Get Mystery Box with random crypto!

ዝክረ ብሒለ አበው

የቴሌግራም ቻናል አርማ behileabew — ዝክረ ብሒለ አበው
የቴሌግራም ቻናል አርማ behileabew — ዝክረ ብሒለ አበው
የሰርጥ አድራሻ: @behileabew
ምድቦች: ያልተመደበ
ቋንቋ: አማርኛ
ተመዝጋቢዎች: 345

Ratings & Reviews

3.50

2 reviews

Reviews can be left only by registered users. All reviews are moderated by admins.

5 stars

1

4 stars

0

3 stars

0

2 stars

1

1 stars

0


የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች 7

2022-12-26 21:04:38
45 viewsbisrat, 18:04
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-12-26 21:03:33 #ታህሳስ_19_ኃያሉ_መልአክ_ቅዱስ_ገብርኤል_ሠለስቱ_ደቂቅን_ከእቶን_እሳት_ያዳነበት_ዕለት_ነው።

አይሁድ እግዚአብሔርን ባሳዘኑት ጊዜ ለተግሳጽ ከፍሎ ለምርኮ ሰጣቸው፡፡ የሚወዷቸውና የሚባረኩባቸው ዕቃዎች (ንዋያተ ቅዱሳትም) ተወሰዱባቸው፡፡ ይህ ለአይሁድ ከባድ ቅጣት ነበር፡፡ በዚህ ደንግጠው ንስሐ እንዲገቡ እግዚአብሔር  ይህን ከደረገ፡፡ እኛም ስናጠፋ እግዚአብሔር በቤተሰብ በኩል፣ ወይም በካህናት አልፎም በሌሎች ሰዎች ይመክረናል፤ ይገስጸናልም፡፡ እኛም ስንቀጣና ስንገሰጽ ልንታረም ይገባል፡፡

ከለዳውያን በዛሬዋ ኢራቅ እና አከባቢዋ የነበሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡ በጥንት ዘመን ኃያል መንግሥት አቋቋሙው የሒሳብ፣ የከዋክብት ጥናት፣... ከአስማትና ጥንቆላ ጋር እንደ ትምህርት ይሰጡ ነበር፡፡

ናቡከደነፆር ከ፮፻፭ - ፭፮፪ ዓ.ዓ የነበረ የባቢሎን ንጉሥ ነው፡፡ ይህ ንጉሥ ሁለት ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቷል፡፡ የመጀመሪያው በይሁዳው ንጉሥ በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት ሲሆን ፤ ሁለተኛውም በልጁ በሴዴቅያስ ዘመን ነው፡፡(፪ኛ ዜና. ፴፮፥፭-፯፣ ፲፩-፳) በመጀመሪያው ወረራ የግብጽን ንጉሥ ኒካዑን አሸነፈ፡፡ ኢየሩሳሌምንም ያዘ፡፡ እርሱ የበላይ ሆኖ ከአይሁድ ልጆች ነገሥታት ይሾም ነበር፡፡ አይሁድ ሲያምጹ ከተማይቱን አፈራረሳት፤ ቤተ መቅደሱንም አቃጠለ፡፡ ሕዝቡንም ማርኮ ወሰደ፡፡ ኤር. ፵፮፥፪፣ ፪ኛ ነገ. ፳፬፥፩-፯፣ ፪ኛ.ዜና ፴፮፥፲፯-፳፩ ከተማረኩት ወጣቶች ዳንኤልና ሦስቱ ጎደኞቹ አናንያ አዛርያና ሚሳኤል ይገኙበታል፡፡ (ዳን. ፩፥ ፩ - ፯ )

የስማቸውም ትርጓሜ:-
#ዳንኤል_እግዚአብሔር_ዳኛ_ነው
#አናንያ_እግዚአብሔር_ቸር_ነው 
#አዛርያ_እግዚአብሔር_ይረዳዋል
#ሚሳኤል_እግዚአብሔርን_ማን_ይመስለዋል ማለት ነው።

ባቢሎናዊ መጠሪያ ስማቸውና ትርጓሜያቸው:-
#ዳንኤልን_ብልጣሶር_የበኣል_ልጅ (መስፍን) ማለት ነው። #በአል  የባቢሎናውያን ዋና ጣዖት መጠሪያ ነው።

