2023-01-20 04:26:22
የውሃ ጥምቀት ምንነት እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉም !
ጥምቀት፡ በግሪክ “ባፕቲዞ” (Baptism:- Immersion) ሲባል የቃሉ ትርጉም ሙሉ በሙሉ ወደ ውሃው መስመጥ እና መሸፈን (ከእይታ ውጭ መሆን) የሚያመለክት ነው፡፡ ሞልቶ በሚሲፈስ ነገር መሸፈን በዚያ ነገር ቁጥጥር ውስጥ መሆን የሚለውን ሐሳብ ይይዛል።
የሚታይ የጥምቀት ሥረዓት ከክርስቶስ ጋር በሁሉ መተባበራችንን የምንገልጠበት ምሳሌያዊ ምስክርነት ነው።
የምንጠመቀው በክርስቶስ የዳንበትን አዳዳን በተግባራዊ ስረዓት ለመግለጽ ነው። ከክርስቶስ በሞቱ እና በትንሳኤው መተባበራችንን በመግለጥ ዓለምንና ዓለማዊነትን መሰናበታችንን በሁሉ ፊት እንመሰክራለን። ከክርስቶስ ጋር በሞቱ እና በትንሳኤው መተባበራችን የሚገለጠው ወደ ውሃው ስንገባ መሞታችንን ፣ስንጠልቅ መቀበራችንን፣ ከውሃው ስንወጣ ለአዲስ ሕይወት መነሳታችንን ለመመስከር የጥምቀት ሥርዓት የምንፈጽመው።
መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር :-
" እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን። ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን" (ሮሜ 6:-4-6)
እኛ ብዙ ጊዜ "ጥምቀት" የሚለውን ቃል የምናያይዘው ከ"የውሃ" ጥምቀት ጋር ብቻ ነው። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ተለያዩ ጥምቀቶች ይናገራል ። የተለያዩ የጥምቀት አይነቶች አሉ፦
1) የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት፦
2) የውሃ ጥምቀት፦
3) የእሳት ጥምቀት፦
4) በመከራ መጠመቅ ስለ እያንዳንዱ ማብራራት ዓላማችን ስላልሆነ ወደ ውሃ ጥምቀቱ እንግባ ።
የውሃ ጥምቀት በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ በማመን መዳናችንን በምሳሌነት የምናሳይበት እውነት መሆኑን ካየን ( 1ጴጥ 3፡20-21 )
የጥምቀት ከመፈጸሙ በፊት የሚያስፈልገው መንድነው ? የሚለውን እንመልከት :-በ (ሐዋ. 8:28-37 ) ሲናገር
ኢትዮጵያዊው ጃንደረባው በውሃ ከመጠመቁ በፊት በት.ኢሳ 53 ያለውን ክፍል አንብቦ ስለ ማን እንደሚናገር ግራ ተጋብቶ ሳለ በፊሊጶስ ጥያቄ ቀረበለት :-
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
" ሲመለስም በሰረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር።መንፈስም ፊልጶስን፦ ወደዚህ ሰረገላ ቅረብና ተገናኝ አለው።ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና፦ በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን? አለው። እርሱም፦ የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል? አለው። ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው። ያነበውም የነበረ የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፥ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል? ጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ፦ እባክህ፥ ነቢዩ ይህን ስለ ማን ይናገራል? ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለ ሌላ? አለው። ፊልጶስም አፉን ከፈተ፥ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት።
ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የወንጌልን እውነት ተረድቶ ጌታ ኢሱስ ክርስቶስን የመስቀል ላይ ሥራ አንብቦ የማዳኑ ሚስጥር ገብቶት :-
“በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም፦ እነሆ ውኃ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው? አለው።”
— ሐዋርያት 8፥36
አየህ የማዳኑ ሚስጥር ከገባህ ፣ በመስቀል ላይ የተሰራልህ አስደናቂ የማዳኑን ስራ በልብህ ከመንክ እንዳትጠመቅ የሚከለክልህ ነገር የለም ።
“ፊልጶስም፦ በፍጹም ልብህ ብታምን፥ ተፈቅዶአል አለው። መልሶም፦ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ አለ።”
( ሐዋርያት 8፥37 )
ከውሃ ጥምቀት በፊት አንድ ሰው በክርስቶስ እየሱስ በመስቀል ላይ የተደረገለትን እና እየሱስ ክርስቶስ ስለ ኃጢያአቱ እንደተቀጣ ማወቅ እና ማመን መቀበል ይኖርበታል። ጃንደረባውም አንባቢ ነበር ታስተውለዋለህ ሲባል እንዴት እንዲህ ታስበኛለህ አላለም ፊሊጶስን ጠራው በጎኑ አስቀመጠ ከርሱ ተማረ ጠየቀ ተረዳ ኢየሱስ ክርስቶስን በሙሉ ልቡ አመነ ተጠመቀ ።
በውሃ የመጠመቁ ትርጉም :-
1) አማኙ በጌታ በኢየሱስ ሲያምን ከክርስቶስ ጋር መሞቱን ፣ አብሮ መሰቀሉን በሞቱ መተባበሩን ይገልጻል።
2) አማኙ ከጌታ ኢየሱስ ጋር በመቀበሩ መተባበሩን ወደ ውሃ ውስጥ በመጥለቅ ነው። በዚህም ለአሮጌው የሕይወት ስርዓት መሞቱን ይገልጽበታል፡፡ ይህም ከጌታ ጋር በመቀበር መተባበሩን ይገልጻል፡፡( ሮሜ 6፡4፣ ቆላ 2፡12.)
