Get Mystery Box with random crypto!

በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አውጥቶናል ! “በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግ | የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ (pastor Alemayehu Abebe )

በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አውጥቶናል !

“በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ።”
— ገላትያ 5፥1
ነጻ የወጣነው ቀድሞ ከተያዝንበት የኃጢያት ባርነት ፣ ከዘር ተወራርሶ ከመጣው ክፉ የመንፈስ አሰራር ቀንበር ፣ አውቀንም ሳናውቅም ከተጫነብን እርግማን ቀነበርም ነው ።

በመናፍስቱ ዓለም አርነት በወጣንበት በክርስቶስ የነጻነት መንፈስ እንድንመላለስ ጠላት አይፈልግም። በቀድሞው አለማዊ ልምምድ እና መንፈሳዊ አሰራር የታሰረ ሰው ደግሞ በእግዚአብሔር ወደተዘረጋለት የከበረ መንፈሳዊ ደረጃ መድረስ አይችልም ። በፊቱ ወዳለው ክብር እንዳይዘረጋ አዕምሮው ሙሉ በሙሉ በቀድሞው ጉዳይ ጠላት ሰይጣን የቀድሞውን ቂም፣ በቀል ፣ጉዳት፣ መገፋት፣ ስቃዩን...ወዘተ በማሰብ ታስሮ እንዲኖር እና የይቅርታ፣ የእርቅ ፣የፍቅር፣ የመተው ሕይወት እንዳይኖረው በማድረግ በበደል ቆጣሪነት ታሥሮ እንዲኖር ያደርገዋል።

ከዚህ የተነሳ በክርስቶስ ያገኘውን የነጻነት ሕይወት እንዳይለማመድ ፣ በመዳኑ ሐሴት እንዳያደርግ ፣ በምሬት እና በማጉረምረም እንዲኖር ያደርገዋል። ስለዚህ ሰዎች በክርስቶስ ባገኙት አርነት ለመገኘት ከመናፍስት አሰራር ፣ ከዓለማዊነት ፣ ከክፉ ሰዎች ተጽኖ ፣ ከኃጢያት እስራት ፣ ከቀድሞ ክፉ ሥራቸው ወቀሳ ...ወዘተ ነጻ መውጣት እና መፈታት ይኖርባቸዋል።

ይህ ደግሞ ቀድሞ ከተሰራው በደልእና ኃጢያት በንሰሐ ፣ ከተጣሉት ሰው ጋር በይቅርታ ፣ የሚጠሉት ያ ሰው ምንም ያህል የበደላቸው፣ ያሰቃያቸው ፣ያንገላታቸው ቢሆን ለዛ ሰው ቀርቦ መልካም በማድረግ እና በተግባር ፍቅርን በስጦታ በመግለጽ የአዕምሮን ጠባሳ መሻር ይገባል ።

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚገሉት ሕይወትን ፣ ለሚጥሉት መነሳትን፣ ለሚያስሩት መፈታትን ፣ ለሚያቆስሉት መፈወስን ፣ ለሚያሰቃዩት እረፍትን ፣ ለነፍሰ ገዳዮች ምህረት ማግኘት ማለደ እኛም የተጠራነው ለዚሁ ነው ። “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።”
— 1ኛ ጴጥሮስ 2፥21

እንዲህ ብለን አንጸልይ እግዚአብሔር ሆይ አሁን ባለኝ እና ወደፊትም በሚኖረኝ የሕይወት ላይ የክፉ መንፈስ አሰራር በምንም መልኩ እድል ፈንታ እና ተጽኖ እንዲኖረው አልሻም ። ያለፈው የበደል እስራት የእርግማን ቀንበር መጥፎ አሳዛኝ ትዝታ ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተቆረጠ ይሁን ።ጌታ ሆይ የጠሉኝን ልወ፣ የጣሉኝን ላነሳ፣ የገፉኝን ላቀርብ፣ የተጣሉኝን ልታረቅ፣ የበደል እስራትን ልፈታ፣ የረገሙኝን ልመርቅ እና ያሳደዱኝን ልቀበል....ወዘተርፈ ቃል እገባሁ አቤቱ የሚረዳኝ ጸጋ ይሰጠኝ ! በበረከትና በነጻነት እንዳልኖር ከቀድሞ ዘመን ተከትሎኝ የመጣ ምንም ነገር በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተቆረጠ ይሁን ! አሜን! አሜን! አሜን !

1ኛ, ወደ ታቀደላችሁ የነጻነት ክብር ለመዘርጋት ወስኑ ።
2ኛ, ተከታትሎ የመጣውን ቂም ጥላቻ በተግባራዊ ምላሽ
በእርቅ በይቅርታ ፍቱ ።
3ኛ,የክፉ መናፍስትን ተጽኖ የቀድሞውን ቀንበር ስበሩት ።
የጠላት ዓላማ በእግዚአብሔር ወደ ተዘጋጀላችሁ ክብር
እንዳትሻገሩ መያዣው ነውና ።
4ኛ, በክርስቶስ የተገኘውን ነጻነት በሕይወታችሁ ፣
በኑሮአችሁ በአገልግሎታችሁ በትውልዳችሁ
ላይ አውጁት ።