2023-03-02 12:16:33
ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ገበዝ፣ ለጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ያደረገው ተአምር ይህ ነው፤
የሰማዕቱ ረድኤት በረከት አይለየን!!! አሜን!!!
ልመናው ጸሎቱ በረከቱ አማላጅነቱ በዕውነት ለዘለላለሙ ይደረግልንና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረገው ተአምር ይህ ነው ።
በዚያን ወራት ከጌታችን ከኢየሱስ ልደት አንድ ሺህ ስምንት መቶ ሃምሳ ዓራት በኋላ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ በነገሠ በሃያ ስድስት ዓመት የምኒልክ የጦር አለቃ ገበየሁ ድል ከአደረጋቸው በኋላ እንደገና ምኒልክን ወግተው የኢትዮጵያን በቅኝ አገዛዝ ሊገዙ የሮም ሰዎች መጡ።
ከዚህም በኋላ የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ አገሬ ኢትዮጵያን እወዳለሁ የሚል ኢትዮጵያዊ ኹሉ ባስቸኳይ ይነሣ መስቀለ ሞቱንም ተሸክሞ ይከተለኝ እግዚአብሔር የወሰነልንን የባሕር ወሰን አልፎ አገር የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት መጥቷልና ሲል ዓዋጅ አስነገረ ።
ዳግመኛም በፈረሶቻቸው መጣብር ላይ በጦራቸው አንደበት ላይ በጋሻቸው እምብርት ላይ የመስቀል ምልክት እንዲያደርጉ ጭፍሮቹን አዘዛቸው መስቀል ጠላትን ድል አድራጊ እንደኾነ አስቀድሞ ያውቅ ነበርና
ከዚያም ተነሥቶ ወደ ትግራይ ክፍለ አገር ዘመተና ከትግራይ አውራጃዎች አንዷ የምትሆን አድዋ ከምትባል አገር ደረሰ ።
የሣህለ ማርያም(ዳግማዊ ምኒልክ) ሚስት ወለተ ሚካኤል (እቴጌ ጣይቱ) በንጉሡ ትእዛዝ ታቦተ ጊዮርጊስን አሲዛ ከሊቀ ጳጳሱ ከአባ ማቴዎስ ፤እንዲሁም ከቀሳውስቱና መነኮሳቱን ጭምር ከንጉሡ ጋር ወደ ጦርነት ተጓዘች ።
በዚህም ጊዜ የአክሱም ጽዮን መነኮሳትና ካህናት የእመቤታችንን ሥዕል ይዘው ወደ ንጉሥ ወደ ምኒልክ መጥተው ከሊቀ ጳጳሱ ከነአቡነ ማቴዎስ ጋር ተቀላቀሉ ከዚያም ሌሊቱን ሙሉ ጸሎተ ምሕላ ሲያደርሱ አደሩ ።
ቅዳሜ ማታ ለእሁድ አጥቢያ ይኸውም የካቲት ሃያ ኹለት ቀን ነው ንጉሡ ሣህለ ማርያም የጦር ልብሱን ለብሶ ከሠራዊቱ ጋር ወደ ጦር ግንባር ሄደ ። ከዚያም ከሮማውያን የጠላት ጦር ጋር ተገናኝቶ ከሌሊቱ በዓሥራ አንድ ሰዓት ጦርነቱን ጀመረ ።
የንጉሡ የሣህለ ማርያም ሚስት ወለተ ሚካኤል ሌሊት በታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስና በእመቤታችን ሥዕል ፊት በጸሎትና በስግደት እያደረች ሲነጋ ወደጦርነቱ ቦታ በመሄድ እጅግ በሚያስደንቅ የአነጋገሯ ኃይለ ቃል በጦርነቱ መካከል እየተገኘች ለንጉሡ ወታደሮች የሞራልና የብርታት ድጋፍ ትሰጣቸው ነበር ።በዕውነትም ለተመለከታት ኹሉ እንደ ኃይለኛ ተጋዳይ አርበኛ ትመስል ነበር እንጂ የሴቶች የተፈጥሮ ባሕርይ በእርሷ ላይ አይታይም ነበር ።
የንጉሡም ወታደሮች የንግሥቲቱን የጀግንነት አነጋገር በሰሙ ጊዜ በእሳት ላይ እንደተጣደ የብረት ምጣድ ልባቸው ጋለ ይልቁንም ላም እንዳየ አንበሳና የፍየል መንጋ እንዳየ ነብር እየተወረወሩ በጦርነቱ መካከል በመግባት የጠላትን ጦር በሰይፍ ይጨፈጭፉት ነበር ።መጽሐፍ ሹመቱን ሽልማቱን ያየ አርበኛ ከጦርነት ከሰልፍ ወደኋላ አያፈገፍግም ብሎ ተናግሯል ።
