2023-02-08 18:45:09
== የእንታረምና የእንለወጥ ጥያቄዎች*** ==
የንጉሠ ነገሥቱ ዙፋን ላይ በግርማሜ ወንድማማቾች ተሞክሮ የነበረው መፈንቅለ መንግሥት በከሸፈ በጥቂት ቀናት ወስጥ ንጉሡን በአካል ሊያገኝ አንድ ሰው ከኒውዮርክ ተሳፍሮ አዲስ አበባ ገባ። ግለሰቡ ደራሲና አምባሳደር ሀዲስ አለማየሁ ነበሩ። አምባሳደር ሀዲስ አለማየሁ በወቅቱ በኒውዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው ነበር የሚያገለግሉት። የደብረ-ማርቆስ ተወላጁ ሀዲስ ሚኒሊክ ቤተ-መንግሥት ውስጥ ገብተው ከንጉሡ ዙፋን ቀረቡ። ከወገባቸው አጎንብሰው እጅ ከነሱም በኋላ፤ «እንኳን ግርማዊነትዎን እና ዙፋንዎን እግዚአብሔር አዳነ» በማለት ንጉሡ ከሥዒረ መንግሥቱ መዳናቸው ደስ እንዳሰኛቸው ገለጡ።
ነገር ግን ሀዲስ ቤተ-መንግሥት የሄዱት ለዚህ ብቻ አልነበረም። ከዚያ ይልቅ ሀገሪቱ በተያያዘችው ኋላ-ቀር የአሥተዳደር ሥርዓት ከቀን ወደ ቀን ወደ ከፋ ቀውስ እያዘቀዘቀች መሆኗ ታይቷቸው አዲስ የሥርዓት ማሻሻያ ለውጥ [ሪፎርም]በግዛተ-አጼው ውስጥ እንዲካሄድ የሚጠይቅ ማስታወሻ አዘጋጅተው ለንጉሡ በእጃቸው ለመስጠት ነበር። ንጉሡ የተሰጣቸውን ማስታወሻ ገለጥ ገለጥ አድርገው ማንበብ ጀመሩ።
የማስታወሻው መግቢያ ለንጉሡ ውዳሴ የሚያዥጎደጉድ ነበር፣ ንጉሡ ማስታወሻው ላይ አይናቸው ባቀረቀረበት በድንገት በብስጭት ቱግ አሉ። «እኛ ከንቱ ውዳሴ እንወዳለን እንዲህ ብለህ ያቀረብኸው? እኛ እኮ እናውቀሀለን» ብለው በቁጣ ተናገሩ። ደራሲ ሀዲስም ፈራ ተባ እያሉ «እኔም እኮ አውቅዎታለሁ! [ይሄን በማለቴ] ሊያስሩኝ፣ ሊገርፉኝ፣ ሊገድሉኝ እንደሚችሉ አውቃለሁ» ብለው መለሱላቸው።
ይህ የሐሳብ ልውውጥ በንጉሡና በአምባሳደሩ መካከል ሲካሄድ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የአሥተዳደር፣ የሙስና፣ የልማት እና የጸጥታ ችግሮችን የተጋረጠችበት ጊዜ ነበር። ንጉሡና አሥተዳደራቸው ደግሞ ችግሮቹን ለመፍታት ብቻም ሳይሆን ለመረዳትም የተሳናቸው ይመስል ነበር።
የንጉሠ ነገሥቱ የሥልጣን ዘመን እያከተመ መኾኑ የታወቀው ቢያንስ ከ1966ቱ ዓብዮት 10 እና 15 ዓመታት በፊት ነበረ። ግዛተ-አጼው በተለያዩ ወቅቶች ይነሱበት የነበረው የከተማና የገጠር አመጾች ሕዝቡ በሥርዓቱ ላይ የነበረው ተስፋ እየተንጠፋጠፈ መሄዱን እያመላከቱ ነበር። የንጉሡና አሥተዳደራቸው እያደረ ከመሻሻል ይልቅ እየተበላሸና እየቆረቆዘ የሚሄድ አካሄድ ያልጣማቸው አምባሳደር ሀዲስ ሀገሪቱ የገጠሟትን ችግሮች በፈርጅ በፈርጅ በመለየት ሊወሰድ ይገባል ያሉትን መፍትሄ ነበር በማስታወሻቸው ያስቀመጡት።
ይህ ለሥርዓቱ ቅርብና ቤተኛ የሆነ ሰው ያቀረበው የ«እንሻሻል» ማስታወሻ በንጉሡም ሆነ ባለሟሎቹ ይህ ነው የሚባል ግምት ሳይሰጠው ቅርጫት ውስጥ ተጣለ። በንጉሡ አሥተዳደር ውስጥ ኾነው ግዛተ-አጼው እንዲሻሻልና ከእንከኖቹ እንዲታረም ሐሳብና ማስታወሻ ያቀረቡት አምባሳደር ሀዲስ ብቻ አልነበሩም። ንጉሡን ከ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት የታደጓቸው ጀነራል መርእድ (የወቅቱ መከላከያ ሚኒስትር)፣ ልዑል ራስ አስራተ ካሳን ጨምሮ አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ፣ ጀነራል አብይ አበበ ወዘተ አሥተዳደራቸው እንዲሻሻል የሚጠይቅ ይፋዊ ማስታወሻ ለንጉሡ አቅርበዋል።
የእነዚህ ግለሰቦች ጥያቄዎች በቅንነት የተሞሉና ከጀርባቸው የተለየ ዓለማ የነበራቸው አልነበሩም። የሁሉም ማስታወሻዎች ጭብጥ የንጉሡ አሥተዳደር ሕገ-መንግሥቱን ከመለወጥ ጀምሮ ግዛተ-አጼው ዘመኑን፣ የኅብረተሰቡን ንቃተ ሕሊና፣ ፍላጎትና አሁናዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ ለውጥ እንዲያመጣ የሚጠይቁ ነበሩ። የእነዚህን ሁሉ ሰዎች ውትወታ ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉት ንጉሡ በ1966 በተነሳ አብዮት ንግሥናቸውንና ለዘመናት ይዘውት የቆዩትን የጥቅም ሞኖፖሊ ከእነቤተሰባቸው አጡ። አሳቸወም ያ ሁሉ ክብርና ሞገስ ተቀምተው በመፀዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ ተቀበሩ።
የንጉሡ ታሪክ ለማሳያነት ቀረበ አንጂ የብዙ መንግሥታትና ተቋማት ታሪክ ተመሳሳይ ነው። ዘመንና ጊዜ እየተቀየረ ሲሄድ የኅብረተሰብ አኗኗር፣ ፍላጎት፣ የመብት ጥያቄ ወዘተ አብሮ እየተለወጠ ይሄዳል። ሕዝብ አይናቅም። ሕዝብ የአሥተዳደርም ሆነ የአካታችነት ጥያቄ ሲያነሳ ወደ ጎን መግፋት መዘዙ ብዙ ነው። የንጉሡ መንግሥት ተሰባበሮ የወደቀው ራሳቸው ንጉሡና አሥተዳደራቸው «ኃላፊነትን ለመቀበል አልደረሰም» ባሉት ሕዝብ ነበር። ሕዝብ ማድመጥ አይጎዳም!
*** የአብዮቱን ወር ወርሃ የካቲትን አስመልከቶ የሰፈረ ማስታወሻ
633 viewsHusen Mohammed, 15:45