2022-08-11 07:20:47
ለመሆኑ በቤታችን ብዙ መንፈሳዊ ቻናሎች እያሉ ለምን ወደ ቤ/ክ እንሄዳለን ???
ባለንበት ዘመን ይህ የብዙ ክርስቲያኖች ጥያቄ እየሆነ እንደመጣ ያውቃሉ ? ከዚህ የተነሳ እቤቴ ሆኜ አስደናቂ ፕሮግራም በቴሌቪዥን እከታተላለሁ ሲሉ ይደመጣል ። በአንጻሩ ደግሞ ማምለክ ማለት ቤ/ክ መሄድ ብቻ የሚመስላቸው እና ጌታ ጸሎት ቤት ሲመጡ እንጂ ቤታቸውን የማያውቅ ማለትም በቤታቸው ጌታን የማያመልኩ ስፍር ቁጥር የላቸውም። በሌላ መልኩ ደግሞ ሲመቸኝ ቸርች እሄዳለሁ በቤቴም ሲመቸኝ ጊዜ ሲኖረኝ እጸልያለሁ የሚሉ አሉ። ይህ አመለካከት ምን ያህል የሚያዋጣ ነው።
እነዚህ እሳቤዎች በማንኛውም ሰው ውስጥ አራት ወሳኝ ጥያቄዎችን ያጭራሉ ።
1ኛ, ጌታ የሚመለከው በቤት በቻናል ብቻ ነው ወይ ?
2ኛ,ጌታ የሚመለከው በሳምንት አንድ ቀን እሁድ ቸርች ሲኬድ ብቻ ነው ወይ ?
3ኛ,ጌታ የሚመለከው ሲመቸን ጊዜ ሲኖረን ብቻ ነው ወይ ? የሚሉት ወሳኝ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎች ናቸው።
4ኛ, ወደ ቤ/ክ የሚሄደው ለማምለክስ ብቻ ነው ወይ ?
“ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል።”
— ዮሐንስ 4፥21
ጌታ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አለ። እግዚአብሔርን ማምለክ በስፍራ ሁሉ ፣ በጊዜ ፣ በዘር ፣ በሐገር ፣ በቦታ ሁሉ ሳይወሰን ይመለካል ።
" ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤
²⁴ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።"(ዮሐንስ 4:-23-24)
በእውነት እና በመንፈስ ለእግዚአብሔር ይመለካል ለእርሱም ይሰገዳል።
የቤተክርስቲያን መስራችና ባለቤት እግዚአብሔር ነው ።“እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።”
— ማቴዎስ 16፥18
ስለዚህ ቤ/ክ ለመሪዎና ለአገልጋዮች ይጠብቋትና ያገለግሏት ዘንድ አደራ ተሰጥቶአቸው እንጂ ባለቤት አይደለም።
“በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።”
— ሐዋርያት 20፥28
ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር ዓላማው ጠርቶ የለያቸው ቅዱሳን ናቸው። በጌታ አምነው የዳኑ ቅዱሳን ህብረት ነው። ጌታ በሕብረት እንዲያመልኩ ፣ አብረው እንጀራን እንዲቆርሱ ፣ሁሉም በተሰጠው ጸጋ እርስ በርሱ እንዲተናነጽ ታዟል፡፡
ወደ ቤተክርስቲያን የምሄደው ለማገልገል ብቻ ሳይሆን ለመገልገልም ጭምር ነው ። እያንዳንዱ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል በሆነችው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የአካሉ ብልት ነው። በህብረት ፣በአንድነት ፣በፍቅር ፣ በመተጋገዝ ፣ በመረዳዳት የበረታው የደከመውን በመሸከም .... ወዘተርፈ አንዱን አካል (የክርስቶስ አካል በሆነችው በቤተ ክርስቲያን) ለማነጽ በተሰጠው ጸጋ ይተጋል ፣ ያገለግላል ለጌታው ክብር ሌት ተቀን ይሮጣል።
ማንኛው አማኝ ክርስቲያን ነኝ የሚል ሁሉ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ላለው ሁለንተናዊ ዕድገት በርሱ ያለው ጸጋ ለሌሎች መታነጽ እና በሌላው ሰው ያለው ጸጋ እርሱ እንዲታነጽበት የተሰጠ መሆኑን ማወቅ ይኖርበታል ፡፡ በቅዱስ አጠራሩ ያዳንን ጌታ በተሰጠን ጸጋ ምን አንደሰራንበት ይጠይቀናል ። ጸጋው ያለው በኛ ቢሆንም የተሰጠው ለቤ/ክ መታነጽ መሆኑን መረዳት ይኖርብናል ።
