2023-04-15 15:44:40
" በሚዲያ ጥፋት የተጠረጠሩ ታሳሪዎች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር ሊለቀቁ ይገባል " - ኢሰመኮ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችንና አባላትን፣ የሚዲያ አባላትንና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ዒላማ ያደረገ እስር እና ወከባ በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል።
ኢሰመኮ በተለያየ ዓይነት ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ከተያዙ ሰዎች ውስጥ በተለይ የሚዲያ አባላትን፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላትን እንዲሁም የማኅበረሰብ አንቂዎችን (Activists) ጉዳይ በተመለከተ ክትትል ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ ከእነሱም መካከል፦
ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ በቁጥጥር ስር የዋሉ
የሚዲያ አዋጁን (የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013) በሚጻረር መልኩ የታሰሩ
በተራዘመ ቅድመ-ክስ እስር ወይም ክስ ሳይመሠረትባቸው በእስር የቆዩ መኖራቸውን፣ በተወሰኑት ላይ የወንጀል ክስ ተመሥርቶ የነበረ ቢሆንም ክሱ በበቂ ማስረጃ የተደገፈ ባለመሆኑ በፍርድ ቤት ውሳኔ ውድቅ ተደርጎ ወይም በፖሊስ ውሳኔ ከተራዘመ እስር በኋላ በነጻ ወይም በዋስትና የተለቀቁ መኖራቸውን ኮሚሽኑ ተመልክቷል።
ኮሚሽኑ መጋቢት 21/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እስከ አሁን ድረስ በእስር ላይ ከሚገኙት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ አመራሮችንና የሌሎችም ተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት ላይ የሚደርሱ እንግልት እና እስሮችን ጠቅሶ መንግሥት የሰዎችን በሕዝባዊ ጉዳዮች ውስጥ የመሳተፍ መብታቸውን የሚገድቡ ተግባሮችን የመመርመርና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት ማሳሰቡን አስታውቋል።
በቅርብ ጊዜ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ያተኮሩ እስሮች እና ማዋከብ እናት ፓርቲን፣ በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲን እና የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲን ይጨምራል።
በዚህ ወር ውስጥ በርካታ የሚዲያ አባላት መታሰራቸውን ኢሰመኩ ገልጿል።
ከፊሎች በእስር ወቅት ተገቢ ላልሆነ አያያዝ የተዳረጉ፣ ከፊሎች ከዚህ በፊት ለተመሳሳይ እስር ተዳርገው የነበሩ እና፣ ከፊሎችም ከተለያየ ጊዜ መጠን እስር በኋላ የተለቀቁ ናቸው።
መንግሥት የወንጀል ተግባሮችን ሁሉ የመከላከል፣ የመመርመርና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት፣ በሚዲያ አባላትና የማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ የሚያተኩር እስር ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመደራጀትና በሕዝባዊ ጉዳዮች የመሳተፍ መብቶች ላይ የሚያስፈራራ፣ የሚያሸማቅቅ እና የሚገድብ ውጤት እንዳይኖረው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ ነው ብሏል ኢሰመኮ።
በመሆኑም የመንግሥት የጸጥታ አካላት፦
- በፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት፣ በሚዲያ አባላትና በማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ ካተኮረ እስርና ማዋከብ እንዲቆጠቡ፣
- በወንጀል የተጠረጠሩና በበቂ ሕጋዊ ምክንያት በቅድመ-ክስ ሊታሰሩ የሚገባቸው ሰዎች በሚኖሩበት ሁኔታም በሕግ በተመለከተው መንገድ ብቻ በጥብቅ ጥንቃቄ አንዲፈጸም
- የተጠረጠሩ ሰዎችን ሁሉ ከምርመራ በፊት ከማሰር እንዲቆጠቡ፣
- በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 መሠረት በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል፣ በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዐቃቤ-ሕግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ ያለበት መሆኑ በግልጽ የተደነገገ በመሆኑ፤ በዚሁ መሠረት እንዲፈጸምና በሚዲያ አማካኝነት ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል ተጠርጣሪ የሆኑ ታሳሪዎች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ ኢሰመኮ አሳስቧል።
141 views12:44