታችን ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚደረግ የትኛውም እርምጃ ቀይ መስመራችን
መሆኑን እየገለጽን አሁን ያለውን የመንግስት አስፈሪ እና አገራችንን እና ህዝባችንን ልንወጣ
ወደማንችለው አሮንቃ ዉስጥ የሚከት ሂደት ይቀለበስ ዘንድ የሚጠበቅብንን ሃላፊነት ለመወጣት
ዝግጁነታችንን እንገልጻለን። ለዚሁም ያግዝ ዘንድ ከሁሉም አገር ማህበራት የተውጣጣ ልዩ ኮሚቴ
በማቋቋም ክትትል የምናደርግ መሆኑንም ጨምረን እናሳውቃለን።
አላሁ (ሱወተ) አገራችንንና ህዝባችንን ይጠብቅልን።
“እርሱ (አላህ) ረዳታችን ነው፤ በአላህ ላይ ምዕመናን ይመኩ” (አል - ተውባ 09፡51)
አላሁ አክበር!
ፈራሚ ሙስሊሞች ማህበራት
• ኢቅራእ ተቋም - ዩናይትክ ኪንደም
• ሰላም ኢትዮ-ጀርመን አንድነት ማህበር
• ነጃሺ የኢትይጵያዊያን ሙስሊሞች ማህበር በስዊድን
• ሰንሰለት ፋውንደሽን - ኔዘርላንድ
• ሉቅማን ኢትዮጵያ - ቤልጂየም
• ኢትይጵያዊያን ሙስሊሞች ማህበር በፊንላንድ
• ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ማህበር በኖርዌይ
• ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ማህበር በስዊዘርላንድ
• ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ማህበር በአውስትሪያ
https://t.me/fethababora
https://t.me/fethababora
https://t.me/fethababora
171 views14:52