ወደ ቅዱሳን ህብረት መምጣት ያለብህ ስለታዘዝክ ነው።እግዚአብሔር ቅዱሳን ሕብረት እንዲያደርጉ አዞአል ። በዚያም በረከትን አዟል ። ደግሞም አንተ አንድ ሰው ነህ በቅዱሳን ሁሉ ያለውን ጸጋ መካፈል ለመንፈሳዊ ሕይወትህ ወሳኝ ነው።
ከቅዱሳን ሕብረት መቅረት ከበረከት መጉደል ነው ። ደግሞም በመጨረሻው ዘመን ይህ እንደ ልማድ እንደሚታይ ቃሉ ይናገራል ።
"ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።"(ዕብራ 10:-24 - 25) ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን የምንተያየት ህብረት ስለሆነ ነው ።
በመጨረሻው ዘመን መገለጫ ምልክቶች ከመሆን ይጠብቀን።በመንም መልኩ መርህ ስለሆነ ከቅዱሳን ሕብረት መጉደል የለብንም።
እግዚአብሔር በቅዱሳን ሕብረት እንደሚገኝ ተስፋንም ሰጠ “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።”
— ማቴዎስ 18፥20 እግዚአብሔር በሚገኝበት መገኘት እንዴት ደስ ያሰኛል ።
በቅዱሳን ሕብረት በመመካከር በመማማር በመተነናነጽ በመበረታታት ከድካም የምወጣበት የምንበረታታበትና ፀጋ የምቀበልበት ቤት ስለሆነ ነው ።
ከቅዱሳን ሕብረት ከሚያስቀሩ ምክንያቶቼ ይልቅ እጅግ የሚጠቅመኝ ሕብረት እንዳደርግ የሚያደርጉኝ ምክንያቶቼ ስለበለጡ ነው፡፡ ቤተክርስቲያንን ሰው ቢመራትም የተመሰረተችው በጌታ ከመሆኑም በላይ የእግዚአብሔር እንጂ የሰው እንዳልሆነች መረዳት ይኖብናል፡፡
ከቅዱሳን ሕብረት ከቤተክርስቲያን የሚበልጥ ቦታ የለም ምክንያቱም እግዚአብሔርን የምናመልክበት፣ ከታዘዘው በረከት የምንካፈለው በዚያ ስለሆነ ። ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ መልካምና ያማረ ስለሆነ ነው። በሕብረት መካከል ለዘላለም የተወሰነውን በረከትና ሕይወት አለ። በክርስቶስ አካል ላይ እኛ ያለ ወንድሞች ህብረት ሙሉ አንሆንም።
ከህብረት መጉደል ከለላ ማጣት ፣ ከበረከት መጉደል ፣ትህዛዝን መተላለፍ ነው ።ከህብረት መጉደል የሌላውን ፀጋ አለመቀበል ነው ።ከህብረት መጉደል ለጠላት መጋለጥ ነው
ከህብረት መጉደል ምኞትን መከተል ነው
" ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው።...
... በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና። "(መዝሙር 133 :-1-4)
1ኛ,ከቅዱሳን ከህብረት ከሚያርቅህ ነገር ራስህን ጠብቅ
ተጠንቀቅ (ዕብራ 10:-24-25)
2ኛ,እግዚአብሔርን በስፍራ ሁሉ አምልክ ኑሮህ ሥራህ ድርጊትህ ሐሳብህ መውጣት መግባትህ ...ወዘተርፈ ያምልከው ! በቤትህም በቤተክርስቲያንም የቤትህ ራስ የሆነው እግዚአብሔር ይመለክ ! (ዮሐንስ 4:-23-24)
3ኛ,የሚመራህ መንፈስ ቅዱስ ምልልስህም ለእግዚአብሔር ክብር ... ይሁን “በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና።”(ሮሜ 8፥14)
4ኛ, የአካል ብልቶች ተለያይተው መኖር እንደማይችሉ እግር ለእጅ አይን ለጆሮ አንዱ ለሌላው አስፈላጊ የሆነውን ያህል አንተም ለሌላው ሌሎችም ለአንተ አስፈላጊ እንደሆኑ እወቅ ። (1ኛ ቆሮ12:-14-26)
53 viewsedited 04:20