#አናንያን_ሲድራቅ_ሲሉት_የአኩ_አምሳል ማለት ነው #አኩ ባቢሎናውያን የጨረቃ ምላክ የሚሉት ጣዖት ነው

#አዛርያን_አብደናጎ_ይሉታል_የነጎ አገልጋይ ማለት ነው። #ነጎ ወይም ሄቦ የፀሐይ አምላክ የተባለ ጣዖት ነበር፡፡

#ሚሳኤልን_ደግሞ_ሚሳቅ ትርጓሜውም እንደ ሻቅ ማነው ማለት ሲሆን #ሻቅ የመሬትና የውበት አምላክ የሚልዋት ጣዖት ነበረች፡፡
እነዚህም ብላቴኖች ከኢየሩሳሌም ተማርከው በባዕድ ሃገር ሆነው እግዚአብሔር ያመልኩ ትዕዛዙንም ያከብሩ ነበር።

ከዕለታትም በአንደኛው ዕለት ንጉሡ ናቡከደነፆር የእርሱን ትዕዛዝና ሕግ የሚያከብረውን ከማያከብረውን ለይቶ ለማወቅ የወርቁን ምስል አሠራ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው ። ለወርቁ ምስል ሁሉም እንዲሰግድ እንዲንበረከክ አዘዘ ከእነዚህ ሦስት ሲድራቅ ሚሳቅና አብደናጎም ብለው የሚጠሯቸው የልዑል እግዚአብሔር ብላቴናዎች  በቀር ሁሉም ሰገደ ተንበረከከ።

ናቡከደነፆርም በብስጭትና በቍጣ ሦስቱን ብላቴናዎች ያመጧቸው ዘንድ አዘዘ ወደ ንጉሡ ፊት አመጡአቸው። አምላኬን አለማምለካችሁ፥ ላቆምሁትም ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን? እንግዲውስ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ከእጄ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? ብሎ ተናገራቸው።

ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም እንዲህ ሲሉ መለሱለት ንጉስ ሆይ፥ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ደግሞም ያድነናል! ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን እንኳን አማልክትህን እንደናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንደማንሰግድ እወቅ አሉት።

የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም ላይ ቍጣ ሞላበት፥ የፊቱም መልክ ተለወጠባቸው፤ እርሱም ተናገረ፥ የእቶንም እሳት ይነድድ ከነበረው ይልቅ ሰባት እጥፍ አድርገው እንዲያነድዱት እና እሳቱ ይጥሉአቸው ዘንድ አዘዘ፤ የዚያን ጊዜም እነዚህ ብላቴናዎች ከነልብሳቸው ከነመጐናጸፊያቸው ታስረው እሳት ውስጥ ተጣሉ። ናቡከደነፆር አሟሟታቸውን ሊመለከት ቆመ ወደ እሳቱም ተመለከተ።

አራት ሰዎችም በእሳት ውስጥ ሲመላለሱ አየ ተደነቀ ፈጥኖም ተነሣ፤ አማካሪዎቹንም። ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን? ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም ንጉሥ ሆይ፥ እውነት ነው ብለው መለሱለት።እርሱም እነሆ፥ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አላቈሰላቸውም፤ የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል ብሎ መለሰ። ይህም ታላቁ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡
ናቡከደነፆር ድምጹን ከፍ አድርጎ ከእሳቱ እንዲወጡ ተጣራ የራሳቸው ጸጉር አልተቃጠለም ልብሳቸውም እንዲሁ ናቡከደነፆር ከዚህ በኃላ እንዲህ ሲል እግዚአብሔርን አመሰገነ “በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ” ትንቢተ ዳንኤል ፫፡ ፩- ፴
 
ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፡፡ አሜን!!!
100 viewsbisrat, 18:03
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-12-17 07:56:34
15 viewsbisrat, 04:56
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-12-17 07:55:32 #ታህሳስ_8_የትዕግስተኛዋ_እናት_የቅድስት_እንባመሪና_ልደት_ነው።

የቅድስት እንባመሪና እናትና አባት ባለጸጋ የነበሩ፣ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ፣ መልካም ምግባር የነበራቸው ነበሩ፡፡ እንባመሪና ገና ሕፃን ሳለች እናቷ ዐረፈች፤

