2022-09-01 09:27:28
ኤሌክትሪክ እና የሚያከትለው አደጋ
*************
ኤሌክትሪክ ለአንድ ሃገር የማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ልማት ስኬት የሚጫወተው ሚና እጅግ የጎላ ነው፡፡ ከእያንዳንዱ ተጠቃሚ የዕለት እንቅስቃሴ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ድረስ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚጫወተው ሚና በቀላሉ ተጠቅሶ አያልቅም፡፡
ታዲያ ይህ እጅግ አስፈላጊና የልማቱ የጀርባ የሆነው ኤሌክትሪክ በአግባቡና በጥንቃቄ ካልተጠቀምነው በአካልና በንብረት ላይ የሚያደርስው አደጋ ከፍተኛ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
የኤሌክትሪክ አደጋ የማስተላለፊያና የማሰራጫ መስመሮች ተፈጥሮዊና ሰው ሰራሽ በሆኑ ምክንያቶች ጉዳት ሲደርስባቸው፣ የማስተላለፊያ መስመሮች ሲበጠሱ፣ ገመዶች እርስ በርሳቸው ሲነካኩ እና የኤሌክትሪክ ተሸካሚ ምሰሶዎች ሲወድቁ ባለማወቅ በሚደረግ ንኪኪ ሊከሰት ይችላል፡፡
የመሰረተ ልማት ስርቆት፣ የኤሌክትሪክ ምሰሶና ትራንስፎርመር ባለበት ቅርብ ርቀት ላይ ግንባታ ወይም የንግድ ሥራ ማከናወን፣ በቤት ውስጥ የኤሌክትሪክ ኢንስታሌሽን በባለሞያና በአግባቡ አለማከናወን፣ ቆጣሪ ያለግባብ መነካካትና ሌሎችም ለኤሌክትሪክ አደጋ መከሰት ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው፡፡
የኤሌክትሪክ አደጋ ሲከሰት ከፍተኛ የሆነ የአካል ጉድለት፣ የንብረት ውድመትና የህይወት መሰዋትነት የሚያስከትል በመሆኑ፤ አደጋዎች እንዳይከሰቱ፣ ከተከሰቱም ጉዳት ሳያደርሱ ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን ያስፍልጋል፡፡
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአካልና በህይወት ሊደርስ የሚችለውን የኤሌክትሪክ አደጋ ለመቀነስ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን፤ ለህብረተሰቡ ግንዛቤን የሚያሳድጉ መረጃዎችን ከማድረስ በተጨማሪ ለአደጋ መንስኤ የሚሆኑ ያረጁ መሰረተ ልማቶችን የማሻሻልና ዓቅም የማሳደግ ሥራ በየጊዜው እየሰራ ይገኛል፡፡
ለሠራተኞቹም የኤሌክትሪክ አደጋ የሚመለከቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና የመስጠት፣ የቅድመ አካባቢያዊና ማህበራዊ ጥናት ማካሄድ፣ የሴፍቲ ኦዲት ማከናወን፣ የስራ ላይ ደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎችን የማሟላት ተግባር በሰፊው እየሰራ ነው፡፡
ተጠቃሚው ህብረተሰብም የኤሌክትሪክ አደጋ እንዳይከሰት ከመከላከል አኳያ የራሱ ሚና መወጣት አለበት፡፡ ሁሉም ደንበኛ የጥራት ደረጃቸውን ከፍ ያሉ መገልገያ ቁሳቁሶችን መጠቀም፣ የቤት ውስጥ ኢንስታሌሽን ስራ በባለሞያ ብቻ ማከናወን፣ የኤሌክትሪክ ምሰሶች በቆሙበት አካባቢ ግንባታዎችና ሌሎች የንግድ ስራዎችን ከመስራት መቆጠብ፣ በኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ ልብስና መሰል ፖስተሮችን አለማስቀመጥ፣ ህፃናትን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ካለባቸው አካባቢዎች እንዲጫወቱ አለመፍቀድ ያስፈልጋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ገመዶች በተለያዩ ምክንያቶች ተበጥሰው ሲወድቁ በእጅ አለመንካትና የተቋረጠውን መስመር በራስ ለማገናኘት አለመሞከር ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ ያስችላል፡፡
ኤሌክትሪክ የማገናኘት ሥራ በቂ ሙያዊ እውቀት የሚጠይቅ የስራ ዘርፍ በመሆኑ ማንኛውም አካል የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮችን፣ ትራንስፎርመሮችንና የተቆረጡ የኤሌክትሪክ ገመዶችን ከመንካት ሊቆጠብ ይገባል፡፡
የኤሌክትሪክ መስመሮችን የመጠገን ስራ በሃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመሆኑ ከተቋሙ ሠራተኞች ውጭ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን የሚነካካ አካል ሲኖር ለህግ አስከባሪ አካላት በማሳወቅ ተጠያቂ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በመጨረሻም የ2015 አዲስ ዓመት እየደረሰ በመሆኑና ከወትሮው በተለየ በበዓላት ወቅት የሚኖረው የኤሌክትሪክ አጠቃቀማችን ከፍ ስለሚል አደጋ እንዳይከሰት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡ ከላይ የተዘረዘሩትን ልዩ የጥንቃቄ መንገዶችን በመጠቀም የኤሌክትሪክን አደጋ መከላከል ያስፈልጋል፡፡
ድንገት ያልታሰበ አደጋ ቢደረስ ወይም አጠራጣሪ ነገሮች ከተመለከቱ በአቅራቢያ ከሚገኝ የተቋሙ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በአካል በመሄድ ወይም በ905 ነፃ የጥሪ ማዕከል በመደወል ማሳወቅ ይቻላል፡፡
#የኢትዮጵያኤሌክትሪክአገልግሎት
ወቅታዊና ትኩስ የተቋማችን መረጃዎች ወዲያውኑ እንዲደርሳችሁ እነዚህን የትስስር ገፆቻችንን ይወዳጁ፡-
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/EEUOfficial/
ቲዊተር፡ https://twitter.com/EEUEthiopia
ቴሌግራም፡ t.me/eeuethiopia
ዩቱዩብ: https://www.youtube.com/c/EthiopianElectricUtility
ድረ-ገፅ፡ http://www.eeu.gov.et
3.0K views06:27