2023-04-08 12:55:07
ይድረስ ለሶፍያ ሽባባው።
ከሁለት ቀናት በፊት "ይድረስ ለኦርቶዶክስ ጳጳሳትና መምህራን!!" በሚል በገጽሽ የለጠፍሽውን ልጥፍ ከነተሰጠው አስተያየት ጭምር አነበብኩት። በዋናነት ሐሳብሽ "እንደዚህ ናችሁና እንደዛ ብትሆኑ" የሚል ከፍረጃ ተነስቶ በጣም በጥንቃቄና በጥበብ የተጻፈ መሆኑን ጽሑፉ በራሱ ይናገራል። የመልእክትሽ ዋና ዓላማም "ይህንን አድርጉና ወደ ኦርቶዶክስ መልሱን!!" በሚል በመግቢያው ተገልጿል። በአጠቃላይ ጥንቃቄ ለተሞላው በጨዋ ደንብ ለቀረበ ሐሳብሽ አድናቆትና ምስጋና አለኝ።
ሰዎች ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሚርቁበት ያልሽው ምክንያት ዘርዝረሻል። በስተመጨረሻም ይሁንልኝ ያልሽውን እርማት እንዲህ በማለት" የአለም ሁሉ መድሀኒት ለሆነው ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የሚገባውን ክብርና ምስጋና እውቅና ትስጥ ያኔ ወደ ኦርቶዶክስ ከሚመለሱት ቀዳሚዋ እኔ እሆናለሁ!" ሐሳብሽን ቋጭተሻል።
ይህን ምላሽ የምጽፍልሽ አንድ ታናሽ አገልጋይ የደብረሊባኖስ ገዳም መነኩሴ ስሆን የማገለግለውም በነገረመለኮት ዩኒቨርስቲ የአንጻራዊ ነገረመለኮትና የሥነ ልቡና መምህር ሆኜ ነው።
በቅድሚያ ጽሑፍሽ "ጉድለት" ወይም "ደካማ ጎን" ብሎ በፈረጀው እሳቤ ላይ የሚያጠነጥንና እንደመፍትሒ ጠቁሞ የሚቋጭነው። በዚህም የቤተክርስቲያኒቱን ጠናካራ ጎን ማንሳት አልተፈለገም አሊያም ዕውቅና መስጠትን ሳይሻ በአሉታዊ ጀምሮ በአሉታዊ ይጨርሳል። ከዚህም በመነሳት ለቤተክርስቲያኒቱ ያለው ምልከታ አንድ ጎን ብቻ መሆኑ ነው።
በቅድሚያ ግለሰቦች ፈጠሩት ላልሽው ችግር ቤተክርስቲያኒቱን ተጠያቂ አድርገሽ መፈረጅሽ አግባብ አይደለም። እንዳልሽው ችግሩ ካለ ግለሰቦች በየትኛው ሥፍራ ተመሳሳይ አካሔዶችን ሊከተሉ ይችላሉ። ነገር ግን እንደቤተክርስቲያን ከኃላፊነት አንጻር ተጠያቂ ለማድረግ በቅዱስ ሲኖዶስ ወስና የተቀበለችው ሐሳብ መሆን አለበት።
ለዛሬ በዋናነት መልስ የሚያስፈልገው የተዛባ ምልከታሽን ሰፋ አድርጌ በማየት ልቋጭ። በሐሳብስ በስተመጨረሻ በሰፈርሽው ሐሳብ " የአለም ሁሉ መድሀኒት ለሆነው ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የሚገባውን ክብርና ምስጋና እውቅና ትስጥ ያኔ ወደ ኦርቶዶክስ ከሚመለሱት ቀዳሚዋ እኔ እሆናለሁ!" ብለሻል። በዚህም ቤተክርስቲያኒቱን ከውጪና በጠላት አፍ ከሚነዛባት ሱሑት እሳቤ ተነስተሽ የግምትሽን ሐሳብ ከመሠንዘር በቀር ጠጋ ብለሽ ከውስጥ እንዳላወቅሻት ማሳያ ነው። ሐሳብሽን አንድ በአንድ ማየትና ለተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያለሽን የተዛባ ምልከታ የሚያረጋግ ጠውን እሳቤ ላንቺም ስለምትናፍቂያት ቤተክርስቲያን ለማወቅና የተዛባውን ምልከታሽን ለማስተካከል የሚረዳሽን እውነት ባጭሩ ልግለጽ።
ስለኢየሱስ "የሚገባውን ክብርና እውቅና ትስጥ" ብለሻል። ይኽ አስተያየት ለተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አይገባትም። ስለኢየሱስ ክርስቶስ የሚገባውን ክብር በዓለም ላይ ከተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በቀር ሌላ የሰጠና የሚሰጥ ያለ አይመስለኝም። እስኪ ከመጠሪያዋ ጀምሮ እንይ። መጠሪያዋ ተዋሕዶ ነው። ይህ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው በመሆን ለዓለም ቤዛ መሆኑን የዓለም መድኃኒት መሆኑን የሚገልጽ ነው። የተመሠረተችው በእርሱ ነው። ዛሬም ሁለንተናዊ ሕይወቷ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስሙንም ከዓመት እስከዓመት ሳታቋርጥ በኪዳን በቅዳሴ በሳህታት በማኅሌት እንዲህ እያለች ታመሠግነዋለች።
“ኢየሱስ ክርስቶስ ጥዑመ ስም ለዘይጼውዖ
ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብስተ ሕይወት ለዘይበልዖ፤
ኢየሱስ ክርስቶስ ጽዋዐ መድኀኒት ለዘይሰትዮ፤
ኢየሱስ ክርስቶስ በግዐ መድኀኒት ለዘይሠውዖ ፤
ከመ ይባርኩነ ይፈኑ አርዳኦ፤
ለጸባኢነ ይጽብኦ ወልታሁ ነሢኦ”
ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚጠራው ስሙ ጣፋጭ ነው፤
ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚበላው የሕይወት እንጀራ ነው፤
ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚጠጣው የመድኃኒት ጽዋ ነው፤
ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚሠዋው የድኅነት በግ ነው፤
ይባርኩን ዘንድ ደቀ መዛሙርቱን ይላክ፤
ጋሻውን አንሥቶ የሚጣላንን ይጣላው።"
እያለች በየእለቱ ቤተ ክርቲያን ስሙ መብል መጠጥዋ ፣ክብሯ ፣ መድመቂያዋ ፣ማንነትዋ እና ሁሉ ነገርዋ እርሱ እንደሆነ ትመሰክራለች። የትኛውም ቅዱስ ቢታሠብ የትኛውም ሰማእት ቢዘከር ኢየሱስ ክርስቶስን አክብሮ በመክበሩ ስለአርኣያነቱና በክርስቶስ ኢየሱስ ስላገኘው ሰማያዊ በረከት እንጂ ከክርስቶስ ተነጻጽሮ አይደለም።
ኢየሱስ ክርስቶስ ስትጠራው እንኳ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብላ ነው። በዚህም ጌትነቱን አዳኝነቱን አምላክነቱንና ክርስቶስነቱን ሳትመሰክር ስሙን አትጠራም። ይህም በዚህ ልክ ከብሮ የሚጠራ ሌላ የለምና ክብሩ ከፍ ያለ አቻም ሆነ ተመሳሳይ የሌለው መሆኑን ያሳያል። ካነሳሽው አይቀር ርስቶስ ኢየሱስን እንዴት እንደምታከብር በደንብ ማየት ከፈለግሽ ውሳጣዊ ዓይንሽን መክፈት ይኖርብሻል።
በዓመት የሚከበሩ በዋናነት የሚታወቁ ዘጠኝ ዐበይትና ዘጠኝ ንዑሳን በዓላት አሉ። ከዘጠኙ ዐመታዊ ዐበይት ወይም ዋና በዓላት መካከል 8 በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ተግባር መዘከሪያ ሲሆኑ አንዱ ብቻ ርደተ መንፈስ ቅዱስን አስመልክቶ በስሙ የተሰየመ መታሰቢያ ዕለት ነው። በዘጠኙ ትይዩ ዘጠኝ ንዑሳን በዓላት ሲኖሩ ዘጠኙም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ጉዞ መታሠቢያ ዕለታት ናቸው።
በዓመት ውስጥ 7 አጽዋማት ሲኖሩ 6 ቱ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ከአማኞች የሚሰጡ የምላሽ መንፈሳዊ ተግባራት ሲሆኑ አንዱ ስለእመቤታችን ክብር ለበረከት የሚጾም ነው።
በወር ውስጥ ረቡዕ በጌታየ በኢየሱስ ላይ ምክረ አይሁድ ስለተፈጸመበት አርብ ስለተሰቀለ እሑድ ሞትና መቃብርን ድል ነስቶ የተነሳባት የጌታ ቀን ሆና ስትታሠብ ወር በገባ በ06 ስሙ ኢየሱስ ተብሎ የተጠራበት በ10 ነገረ መስቀሉ የሚታሠብበት 27 እርጥብ መስቀል ተሸክሞ መንገላታቱ ና ስቃዩ የሚታሰብበት በ28 እግዚአብሔር ሰውን መታረቁ ክርስቶስ ወይም አማኑኤል በሚለው ስሙ የሚታሰብበት ሲሆን ወር በገባ በ29 ደግሞ ሰው ወደ አምላክነቱ ዙፉን ለመውጣት በመፈለግ የሠራውን ስሕተት፤ እግዚአብሔር ወደ ሰውነት በመውረድ ለማረም በከብት በረት ስለኛ ድህነት የሰው ሥጋ ተዋሕዶ በቤተልሄም በግዕዘ ሕጻናት ያለቀሰበት የልደቱ መታሠቢያ ዕለታት ናቸው። በዐጠቃላይ በወር ውስጥ ለ 17 ቀናት በዋናነት የሚታሠብ ሲሆን ከወር እስከወር ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ተብሎ በኪዳንና በመስዋት ይታሠባል።
በእርግጠኝነት በዚህ ልክ ክርስቶስን የሚያከብር የእምነት ተቋም ቢኖር ብቸኛዋ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ናት። ለመገመት ያህል አንቺ በምትሳተፊበት እምነት ቢታሠብ በወር ከ4 ቀናት እንደማይበልጥና እሱም በትርፍ ቀን ተብሎ እንጂ እንደተዋሕዶ የጌታ ቀን ተብሎ የተሰየመ ሰንበት ኖሮኣችሁ አይመስለኝም።
በሳምንት እንደዚሁ 3 ቀን ረቡዕ አርብና እሑድ ከላይ እንደገለጽኩት በተለየ የሥርዓተ አምልኮ ክንዋኔ ሲታሰብ ከሳምንት እስከሳምንት ኢየሱስ ክርስቶስ ተብሎ በኪዳን ቀስብሐተ ነግህ እና በመስዋእት ይታሠባል።
እነዚህ ሁሉ ተግባራት በስሙ መከናወናቸው ለአምልኮና ከነገረ ድህነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ መሠረት ስላላቸው ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል። “ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤”
— ፊልጵስዩስ 2፥12
402 views09:55