2023-03-10 16:57:08
"እኔን በጣም እያሳሰበኝ ያለው እና አጥብቄ የምጸልይበት ጉዳይ ቢኖር አጠቃላይ የሚዲያ ጉዳይ፣ ይዘቱ እና በአማኞች ነፍስ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ነው። ምክንያቱም ዲያብሎስ አምላክ ላይ በትክክል ውጊያ የከፈተበት ቦታ ሚዲያ ነውና።"
/16ኛው የሩሲያ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ፖፕ ቄርሎስ/
ፖፕ ቄርሎስ በኮሚኒዝም ዘመን እና ከእርሱም በኋላ ከፍተኛ መቀለጃ እና መሳለቂያ ሆና የነበረችውን ቤተ ክርስቲያናቸው ወደ ከፍታ ለመውሰድ እና የጠፉ ልጆቿን መልሳ ለመሰብሰብ እንድትችል በቤተ ክህነታቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ የመዋቅር እና የአሠራር ለውጥ በማምጣት ይታወቃሉ። ከዚህ ሁሉ በላይ በዓለም ጭምር የሚደነቁበት ግን በሚዲያ አጠቃቀም ላይ ባመጡት አዲስ ስትራቴጂ ነው። መዋቅር እና አሠራር ከመዘርጋታቸውም በፊት ስለዚህ ሁኔታ ታላላቅ ንግግሮችን አድርገው ነበር። ከላይ የጠቀስኩትም የዚሁ ንግግራቸው አካል ነበር።
ፖፕ ቄርሎስ ቤተ ክርስቲያናቸው የትልልቅ ሚዲያ ተቋማት ባለቤት መሆን ያለባት መሆኑንም ሲያስረዱ እንዲህ ብለው ነበር።
"ዐለማዊ ጋዜጠኞች ትንሣኤንና ልደትን ጠብቀው ኦርቶዶክስን የሚጠሩበት ወቅት አልፏል። ዛሬ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ በየጋዜጣው ገጾች ፣ በሬዴዮኖች፣ በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ በየኢንተርኔቱም ይወጣል። ልክ ነው ይህ ደስ ያሰኛል። ሆኖም ትልቅ ኃላፊነት እንደሚጠብቀን እና ለሚዲዮች በመተባበር ስለራሳችን ለመናገር በንቃት መሳተፍ እንዳለብን የሚጣራ ነው። ገለልተኛ ሆነን ከቆምን ጋዜጠኞች ስለቤተ ክርስቲያናችን እና ስለ እምነታችን ራሳቸው የመሰላቸውን ምስል ፈጥረው ለማኅበረሰቡ ያሰራጫሉ። ያለ እኛ ተሳትፎ ከሆነ ይህ እነርሱ የሚፈጥሩት ምስል አንድ ገጽ ይሆናል፣ ከባሰም የተጣመመ እና ሐሰተኛ ሊሆን ይችላል"
እኒህ አባት ሌላም ጊዜ "እኛ ስለቤተ ክርስቲያናችን እና ስለ እምነታችን ትክክለኛውን እና ተገቢውን የማንናገር ከሆነ ሌሎች ስለ እኛ የሚናገሩት እውነት ተደርጎ ይወሰዳል" ብለዋል።
በዚህ ዘመን ስለ ሚዲያ አስፈላጊነት ማስረዳት የሚያስፈልግ ላይሆን ይችላል። ልማታችንም ጥፋታችንም ከእርሱ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ መሆኑ ግልጽ ከሆነ ከራርሟልና።
የእኛ ቤተ ክርስቲያንም ዘግይታም ቢሆን የሚዲያውን ዳዴ ጀምራዋለች። ይህ ውጤታማ የሚሆነውና እንደሌሎቹ ለላቀ ግብ የሚደርሰው ግን ሁላችንም የድርሻችን ስንወጣ ነው።
አንድ መክሊቱን እንደቀበራት ክፉ አገልጋይ እንዳንወቀስ ከፈለግን ያችኑ መክሊት ለተገቢው አካል እንስጥ። ጌታ ክፉውን ባሪያ "ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበት የምትሰበስብ መሆንህን ስለማውቅ" (በፈለግኸው አድረህ ትሠራለህ ብዬ ነው) ብዬ ነው ብሎ ሲያመካኝ እንደዚያ ብለህ ካሰብክ ለዚያ አድሮበት ይሠራል ላልከው ሰው ለምን አልሰጠኸውም ሲል የፈረደበት እንዳይደርስብን የሚሠሩትን እድናግዝ በታላቅ ትሕትና እጠይቃለሁ።
ወዳጄ ገንዘብ ጥየቃው በዛ፣ ሰሞኑን ለቦረና እና ለመቄዶንያ፣ ለተፈናቃዮች እና ለችግረኞች፣ ለአጥቢያዬ ሕንፃ ግንባታ እና ነፍስ አባቴ ለጠየቀኝ፣ ለገዳም እና ... አሁን ደግሞ ለሚዲያ፤ አልበዛም ወይ እያልክ አትቁጠር አደራህን። ይልቁንም የምሰጠው አታሳጣኝ ፣ የሚለመንላቸው ውስጥ ከመሆን አድነኝ እያልህ የተቻለህን ብቻ አድርግ እንጂ እንዳታማርር። እንኳን እኛ እርሱ ከሰጠን ላይ የምንሰጠው ይቅርና ስለምንጠይቀው እና ስለሚሰጠን ብቻ ሳይሆን ሳንጠይቀውም ስለሚያደርግልን ነገር እግዚአብሔርም እኛን አላማረረምና ሳንማረር የተቻለንን እናድርግ።
889 views13:57