2022-09-20 05:35:00
የእግዚአብሔር አብሮነት በልዩነት ያኖራል !
(መዝሙር 124 :- 1 - 8)
የእግዚአብሔር አብሮነት ሚስጥር እጅግ ታላቅ ነው። በክብር፣ በሞገስ፣ በመፈራት ፣ በድል፣ በኃይል ፣ በእረፍት፣ በሰላም፣ በልዩነት ያኖራል ።ይህ ክፍል የእግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆንና አለመሆን ውጤት የሰው ልጅ መናገር እንዳለበት የሚገልጽ መዝሙር ነው ።
ዛሬን በህይወት የመገኘታችን ሚስጥር ዛሬን የማየታችን ሚስጥር የእግዚአብሔር አብሮነት ነው። በምድር ላይ በሕይወት እንድንገኝ የማይፈቅዱ ከአቅማችን፣ ከችሎታችን ፣ከጉልበታችን በላይ የሆኑ የማንቋቋማቸው እጅግ ብዙ ነገሮች አሉ። ነገር ግን ከእግዚአብሔር አብሮነት የተነሳ በምህረቱ፣ በጥበቃው ፣ በፍቅሩ ፣በርህራሔው፣ በቸርነቱ፣ በጥበቃው፣ በፍቅሩ...ወዘተርፈ ውስጥ ተይዘናል ።
ከዚህ የተነሳ ሊያጠፋን የዛተው አላጠፋንም፣ ሊገለን የመጣው አላገኘንም፣የተጠመደልን፣ የተመከረብን፣ የታሰበብን፣ የተወሰነብን አልሆነብንም። ተዘልለን ፣ በሞገስ፣ በመፈራት፣ በክብር የመኖራችን ምክንያቱ የእግዚአብሔር አብሮነት ነው። ምክንያቱም ለሰዎች ቁጣ ዛቻ እና ማስፈራራት ለጥርሳቸው ንክሻ ያላደረገን እግዚአብሔር ነውና።
ወገኖቼ ስንት ጊዜ ለሞት ወጥመድ ተዘረጋ ፣ጦርና ቀስት ተወረወረ ? ያስመለጠን፣ ያዳነን፣ የደረሰልን፣ አቅማችን፣ ዘራችን ጉልበታችን ፣ ሐብታችን፣ ችሎታችን...ወዘተርፈ አይደለም የእግዚአብሔር አብሮነት ነው እንጂ።
አስቲ ማዳኑን እዩ ወጥመድ ስውር ነው ፣ ድብቅ ነው ፣ ሳይታሰብ ደርሶ የሚነድፍ ፣ አስሮ ለጠላት አሳልፎ የሚሰጥ ፣ አልያም የሚገድል ነው ። ነገር ግን ከተሰነዘረው ጦር ፣ ከተወረወረው ቀስተ ፣ ከተጠመደው ወጥመድ ለመዳን ለማምለጥ የቻልንበት ሚስጥር የእግዚአብሔር አብሮነት ብቻ ነው። ከብር ለእግዚአብሔር ይሁን ። ለዚህ ነው ዳዊት ነፍሳችን እንደ ወፍ ከአዳኞች ወጥመድ አመለጠች፤ ወጥመድ ተሰበረ እኛም አመለጥን ያለው። የተጠመደውን የሰበረ የተመከረውን ያፈረሰ የጠላትን ሐሳብ ከንቱ አድርጎ በክብር ያቆመን እግዚአብሔር ነው። አሜን ! አሜን ! አሜን !
ረድኤታችን ሰማይንና ምድርን በሠራ ፣በሁሉ ላይ ሥልጣን ባለው ፣ሁሉን በሚገዛ ፣ የጌቶች ጌታ የኃያላን ኃያል ፣ የነገሥታት ንጉስ በሆነው በእግዚአብሔር ስም ነው።
ስለዚህ :-
1ኛ, በእግዚአብሔርን አብሮነት እመን ታመንም
ይህ ባይኖር በልዩነት መኖር ከወዴት በተገኘ ?
ስለዚህ እንደ ዳዊት ማዳኑን ክብሩን ጥበቃውን
አውጅ አመስግን ! ጥበቃውና እና ማዳኑ ልዩ ነው !
2ኛ, ለጠላት ፈቃድ ተላልፎ ያለመሰጠቴ ምክንያት
የእግዚአብሔርን አብሮነት ነው በል ጥበቃው ልዩ
ነውና ። ስለዚህ በእግዚአብሔር ታመን ።
3ኛ, ለሞትህ የተጠመደ ወጥመድ ሰብሮ ያስመልጣል !
የጠላት እቅድ ፕሮግራም በሕይወትህ
እንዲከናወን ያልፈቀደው እግዚአብሔር ነው።
ስለዚህ እግዚአብሔርን አመስግን !
4ኛ, እግዚአብሔር ያደረገላችሁን አውሩ አውጁ ተናገሩ
እስራኤል እንዲህ ይበል እንደተባለ በል ተናገር !
ወጥመድ ተሰበረ እኛም አመለጥን ። የታሰበው ፣
የታቀደው ፣ የተመከረው ፣ የተመተተው፣የተጻፈው ፣
የተደገመው አልሰራም አይሰራም አይከናወንም ።
5ኛ, መኖሪያችን ፣መታመኛችን ፣መጠጊያችን ፣እረኛችን፣
ረዳታችን፣ አለኝታችን፣ ክብራችን ፣ሞገሳችን ለእኛ
ሁሉን በሁሉ ሆኖ ያኖረንና የሚያኖረን እግዚአብሔር
ነው ። አሜን ! ክብር ሁሉ ለርሱ ይሁን ! ቅዱሳን ሁላችሁ
ስለ እኛ እና ከእኛ ጋር እግዚአብሔርን አመስግኑ !!!
90 views02:35