2023-04-12 07:07:47
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በስምዖን ዘለምጽ ቤት የአልባስጥሮስ ሽቶ ይዛ መጥታ ከክርስቶስ እግር ሥር ተደፍታ በዕንባዋ ንስሐ ስለገባችው ሴት እንዲህ አለ
ኃጢአተኛዋ ሴት እያለቀሰችና ደረቷን እየመታች እንደዚህ አሰበች
፨ ነፍሴ ሆይ "እንግዲህ ሰው እንደመጣለት በሚናገረው ቃል ሁሉ በፍርድ ዕለት ይፈረድበታል "ላለው ዓለምን ሁሉ ለሚዳኘው ምን ትመልሺለታለሽ?
፨ ነፍሴ ሆይ ከእውነት ፈራጁ ትዕዛዝ ሲመጠብሽ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወደ ሚሆንበት ትሉ ወደ ማያንቀላፋበት ውርጩ ወደ ማይሞቅበት እሳቱ ወደ ማይጠፋበት ወደ ጨለማ ዳርቻ ሲወስዱሽ እንዴት ትሆኛለሽ ?
፨ ነፍሴ ሆይ በዚህች ሰዓት የሚረዳሽ ማን ነው ንስሐ በሌለበት ነፍስ ሁሉ በተናቀችና በተጣለች ጣርና ጩኸት ባለበት ጊዜ ማን ይለምንልሻል ?
፨ ነፍሴ ሆይ በዚህ በሚያልፍ ዓለም ነገር ይልቁንም ለኃጢአት ሥራ የሚያፈቅሩሽ የሚጠቅሙሽ ይመስልሻል ?
፨ ዓይኖቼ ሆይ የሞት ጥላ ሲሸፍናችሁ ኩል ይጠቅማችኃልን ? አፌ ሆይ መራራ የሞት ጽዋ ስትጠጪ ይህ በየአይነቱ ምግብ ይጠቅምሻልን? ብዙ ጎረምሶች የደለልኩበት ምላሴ ሆይ ሞት ዝም ሲያሰኝ እንዴት ትሆናለህ ዓለምን ሁሉ ለሚዳኘው ምን ልትመልስለት ትችላለህ ?
፨ በቀለም ዓይነትና በቀለበቶች ታጌጡ የነበራችሁ እጆቼ ሆይ የሞት ልብስ የተንደላቀቅህ ሥጋ ሆይ በክብር ንጉሥና የሥራህን ክፋት ሊሰሙ በቆሙት ስፍር ቁጥር በሌላቸው መንፈሳውያን መላእክት ፊት ራቁትኸን ስትቆም እንዴት ትሆናለህ ?
፨ ነፍሴ ሆይ በዚያ በአስፈሪ አደባባይ የሚረዳሽ አለን እዚያ የትል ምግብ የዚኸ ዓለም ምግብ ይጠቅምሻልን ሁል ጊዜ ወደ ዝሙት የምትሮጡ እግሮቼ ሆይ ሞት ሲያሥራችሁ እንዴት ትሆናላችሁ ልታመልጡ ትፈልጋላችሁ ግን አይቻላችሁም
ነፍሴ ሆይ በዚህ ዓለም ያገኘሽው ድሎት ምን ይጠቅምሻል ?
መዳኛ እንዴት እንደምታገኘ ግን አላወቀችም ሆኖም የሰውን ልብ የሚያውቅ የጴጥሮስን መራራ ለቅሶ የተቀበለ ንስሐውን ተቀብሎ ወደ ክብሩ ያስገባው የቀራጩ ጩኸትም ያልተሠወረው እግዚአብሔር በንጹሕ ልቦና በብሩሕ ሕሊና ወደ እርሱ እንደተመለሰች አወቀ
/ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ዘስሙን ቅድስት/
412 viewsedited 04:07