2023-04-07 18:14:39
ጋዜጠኛ አባይ ዘውዱ “ሁከት እና ብጥብጥ” የሚል የሀሰት ክስ ቀረበበት።
‹የጦር መሳሪያዎችን በመያዝ ተልዕኮ ተቀብለው የመንግስትስ ከፍተኛ አመራሮችን እና ታዋቂ ሰዎች ላይ እርም ለመውሰድ ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት ህገመንግስቱን እና ህገመንግስታዊ ስርአቱን በሀይል ለመናድ...› አቃቢ ህግ
‹የቀረበብን ክስ ሳይሆን ስድብ ነው። ምሁራንን በእንዲህ አይነት ተራ ወንጀል መጠርጠር አለማወቅ ነው› የህሊና እስረኞች
የአማራ ሚዲያ ማዕከል
መጋቢት 29 2015 አ/ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
የአማራ ሚዲያ ማዕከል ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ዓባይ ዘውዱ ከሌሎች 8 ሰዎች ጋር የሀሰት ክስ ቀረበበት።
በትናንትናው ዕለት መጋቢት 28 2015 ዓ/ም በፖሊሶች ለጥያቄ እንፈልግሀለን በሚል የተወሰደ ሲሆን ከሰአት በኋላ አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት ከሌሎች 8 የህሊና እስረኞች ጋር “ሁከት እና ብጥብጥ” መፍጠር በሚል የሀሰት ውንጀላ ቀርቦባቸው ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ፋይል የተከፈተባቸው የህሊና እስረኞች
1 ሰይፈ ተስፋዬ ተፈሪ
2 ማስረሻ እንየው ታረቀኝ
3 ታደሰ ወዳይነው ተሰማ
4 ታደለ መንግስቱ ጉዳይ
5 ጌታቸው ወርቄ አያሌው
6 አንደበት ተሻገር ታደሰ
7 አለልኝ ምህረቱ አድገህ
8 አባይ ዘውዱ ደመቀ
9 ዶክተር አሰፋ ደሞዜ ሲሆኑ
አቃቢ ህግ ያቀረበው የሀሰት ውንጀላ “የራሳቸውን የፖለቲካ አላማ እና ፍላጎት ለማሳካት አስበው የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀምና በተለያዩ መንገድ በመገናኘት ህገወጥ አደረጃጀት በመፍጠር ወጣቶችን ለወንጀል ተግባር በመመልመል እና
በማደራጀት ወጣቶችን ለአመፅ በማነሳሳት በሀገሪቱ መረጋጋት እንዳይኖር ግጭት እንዲነሳ በማሰብ በአዲስ አበባ ከተማ እና በተለያዩ ቦታዎች በመንቀሳቀስ በህገወጥ መንገድ ወጣቶችን በህቡዕ እየመለመሉ በማደራጀት የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በማስታጠቅ በተለያዩ ቦታ ከሚንቀሳቀሱ ለአመፅ ተግባር ከተደራጁ ኢ መደበኛ ኃይሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር
የመለመሏቸውን ወጣቶች ወታደራዊ ስልጠና እና የተኩስ ልምምድ እንዲወስዱ በማድረግ በህገወጥ መንገድ ቡድኑን ከሚመሩ አመራሮች ጋር በመገናኘት በአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች እና በአዲስ አበበአ ከተማ ህዝብ በመንግስት ላይ አመኔታ እንዳይኖረው ለማድረግ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በመያዝ ተልዕኮ ተቀብለው የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችን እና ታዋቂ ሰዎች ላይ እርም፡ ለመውሰድ ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት
ህገመንግስቱን እና ህገመንግስታዊ ስርአቱን በሀይል ለመናድ ካልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመንቀሳቀስ ላይ እያሉ በተደረገ ክትትል ከቀን 26/07/15 ዓ/ም ጀምሮ በቁጥጥር ስር ውለው በምርመራ ክፍላችን በ እስር ላይ ይገኛሉ” ይላል በሀሰት የተቀነባበረው ክስ።
በሀሰት የቀረበባቸው ውንጀላ የሰሙት የህሊና እስረኞችም ለፍርድ ቤቱ የሚከተለውን ብለዋል
። መንግስት ከሕዝብ አመኔታ የሚያጣም ሆነ የሚያገኘው በሚሰራው ስራ እንጅ ፌስቡክ ላይ በሚለጠፍ ሀሳብ አይደለም፣
ህገመንግስት የሚናደውም የሚፀናውም በራሱ የመንግስት አስተዳደር እንደሆነ፣ እኛ በሀሳብ ሞግተን ማሳመን የምንችል እና የተሰራ ሀሳብ ለሚያቀርብልንም ሀሳቡን ለመቀበል ጭንቅላታችን ዝግጁ ስለሆነ የብጥብጥ ስራ ላይ አንሰማራም፣
ለአማራ ህዝብ ከታሰበለት የአማራ ምሁራንን ለቃቅሞ ማሰር ሳይሆን የሚገደለውን አማራ እንዳይገደል ማድረግ እንዳይፈናቀል ማድረግ ነው፣በጥቅሉ እኛ ላይ የቀረበው ክስ ስድብ ነው ከምንለው በቀር እንዲህ ያለ ለከስካሳ ስራ ላይ አንሰማራም። ከሀሳባችንም የለም ።
ምሁራንን በእንዲህ አይነት ተራ ወንጀል መጠርጠር አለማወቅ ነው። የሙያ ስራዎች ሚዲያ ላይ የሚወጡት የሙያ ግዴታችንን ለመወጣት እንጅ ማንንም ለማስጠላት አይደለም።መንግስት የሚጠላውም የሚወደደውም በሚሰራው ስራ ብቻ ነው የሚል ምላሽ ለፍርድ ቤቱ አሰምተዋል።
ፍርድ ቤቱ አቃቢ ህግ ያቀረበውን የሀሰት ውንጀላ በመስማት 14 ቀን የምርመራ ግዜ ፈቅዷል።
ጋዜጠኛ ዓባይ ዘውዱ የአማራ ሚዲያ ማዕከል ጋዜጠኛ ሲሆን በአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሰው መጠነ ሰፊ ጥቃት በመዘገብ ለህዝብ በማድረስ ግፍን የሚያጋልጥ : ለህዝብ ድምፅ የሚሆን ብርቱ ጋዜጠኛችን ነው።
ከዚህ በፊትም ለተደጋጋሚ ግዜ የታሰረ ሲሆን ፀረ አማራ ስርአት የሚመራው መንግስት ጋዜጠኛ ዓባይን በማፈን የህዝብ ድምፅ እንዳይሆን ማድረግን ያለመ አፈና አካሄዶበታል።
የብልፅግና መንግስት የነቁ እና አማራ የተጋረጠበትን የህልውና አደጋ የተረዱ ምሁራንን በማፈን ላይ መጠመዱ አማራን ማሳዳድ መንግስታዊ መመሪያ መሆኑ የሚያሳይ ብሎም ስርአቱ የገባበትም ፍርሀት እና አጣብቂኝ መገለጫ መሆኑ በምሁራን ተገልጿል።
1.3K views15:14