2022-09-08 11:09:19
የኃይል ጭነት በማይበዛባቸው ሰዓታት ኤሌክትሪክ መጠቀም የላቀ አስተዋፅኦ አለው
************************
መጪው የ2015 አዲስ ዓመት በዓል ዋዜማ ላይ እንገኛለን፡፡ እንደሚታወቀው በዓላት ሲመጡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፍላጎት ይጨምራል፡፡ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ተቋማችን አስቀድሞ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እያከናወነ ይገኛል፡፡
ተቋሙ በበዓሉ ዋዜማና በዕለቱ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መዋዥቅ ችግር ሳያጋጥም ለተጠቃሚው ለማድረስ፣ ችግሩ ከተከሰተም አፋጣኝ የአስቸኳይ ጥገና በማከናወን የተቋረጠውን አገልግሎት መልሶ ለማገናኘት የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎች በማከናወን ላይ ሲሆን፤ ለዚህም የሚረዳ ከኮርፖሬት ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የአስቸኳይ ጥገናና ቅደመ-መከላከል ግብረ-ሃይል አቋቁሟል፡፡
ከኃይል ማመንጫ ጀምሮ እስከ ማሰራጫ መስመር ድረስ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በአግባቡ ለመፍታትና አቅርቦቱን ለማሳለጥ እንዲቻል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል ዝግጅትም ተደርጓል፡፡
ሆኖም መሰል ዝግጅት ቢደረግም ኤሌክትሪክ በባህሪው በተለያዩ ምክንያቶች አልፎ አልፎ ሊቋረጥ እንደሚችል በመገመት በተለይ የመኖሪያ ቤት የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ደንበኞች በአጠቃቀም ወቅት የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ይገባቸዋል፡፡
በዋዜማውና በዓሉ እለት ደንበኞች የኤሌክትሪክ አጠቃቀማቸው የኃይል ጭነት በማይበዛባቸው ስዓታት በተለይ ከምሽቱ 4፡00 እስከ ንጋቱ 11፡00 ባለው ጊዜ ቢጠቀሙ አስተማማኝና የማይዋዥቅ ኃይል ለማግኘት እንዲሁም በዲስትሪቡዩሽን መስመር ላይ የሚፈጠር መጨናነቅን ለመቀነስ የላቀ ሚና አለው፡፡
በተጨማሪም በዚህ ሰዓት መጠቀም በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ለመጨረስ፣የፍጆታ ሂሳብንም ለመቀነስ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተገንዝበው፤ በዚህ አግባብ እንዲጠቀሙ እንመክራለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ደንበኞች በቤት ውስጥ የሚገለገሉባቸውን የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶች ኃይል ቆጣቢና ለአደጋ የማያጋልጡ መሆናቸውን ሊያረጋግጡ ይገባል፡፡
የቅድመ ክፍያ ተጠቃሚ ደንበኞች በዓሉ ሲደርስ የሚኖረውን አላስፈላጊ እንግልት ለማስቀረት እንዲችሉ ከወዲሁ የሚበቃቸውን ያህል የኤሌክትሪክ ኃይል አስቀድመው እንዲገዙ /ካርድ እንዲሞሉ/ እናሳስባለን፡፡
በበዓሉ ዕለት የኤሌክትሪክ ኃይል በሚቋረጥበት ጊዜ የጥገና ስራ ለማከናወን የተቋሙን መታወቂያ የያዙ የቴክኒክ ባለሞያዎቻችን በተለያዩ አካባቢዎች ለስራ ጉዳይ እንደሚንቀሳቀሱ ህብረተሰቡ ተገንዝቦ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም እንጠይቃለን፡፡
ይሁንና የተቋሙን የጥገና ሰራተኞች በመምሰል መሠረተ-ልማቱ ላይ ስርቆትና ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ አካላት ሊኖሩ ስለሚችሉ፤ ህብረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮችን እንደራሱ ንብረት አድረጎ በመጠበቅ እንዲተባበርና እኩይ ተግባራት ሲመለከት ለሚመለከተው የፀጥታ አካላትና ለተቋሙ ማሳወቅ ይገባዋል፡፡
በመጨረሻም ድንገት የኤሌክትሪክ አደጋ ቢያጋጥም፣ ተቋሙን የሚመለከቱ ሌሎች መረጃዎች ለመጠየቅ እንዲሁም ጥቆማዎችና አስተያየቶችን ለማቅረብ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በአካል በመሄድ ማሳወቅ ወይም ወደ 905 ነፃ የጥሪ ማዕከል መደወል እንደሚያስፈልግ እንጠቁማለን፡፡
#የኢትዮጵያኤሌክትሪክአገልግሎት
ወቅታዊና ትኩስ የተቋማችን መረጃዎች ወዲያውኑ እንዲደርሳችሁ እነዚህን የትስስር ገፆቻችንን ይወዳጁ፡-
ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/EEUOfficial/
ቲዊተር፡ https://twitter.com/EEUEthiopia
ቴሌግራም፡ t.me/eeuethiopia
ዩቱዩብ: https://www.youtube.com/c/EthiopianElectricUtility
ድረ-ገፅ፡ http://www.eeu.gov.et
5.0K views08:09