3) ከኢየሱስ ትንሳዔ ጋር መተባበሩንና ለአዲሱ የሕይወት ስርዓት በትንሳኤው የክርስቶስን ህይወት ተካፍሎ መነሳቱን ያሳል፡፡ (ሮሜ 6፡4-5, 1ጴጥ 3:21.) ይህም ከውኃው በሚወጣበት ቅጽበት ይገለጻል፡፡
4) ከዚያ በኋላ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ የትንሳኤ ሕይወት እየተገለጠበትና የንሰሐ ፍሬን በማፍራት በአዲስ ሕይወት መመላለስ ይገባል ፡፡ (ሮሜ 6፡7-11)
ደህንነት ወይም የዘላለም ሕይወት የሚገኘው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለኃጥያታችን መሞቱን እና መነሳቱን እንዲሁም ለደህንነታችን በመስቀል ላይ የተፈጸመልንን ሥራ አምኖ በመቀበል ነው፡፡
አንድ ሰው የውሃ ጥምቀትን ለመውሰድ የተሰጡ አራት መርሆች :-
1). ወንጌል ሊመሰከርለት ይገባል !
2). በሙሉ ልቡ አምኖ መቀበል ይኖርበታል /እምነት/
3). በንሰሐ በክርስቶስ ደም ሕሊናውን ተረጭቶ መቀደስ
4). ስሙን እየጠራ መጠመቅ ይኖርበታል !
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል:-
ጌታ ኢየሱስ ለአጥማቂዎች በማን ስም ማጥመቅ እንዳለባቸው በታላቁን የወንጌል ተልዕኮ ሲገልጥ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲያጠምቁ መመሪያ ሰጥቷቸዋል " እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ። (ማቴዎስ 28:-19-20 )
ተጠማቂው የሚጠመቀውን ሰው ደግሞ የጌታ የኢየሱስን ስም እንዲጠራ ይደረጋል ምክንያቱም የመጀመሪያዎቹ አይሁዶች በዚያን ዘመን አብንና መንፈስ ቅዱስን ቢያወቁም ኢየሱስ ክርስቶስን ግን አይቀበሉትም ነበር ይህ ደግሞ የመዳናቸውን እውነት መጣል ስለሆነ ማመናቸውን ለማወቅ እየጠሩት እንዲጠመቁ ይደረግ ነበር።“አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ።”አለው ( ሐዋርያት 22፥16)
ለምሳሌ ሐዋርያው ጴጥሮስ በበዓለ ሀምሳ ወንጌል የሰበካቸውንና ያመኑትን ሰዎች የጌታን ስም እየጠሩ እንዲጠመቁ ያዛቸዋል።ጴጥሮስም፡— ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። (ሐዋ. ሥራ 2 :-38)
በአጠቃላይ ጥምቀት አማኙ ኢየሱስን በማመን ብቻ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ከተቀበለ በኋላ ከክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ጋር መተባበሩን በመመሥከር የቤተክርስቲያን አባል ለመሆንና እንደሌሎች ወንድሞቹ ሁሉ ለኃጥያት መሞቱንና ከጌታ ኢየሱስ ጋር መቀበሩን፣ መነሳቱን እንዲሁም በአዲስ ሕይወት ለመመላለስ መወሰኑን የሚያሳይበት ምሳሌ ነው፡፡
176 views01:26