Get Mystery Box with random crypto!

ከዛሬ ጀምሮ የክልል ልዩ ኃይል የሚባል አደረጃጀት የለም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከዛሬ | Ewnet Media

ከዛሬ ጀምሮ የክልል ልዩ ኃይል የሚባል አደረጃጀት የለም

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ከዛሬ ጀምሮ የክልል ልዩ ኃይል የሚባል አደረጃጀት የሌለ መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

የክልል ልዩ ሃይሎችን በፌዴራልና የክልል የጸጥታ ተቋማት መልሶ የማደራጀት ስራ የመከላከያ ጀነራሎች፣ ፌዴራል ፖሊስ እና የክልል የስራ ኃላፊዎች በተገኙ ተገምግሟል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ የክልል ልዩ ሃይሎች እንደገና በመደራጀታቸው ህብረ ብሄራዊ ጠንካራ የጸጥታ ተቋም ይገነባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከነበረችበት የጸጥታ ችግር በፍጥነት መውጣቷን የገለፁት ፊልድ ማርሻሉ፤ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የክልል ልዩ ኃይሎች አደረጃጀት ህጋዊ አለመሆን፣ በክልሎች መካከል እንደ ስጋት መተያየት እንዲሁም ችግሮችን በሃይል ለመፍታት የሚደረገው እንቅስቃሴ አደረጃጀቱን ለመቀየር አስገድዷል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በሁሉም ክልሎች መልሶ የማደራጀት ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመው "ከዛሬ ጀምሮ የክልል ልዩ ኃይል የሚባል አደረጃጀትና መዋቅር የለም" ብለዋል።

በመሆኑም የጸጥታ መዋቅሩ መከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስና የክልል ፖሊስ ሲሆን በክልል ልዩ ኃይሎች ስም ተልዕኮም ሆነ ግዳጅ የሚቀበል ኃይል አይኖርም ሲሉ አረጋግጠዋል።

ከዚህ በኋላ በመረጡት አደረጃጀት መሰረት ሁሉንም ወደ ተመደቡበት የማጓጓዝና ወደ ስልጠና የማስገባት ስራ ይከናወናል ብለዋል።