በዚህን ጊዜ አቧቷ ወደ ገዳም በመሄድ ሊመነኩስ ፈለገ፤ ንብረቱንም አውርሷት ለመሄድ ሲነሣ እንባመሪናም (ልጁም) አብራው መነኩሴ መሆን እንደምትፈልግ ነገረችው፡፡ ንብረቱን ሽጦ ለችግረኞች ከሰጠ በኋላ ከልጁ ጋር መንኩሶ እግዚአብሔርን እያገለገለ ለመኖር በመወሰኑ ልጁን አስከትሎ ወደ ገዳም ሄደ፡፡ ሴቶች ከወንዶች ገዳም መግባት ስለማይፈቀድላቸው ፀጉሯን ላጭቶ የወንድ ልብስ ካለበሳት በኋላ ወደ ገዳም አብረው ገቡ፤ በጾም፣ በጸሎት፣ በገድልና በትሩፋት ብዙ ዓመት ከኖሩ በኋላ የእንባመሪና አባት ታመመ፤ ልጁንም ለገዳሙ አበምኔት አደራ ሰጠና ዐረፈ፡፡

እንባመሪናም በጽኑ ተጋድሎ ሴት መሆኗን ማን ሳያውቅ በጾም፣ በጸሎትና በትሩፋት ሥራ በረታች፡፡ ታዲያ በአንድ ወቅት መነኮሳቱ ወደ መንደር ለሥራ ጉዳይ ሲላኩ እንባመሪናንም አስከትለው ተጓዙ! ለገዳሙ የሚያስፈልገውን እህል ከሰዎች በመሰብሰብ እያጠራቀመ ለመነኮሳቱ የሚሰጥ አንድ ደገኛ ሰው ነበር፡፡ እንደተለመደው የሰበሰበውን እህል ለመውሰድ ከቤቱ ገቡ፤ ምሽትም ስለነበር መነኰሳቱ በእንግድነት እዚያው አደሩ፡፡ በጠዋትም ተነሡና ወደ ገዳሙ ተጓዙ፡፡ መነኮሳቱ ሰውየው ቤት በእንግድነት ባደሩበት ዕለት አንድ ክፉ ሰው ከሰውየው ቤት ገብቶ የሰውየውን ሴት ልጆ አስነውሮ ሄደ፡፡ ሰውየው በጣም የሚወዳት በእንክብካቤ ያሳደጋት በወግ በማዕረግ የቆየች ልጁ ነበረች ግን ያ ክፉ ጎረምሳ ንጽሕናዋን አጎደፈው፤ መነኮሳቱም የተሰጣቸውን ኃላፊነት ፈጽመው ወደ ገዳማቸው ተመለሱ፡፡

ከሦስት ወር በኋላ ያ የገዳሙን ንብረት እየሰበሰበ መነኮሳቱን በመርዳት የሚያገለግለው ባለጸጋ ሴት ልጅ ነፍሰጡር መሆኗ ታወቀ፡፡ ሰውየውም በክብር፣ በወግና በማዕረግ ባል አጋባታለው እያለ ሲያስብ ድንገት አርግዛ (ነፍሰ ጡር ሆና) ሲመለከት በጣም አዘነ ፡፡  ቤተሰቦቻችን እኛ በሥርዓት፣ በጥሩ ሥነ ምግባር፣ በንጽሕና አድገን የእኛን መልካም ነገር፣ ደስታ ወግ ማዕረግን ማየት ይፈልጋሉ፡፡ ታዲያ እኛም ጥሩ ሥነ ምግባር ያለን ራሳችንን ከከንቱ፣ ከክፉ ነገር በመጠበቅ መኖር ይጠበቅብናል፡፡

ሰውየው ልጁ ድንገት ከሥርዓት ውጪ ባል ሳታገባ ልጅ ልትወልድ መሆኑን ሲመለከት በጣም አዘነ፡፡ ልጁን ከክብር ያሳነሰበትን፣ ሕልሙን ያበላሸበትን፣ ደስታውን የነጠቀበትን ፣ ሰው ማን እንደሆነ ትነግረው ዘንድ አስጨነቃት፡፡ ማን እንደዚህ እንዳደረጋት በጣም ሲጨንቃት ”ቤታችን በእንግድነት መጥተው ከነበሩ መነኮሳት መካከል ወጣቱ መነኩሴ እንባመሪና ነው‘ እንደዚህ ያደረገኝ አለች፡፡ ይህንን ያለችበት ምክንያትም ያ ከክብራ ያሳነሳት ክፉ ጎልማሳ ”እኔ መሆኔን ከተናገርሽ እገልሻለሁ‘ ብሏት ስለነበር ነው፡፡ አባትየውም ከገዳሙ ሄዶ ለአበምኔቱ አመለከተ፡፡