በዚያም ጊዜ ንጉሡ ሣህለ ማርያም በጦርነቱ መካከል ሳለ ሊቀ ጳጳሱ አባ ማቴዎስ እንዲሁም የአክሱም መነኮሳት እና ሌሎቹ ካህናት በሙሉ ታቦተ ጊዮርጊንና ሥዕለ ማርያምን ይዘው ከንጉሡ በስተኋላ በደጀንነት ቆመው ጸሎተ ምህላ ያደርሱ ነበር ።ንግሥቲቱ ወለተ የሚካኤል በጸሎት ጊዜ በመዓልትም በሌሊትም ከእነሱ አትለይም ነበር
የጽዮን አገልጋዮች በእግዚአብሔር የሕጉ ታቦት ፊት መለከት ይነፉ ነበር ።በዚህም ዕለት ይኸውም የካቲት ሃያ ሦስት ቀን በሮማውያንና በኢትዮጵያውያን መካከል ከፍተኛ ጦርነት ኾነ በዚህም ጊዜ በሰማይ ታላቅ ተአምር ተደረገ።ማለት የቀስተ ደመና ምልክት ታየ ከዚያም ደመና ውስጥ መልኩ አረንጓዴ የመሚስል ጢስ ይወጣ ነበር ።ከዚህም ጢስ ውስጥ እንደ ክረምት ነጎድጓድ ያለ ድምፅ ተሰማ ።
ከዚህም የነጎድጓድ ድምፅ የተነሣ በሮማውያን ወታደሮች ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤና ሽብር ኾነ ለመዋጋትም አልቻሉም። ይልቁንም ኃያሉ ገባሬ ተአምር ቅዱስ ጊዮርጊስ በአምባ ላይ ፈረስ ተቀምጦ ከነፋስ ሩጫ ይልቅ እየተፋጠነ በዓየር ላይ በተገለጸ ጊዜ በግምባራቸው ፍግም እያሉ ወደቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ አምላካቸው ሊረዳቸው መጣ እንግዲህ ማን ያድነናል አሉ ፤ ምድር ጠበበቻቸው በዚህም ጊዜ የኢትዮጵያ ሠራዊት የሮምን የጦር ሠራዊት ፈጁዋቸው ። የተረፉትንም ማረኳቸው ፈጽመውም እስኪአጠቸፏው ድረስ በሮማውያን ላይ በእግዚአብሔር ሥልጣን የኢትዮጵያውያን እጅ እየበረታች ሄደች።
ከዚህም በኋላ የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ሣህለ ማርያም በእግዚአብሔር ኃይልና በተአምራት አድራጊው በቅዱስ ጊዮርጊስ ተራዳኢነት የሮማውያንን የጦር ሠራዊት ድል አድርጎ የድል አክሊል ተቀዳጀ ።
ስለዚህም በዳዊት የምስጋና ቃል የድል የዘውድ ያቀዳጀኝን እግዚአብሔርን ባለ ዘመኔ ኹሉ አመሰግነዋለሁ ለፈጣሪዬም እዘምራለሁ አለ ሕዝቡም ኹሉ በክብር ከፍ ከፍ ያለ እግዚአብሔርን በፍጹም ምስጋና እናመሰግነለዋን የሮማውያንን ኃይል ተቀጥቅጦ አጥፍቷልና ሠረገሎቻቸውንም ሠባብሯልና ፤ ሠራዊቱንም ኹሉ በምድር ላይ በትኗልና እያሉ አመሰገኑ ።በፈጣረው በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል በጦርነቱ መካከል የረዳቸውን ቅዱስ ጊዮርጊስንም በፍጹም ማድነቅ አደነቁት።
የሮማም የጦር ሠራዊት በኢትዮጵያውያን ፊት ተዋረዱ ዳግመኛም በኢትዮጵያ ላይ ራሳቸውን ከፍ ከፍ አላደረጉም ።በምኒልክ ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያ ከጦርነት ለዓርባ ዓመት ያህል ።
የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ከዓድዋ ጦርነት ከተመለሰ በኋላ አዲስ አበባ በምትባለው ከተማው መካከል በቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ቤተክርስቲያን አሠራ ስሟንም ገነተ የጽጌ ብሎ ሰየማት ። ቅዱስ ጊዮርጊስ በጦርነት ቦታ ኹሉ ይረዳው ነበርና ።
ልመናው ክብሩ በኛ ለዘለለዓለሙ በዕውነት ይደርብን።
3 views09:16