2023-04-25 07:02:06
የህብረተሰቡን የቤት ልማት ፕሮግራም ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት መጠናከር እንዳለበት ተጠቆመ
ግንባታቸው በመፋጠን ላይ የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በማጠናቀቅና ነባር ፕሮጀክቶችን በመዝጋት የህብረተሰቡን የቤት ልማት ፕሮግራም ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገው ርብርብ ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት ተጠቆመ፡፡
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ እንዲሁም የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን እና የቅርንጫፍ ጽ/ቤት የሥራ ኃላፊዎች ባለፉት 15 ቀናት በተከናወኑት ተግባራት ዙሪያ ባካሄዱት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ላይ በሰነዘሯቸው አስተያየቶች በተለያዩ ሳይቶች ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ቀሪ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለነዋሪዎች ለማስተላለፍና ፕሮጀክቶቹን በመዝጋት ሌሎች ቀጣይ የልማት ሥራዎችን ለማፋጠን እየተደረገ ያለው ጥረት ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የቤቶቹን ግንባታ ከፍፃሜ በማድረስ ፕሮጀክቶቹን ዘግቶ ለመውጣት እየተደረገ ባለው ርብርብ በተለይ ለመሠረተ ልማት ግንባታ፣ ለወሰን ማስከበር እንዲሁም ለግብዓት አቅርቦትና ለሌሎችም ቁልፍ ተግባራት ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ያመለከቱት የሥራ ኃላፊዎቹ የከተማዋን ነዋሪዎች የቤት ባለቤት በማድረግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይበልጥ ተቀናጅቶ በጋራ መረባረብ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራትና የኮርፖሬሽኑ የግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ቶማስ ደበሌ እንዲሁም ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች የከተማ አስተዳደሩ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ነባር የቤት ልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለነዋሪዎች ማስተላለፍና ህብረተሰቡ በየጊዜው ለሚያነሳቸው ቅሬታዎች ምላሽ መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከመደበኛ የሥራ ሠዓት በተጨማሪ ትርፍ ጊዜያቸውን በመጠቀምና አምሽቶ በመሥራት የተቀመጠውን ዕቅድ ለማሳካት ጠንክረው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በሥራ አፈፃፀም ግምገማው ላይ የቢሮው ፣ የኮርፖሬሽኑ እንዲሁም የቅርንጫፍ ጽ/ቤት የሥራ ኃላፊዎችና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመሰረተ ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ልማት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
http://www.aahdab.gov.et
https://t.me/aahdabofficial
https://www.facebook.com/aahdabofficial
2.3K views04:02