እንባመሪናም ባልሠራችው ሥራ፣ ባልፈጸመችው በደል ተከሰሰች፡፡ ለክብር የመጣባት ፈተና ነበርና ራሷን መግለጥ (ሴት መሆኗን) ተናግራ ”አልፈጸሙክኝም ‘ ማለት እየቻለች በዚህ የተነሣ ሴት መሆኗ እንዳይታወቅ ፣በማለት በትዕግሥት ”አዎ ፈጽሜያለው፤ ግን ይቅርታ አድርጉልኝ! ልጁ ሲወለድ አሳድጋለሁ አለች፤ አበምኔቱ በጣም አዘነ፡፡ ከመነኰሳቱ መካከል በዝሙት ተፈትኖ የወደቀ፣የአገልጋያቸውን ሰው ልጅ የበደለ መነኩሴ በገዳሙ በመገኘቱ አለቀሰ፡፡ ከዚያም እንባመሪና ከገዳም ተባረረች።

ከዚህም በኋላ ይቅርታ እንዲደረግላት ጠይቃ ከጽኑዕ ቅጣት በኋላ ከገዳሙ አቅራቢያ እንድትኖር ተፈቀደላት፡፡ የሰውየው ልጅም ወለደች፡፡ ሕፃኑንንም ታሳድግ ዘንድ ለእንባመሪና ሰጧት፡፡ በጣም አሳዛኝ ነገር ነው፡፡ ሴት ሆና ሳለ ራሷን በትሕትና ባለመግለጿ ባልሠራችው ተወንጅላ የእርሷ ያልሆነውን ልጅ በአባትነት እንድታሳድግ ተሰጣት፡፡

ይገርማችኋል እንባመሪና ያንን ሕፃን ወተት ከሰላም እረኞች እየለመነች አሳደገችው፡፡ እርሷም በጾምና በጸሎት በተጋድሎ ኖረች፡፡ ከዚያም ልጁ አደገና የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ተማረ፡፡ ከገዳም ገብቶ በዚያም መነኮሰ፤ እንባመሪናም ታማ ዐረፈች፡፡

በዚህን ጊዜ መነኮሳቱ ተሰበሰቡ ገንዘው ሊቀብሯት ሲሉም ያን ጊዜ ወንድ ሳትሆን ሴት መሆኗን ተመለከቱ በጣም አዘኑ፤ አለቀሱም፤ ባልሠራችው ሥራ ተወቅሳና ተቀጥታ፣ ያልወለደችውን ልጅ ልጅሽ ተብላ፣ ደክማ አሳድጋ፣ አስተምራና እንዲመነኩስ በማድረጓ ጽናትና ትዕግስቷን አስታውሰው አለቀሱ፡፡ ”ማሪን!‘ እያሉ ሁሉም ተጸጸቱ፣

የልጅቷንም አባት ወደ ገዳሙ አስጠሩና የሆነውን ሁሉ ነገሩት፡፡ ልጁን ያስነወረችው እርሷ እንዳልሆነች ባወቀ ጊዜ መራራን ኀዘን አዘነ፡፡ ከቅድስት እንባመሪና አስክሬን ላይ ተደፍተው ”ማሪን!‘ እያሉ አለቀሱ፡፡ የሰውየውም ልጅ እውነቱን እንድታወጣ ተጠየቀችና እንባመሪና ምንም እንዳላደረገቻት ተናገረች፡፡

