2022-08-30 14:37:21
አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሊዩሽን የአቅርቦት እና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ጀመረ
አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሊዩሽንስ አ.ማ ከተሰማራባቸው አስራ አንድ የቴክኖሎጂ ዘርፎች መካከል በድረገጹ የሚሰጠውን የምርት አቅርቦት እና ሎጀስቲክስ አገልግሎት በዛሬው እለት አስጀምሯል፡፡
ዲጂታል ኢትዮጲያ 2025 ራዕይን ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረገውን የመንግስት ጥረት እያገዘ መሆኑን የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል በቀለ ተናግረዋል፡፡
አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሊዩሽንስ በአሁኑ ሰአት ከ1600 በላይ አቅራቢዎችን በመያዝ ፤ ከ5 ሺህ በላይ ምርቶችን ashewa.com በተሰኘው ድረገጹ ላይ እያገበያየ ነው፡፡
በዛሬው እለት ስራ ያስጀመረው የምርቶች አቅርቦት እና ሎጀስቲክስ አገልግሎት የኑሮ ውድነትን እና ገበያን ለማረጋጋት ሚና ይኖረዋል የተባለ ሲሆን ቀላል እና አስተማማኝ በሆነ መንገድ የገጠሩን ማህበረሰብ ከከተሜው ጋር በቢዝነስ ለማስተሳሰር የተዘጋጀ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በቀጣይ አንድ ወር በአገልግሎቱ ከ15 ሺህ በላይ ከሆኑ ነጋዴዎች ፤ ከ10 ሺህ በላይ ለሆኑ ደንበኞች ከ5 ሺህ በላይ ምርቶችን በማቅረብ ለመስራት ታቅዷል፡፡
ድርጅቱ በአሁኑ ሰአት አገልግሎቱን የሚሰጠው በአዲስ አበባ ሲሆን ለምርቶች ማከማቻ የሚሆኑ ሶስት መጋዘኖችን እንዳዘጋጀ የዴሊቨሪ እና ፈጣን መልእክት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ገ/ማርያም አለሙ ለኢትዮ የንግድ እና ኢንቨስትመንት መድረክ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ የመጋዘኖቹን ቁጥር ወደ 8 ለማሳደግ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ስርአት ምርቶችን የሚገዙ ደንበኞች የሚፈልጉትን ምርት በመረጡት የተሽከርካሪ አይነት ካሉበት እንዲደርሳቸው የሚደረግ ሲሆን ምርቱን ከገዙ በኋላ ባሉት ሰባት ቀናት ውስጥ ተመላሽ ማድረግ ወይም ቅያሪ ቢፈልጉ እንደሚስተናገዱ አቶ ገ/ማርያም ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ምርቶቻቸውን መሸጥ የሚፈልጉ ነጋዴዎችም በተዘጋጁት መጋዘኖች እስኪሸጡ ድረስ ማስቀመጥ ይችላሉ፡፡
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ነሐሴ24 ቀን 2014 ዓ.ም
2.4K views11:37