2022-09-26 13:42:58
ፍለጋችን መስቀሉን ይሁን ወይስ ስለ እኛ የተሰቀለው ኢየሱስ ክርስቶስ ?
“እርሱ ግን፦ አትደንግጡ፤ #የተሰቀለውን #የናዝሬቱን #ኢየሱስን #ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም፤ እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ።”(ማርቆስ 16፥6)
የመስቀል ሚስጥር ሲገባን እንደፈለግን ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለን መኖር በቃሉ መመራት እንጀምራለን።
እስኪ በጥያቄ ልጀምር መስቀሉ ወይስ የመስቀሉ ቃል በየትኛው ነው የዳንከው ?
የመስቀሉ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ።
የመስቀሉ ቃል የኃይል ምንጭ ነው
የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት። ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር። ኃይል ነው(1ቆሮ1:18)
መጽሐፍ ቅዱስ ገለጻ መስቀል ምንድነው ?
የኃጢአታችን እዳ የተከፈለበት የወንጀለኛ መስቀያ ነው!
የኢየሱስ ክርስቶስ ስለእኛ ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት በገዳዮቹ የተዘጋጀ መስቀያ እንጨት ነው !
ስለዚህ የሰው ልጅ ደህንነት ሚስጥር ያለው በመስቀያ እንጨቱ ላይ ሳይሆን ስለ ሁላችን ደሙን ባፈሰሰው በመስቀሉ ቃል በኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ከተሰቀለበት እንጨት የተሰቀለልን ኢየሱስ ይበልጣል በፍጹም አይወዳደርም አይነጻጸርም !
“እናንተ #በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን የአባቶቻችን አምላክ አስነሣው፤”(ሐዋርያት 5፥30)
“እኛም በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ባደረገው ነገር ሁሉ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም #በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት።”(ሐዋርያት 10፥39)
“#በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤”
(ገላትያ 3፥13)
በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው።
ኢየሱስ ስለ እኔና ስለናንተ በዚህ በተረገመ እንጨት ላይ ሲሰቀል
እሱ ጻድቅ ኃጢያት የሌለበት ነውር ያልተገኘበት ፍጹም አምላክ ነው።
ነገር ግን ስለእኔ እና እናንተ እርግማን ሆኖ #በእንጨት ላይ ተሰቀለ። በመስቀል ላይ ክቡር ደሙን አፍስሶ ሞተ ተቀበረ በሦስተኛውም ቀን ሲኦልን ድል ነስቶ የሞትን ጣር አጥፍቶ ተነሳ ።
ስለዚህ መስቀል የወንጀለኛ የሚቀጣበት ነው። የኢሱስን መገለጥና መገኘት አዘናግቶ የመስቀሉን መገኘት ማወጅ ከተሰጠን ተልዕኮ ውጭ የሆነ ክህደት ነው ።
ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ህይወቱን ሰጠን። መዳናችንን ያወጅን ሁላችን ሰርተን አልዳንም በመስቀል ላይ ተሰርቶልን እንጂ። ኢየሱስ ክርስቶስ ፍርዳችንን የኃጢያት ዕዳችንን ተሸክሞ ሞታችንን በመስቀል ላይ ሞቶ አዳነን ። በመስቀል ላይ ስለ እኛ ሞተ ። ለመዳን ማመን ያለብን በመስቀል ላይ ሥራችንን ሰርቶ ጨርሶ ያዳነንን ጌታ እንጂ መስቀሉን አይደለም።የዳነው በእርሱ በተሰራልንን በተፈጸመልንን ሥራ ነው።
ጤናማው የመስቀል ሚስጥር መልዕክቱ ሲገባን ጨለማው ሊጋርደን አይችልም። ቤተክርስቲያን ተልዕኮን ይዛ ስራን የጀመረችው ከመስቀሉ ሞት ከዛም ከትንሳኤው በኋላ ነው።በክርስቶስ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የተሰራልን ሥራ አልገባንም ማለት የእግዚአብሔር የማዳን ዓላማው እንዲገባን የሚያስችለንን እምነት የለንም ማለት ነው።
መስቀል ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅን ቅጣት ለመቀበል የምትክነት ስራ ያከናወነበት የወጀለኛ መቅጫ ነው።
“ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን #በእንጨት ላይ ተሸከመ፤ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ።”(1ኛ ጴጥ 2፥24)
እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን እንጂ የተሰቀለበትን አንሰብክም ለትውልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው መሰብክ ያለበት።ቢሆን እንኳ መስቀል መታወስ ያለበት የስቅለት መታሰቢያ በዓል ላይ በፋሲካ ነበር( ዮሐ19:17-18) የመስቀሉ መልዕክት የተሰቀለበትን የሰማይና የምድር ፈጣሪ ኢየሱስ ክርስቶስን የመስቀል ላይ የማዳን የፍቅር ስራ ነው መግለጥ ያለበት።ምክንያቱም በመስቀሉ ላይ የተሰራው ሥራ ለሰው ልጅ ሁሉ የደህንነትን፣ የምሕረት፣ የሰላምና የእርፍት አስደናቂ የመለኮት አጀንዳ ያለበት ነው ።
“እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥”
(1ኛ ቆሮንቶስ 1፥23)
መስቀሉ፡-እግዚአብሔር ወልድ ሥልጣን እያለው ጌታ ሆኖ እያለ፣ በሰው አፍና እጅ በመዋረድ፣ በመሰደብ፣ በጥፊና መመታት፣ በጅራፍ በመገረፍ፣ መስቀል ተሸክሞ በመንገላታት፣የእሾህ አክሊል በመድፋት፣ በምስማር በመቸንከር ፣ እንዲሁም በጦር መወጋት ፣በመስቀል ላይ መጠማት፣ መዘባበቻ በመሆን በስቃይ በመሞት ስለ ሰው ልጆች ሁሉ ኃጢያት ምትክ ሆኖ የሞትን ፍርድ በመስቀል ላይ በመቀበል ከዘላለም ፍርድ ያዳነበት ነው።
እርሱ ግን "ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፣ መከራንም ሲቀበል አልዛተም፡፡ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ"(1 ጴጥ 2፡23)
እንዲያውም "አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው"ለገዳዮቹ ለሰቃዮቹ ማለደላቸው(ሉቃ 23፡34)፡፡
በአዲስ ኪዳን፣ የብሉይ መሥዋዕቶች በክርስቶስ ተተክተዋል፡፡ ሁሉንም የመሥዋዕትነት ዓላማ ያሟላ ፍጹም መሥዋዕት ሆኖ ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቀርቦልናል፡፡
ለእግዚአብሔርም የመልካም መዓዛ ሽታ፣ ለእኛ ደግሞ የኃጢአታችን ማስተስሪያ በመሆን መሥዋዕትም፣ መሥዋዕት አቅራቢም ሆኖ የድነትን ሥራ ሰርቶ ፈጽሞልናል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በመሥዋዕትነቱ ደም የበደላችንን ይቅርታ አስገኘልን፡፡ በእርሱም ሞት ምክንያት የሞት ዕዳችን ተሻረ፡፡ ቅጣታችንንና የእግዚአብሔርን ቁጣ ከላያችን አነሣልን ማለት ነው፡፡ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ለአምልኮ የምንገባበትንም በር ከፈተልን፡፡ድነትን ሰላምና እረፍትንም ሰጠን፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው በክርስቶስ ክቡር መሥዋዕትነት ነው፡፡
እግዚአብሔርም የዘላለምን ህይወት እንደ ሰጠን ይህም ህይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው "ልጁ ያለው ህይወት አለው የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ህይወት የለውም " (1ዮሐ 5÷12)
“ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።”( ዮሐንስ 14፥6) ስለዚህ ጌታ እኔን ፈልጉ እንጂ መስቀል ፈልጉ አላለም ።ጌታ በመስቀል ላይ ለመዳናችን የመሆነውን ሰርቶ ጨርሶታል።
1ኛ.መስቀሉ በክርስቶስ የተሰራልን የድነት ሥራ የተከናወነበት እንጨት ነው። በታረደው በግ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ታርቀን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቁ ሊቀ ካሕናታችን በመሆን እና መሥዋዕት በመሆን ወደ እግዚአብሔር አብ የጸጋው ዙፋን አቀረበን፣ አዳነን ፣ አበቃን (ዕብ 10፡1-10 ዕብ 2፡ 17-18)፡፡
2.መስቀሉ በክርስቶስ በተሰራልን የድነት ሥራ በእኛ ሕይወት የተፈጸመውንም ታላቅ ነገር ይገልጣል - አሮጌው ሰዋችን ከክርስቶስ ጋር እንደተሰቀለ (ሮሜ 6፡ 6፤11)፣ ለኃጢአትም ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር መደረጋችንን ይነግረናል። (1ጴጥ 2፡24)፡፡ በመሆኑም፣ በእኛ በአማኞች ሕይወት ውስጥ የተፈጸመና ሊታይም የሚችል ታላቅ ለውጥ ተሰርቷል አዲስ ፍጥረት ሆነናል፡፡ በአዲስ ሕይወት ለመመላለስ ለአሮጌው ሞተናልና፡፡ (ገላ 2:-20)
ክብር ሁሉ በቀራኒዮ ሥቃይ በደሙ ለዋጀን፣ ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፡፡ አሜን !
22 views10:42