ከዚህም በኋላ እርሷንም ያስነወራትንም ጎረምሳ ክፉ ሰይጣን ያዛቸውና ከእንባመሪና መቃብር ሄደው ኃጢአታቸውን በሕዝቡ ሁሉ ፊት እስኪያምኑ ድረስ እጅግ አሠቃያቸው፡፡
በእውነት የእንባመሪና ተጋድሎ ድንቅ ነው! አምላካችን በረከቷን ያድለን፤ ከእንባመሪና ታሪክ የምንማረው ትዕግሥትን ነው፡፡ ሰይጣን በሰዎች አድሮ ማንነቷን በመግለጥ ከገዳም እንድትወጣ ቢጥርም እርሷ ግን በትዕግሥት ያልሠራችውን አምና ተቀብላ ለበለጠ ክብር በቃች፡፡ ውሸት ለጊዜው ተቀባይነት ቢታገኝም እውነት ግን አንድ ቀን እንደምትገለጥና ሐሰተኞች እንዲሚያፍሩና እንደሚቀጡ ያስተምረናል፡፡ ስለዚህ በሕይወታችን ታማኞችና እውነተኞች ልንሆን ይገባል፡፡ ክብርን አለመጠበቅና ያለሥርዓት መጓዝ ትልቅ ዋጋ እንደሚያስከፍል ማስተዋል አለብን፡፡ ራሳችንን ጠብቀን መኖር እንደሚገባንም ተምረናል፤  ነገሮችን ሳንመረምርና ሳናጣራ በሰው ላይ መፍረድ እንደማይገባ፣ በጾምና በጸሎት ጠላታችን ሰይጣንን ድል እንደምናደርገው ከቅድስት እንባመሪና ታሪክ እንማራለን፡፡ 

የእግዚአብሔርን ወዳጆች የቅዱሳንን ታሪክ፣ የሕይወት ተጋድሎ፣ ክብራቸውን የምንማረው እኛም እንደነርሱ ራሳችንን ከክፉ ነገር ጠብቀንና መልካም ሠርተን መኖር እንድንችል ነው፡፡ በምንማረው ትምህርት ቅዱሳንን አርአያ ልናደርጋቸው ይገባል፤ ትሑታን፣ሰዎችን አከባሪ፣ በመሆን በቤተ ክርስቲያን እያገለገልን ልናድግ ይገባናል፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! እኛንም በትዕግስተኛዋ እናት ጸሎት ይማረን አሜን
፡፡ ይቆየን!!!
17 viewsbisrat, 04:55
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-12-14 18:33:22
21 viewsbisrat, 15:33
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-12-14 18:32:35 #ታኅሣሥ_6_ለቅድስት_አርሴማና_ለተከታዮቿ_ሰማዕታት_የፍልሰትና_የቅዳሴ ቤት_መታሰቢያ_ዕለት_ነው።

በዚህች ዕለት የቅድስት ሰማዕት አርሴማ የቤተክርስቲያንዋ ቅዳሴ ከእርሷም ጋር የተገደሉ የሃያ ሰባት የቅዱሳን ሰማዕት የስጋ ፍልሰትና ሰማዕት የሆኑ የእነዚያ ደናግል መታሰቢያ ሆነ፡፡

. . .ንጉስ ድርጣድስም ይህችን ቅድስት አርሴማን ከእኛ ጋር ስትኖር ይህንን ያህል እውቀት በልብሽ የለውምን አላት ፡፡ ቅድስት አርሴማም ድርጣድስን ሰነፍ የሰማይ ኑሮ ይበልጣል ይሻላልም አለችው፡፡ ያን ጊዜም ንጉስ ድርጣድስ ወደ መገደያው ቦታ እንዲወስዷአትና ራቁትዋን አድርገው በሰይፍ አንገትዋን እንዲቆርጧአት አዘዘ፡፡ እርሱዋም በመንግስት ሰማያት የክብር አክሊልን ተቀበለች፡፡

 . . .በዚህም ቀን ታላላቅ ተአምራቶች ተደርገዋል፤ በተለይም ይህ ቀን በአገረ አርማንያ ልዩ ስፍራ አለው፤ በመዲናችን አዲስ አበባ አስኮ ቃሎ ተራራ ላይ ግሩም ቤተክርስቲያን አላት ታዋቂው ገዳሟ ግን ወሎ ሲሪንቃ ይገኛል። መስከረም 29 በሰማዕትነት ያረፈችበት ነው፤ እነዚህን ሁለቱን ቀናት ቤተክርስቲያን በደማቁ ታከብራቸዋለች፤

ሌላው በዛሬው ቀን ታላቁ አባት አብርሃም ሶርያዊው ያረፈበት ቀን ነው፤ ይህ አባት ተራራን ያፈለሰ ነው፤

ታሪኩ ወዲህ ነው አባ አብርሃም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ በነበረበት ወራት አንድ አይሁዳዊ ወደ ንጉሱ ገብቶ እንዲህ ይለዋል “እነዚህ ክርስቲያኖች የሚገርሙ ናቸው በወንጌላቸው ላይ የሰናፍጭ ቅንጣት እምነት ካላችሁ ይህንን ተራራ ተነቅለህ ወደዚያ ሂድ ብትሉት ይሆንላቹዋል ይላል፤” ይህ የሐሰት ወንጌል ነው፤ከመካከላቸው ይህን የሚያደርግ አንድስ እንኳን የለም ይለዋል” ንጉሱም አባ አብርሃምን አስጠርቶ “በእርግጥ ወንጌላችሁ እንዲህ ይላልን ?” ይለዋል አዋን ንጉስ ሆይ ብሎ ይመልስለታል፤ ታዲያ የክርስቲያኖች ሁሉ አባታቸው አለቃቸው አንተ ነህ እስኪ አድርግና አሳየኝ ይለዋል፤ እሺ ግን 3 ቀን ብቻ ይስጡኝ ብሎ ወጣ፤ ጨነቀው ወደ እምቤታችን ቤተክርስቲያን ገብቶ 3 ቀን 3 ሌሊት እህል ሳይበላ ውኃ ሳይጠጣ አለቀሰ፤ እመቤቴ አታሳፍሪኝ አላት፤ ተገለጸችለት ይህ ላንተ አይሆንም ግን ወደ ከተማ ውጣ በእንስራ ውሃ ተሸክሞ የሚሄድ ሰው ታገኛለህ፤ ስሙ ስምዖን ጫማ ሰፊ ነው፤ አንድ አይና ነው፤ አንዱን አይኑን ያጠፋው የልጄን ትዕዛዝ ለማክበር ብሎ ነው፤ ለእርሱ ይቻለዋል እርሱ የሚልህን አድርግ ትለዋለች፤

እንደተባለውም ስምዖንን ያገኘዋል፤ ነገሩን ሁሉ ይገልጽለታል፤ እሺ ለማንም ስሜንም ስራዬንም እንዳትገልጽቢኝ፤ ህዝቡን ሰብስብ እኔ በተሰወረ ቦታ ሆኜ የማሳይህን እየተመለከትክ አድርግ አንተ የምታደርገውን ደግሞ ህዝቡ ያድርግ አለው፤

ንጉሱም ሰራዊቱም ህዝቡም ይህንን ታአምር ለማየት ተሰበሰበ፤ 41 ጊዜ ኪራላይሶን ብለው ሶስት ጊዜ ሰገዱ፤ ከዚያም አባ አብርሃ ስምዖን የሚያሳየውን እየተከተለ መስቀሉን አውጥቶ ወደ ተራራው አማተበ፤ ተራራው ወደ ላይ ተነሰ፤ ታላቅ ፍርሃት ሆነ፤ ሶስት ጊዜ ተራራው ወደ ላይ እየተነሳ ይቀመጣል በተራራው ስር ከወዲያ ማዶና ከወዲህ ያሉ ሰዎች ይተያዩ ነበር ይላይ፤ ንጉሱም ህዝቡም እጹብ እጹብ አሉ ምስጉን እግዚያብሔርንም አመሰገኑ፤ ንጉሱ ክርስቲያን ሆኖ ተጠምቋል ብዙ አብያተክርስቲያናትንም አንጿል። አባ እብርሃምም ተፈርቶና ተከብሮ በቅድስናም ኖሮ በዛሬዋ እለት አርፏል።

 ከቅድስት አርሴማ፤ ከአባ አብርሃምና ከስምዖን ጫማ ሰፊ በረከታቸውን ያድለን። አሜን
23 viewsbisrat, 15:32
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-12-13 20:00:32
25 viewsbisrat, 17:00
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-12-13 20:00:01 #ታህሳስ_5_ጻድቅት_ወሰማዕት_ቅድስት_አውጋንያ_ሰማዕት_የሆነችበት_ዕለት_ነው ::

የቅድስት አውጋንያ ስም አጠራሯ በእውነት የከበረ ነው:: ዜና ሕይወቷ ሲሰማ ጣዕመ ነፍስን ያድላልና:: በፈጣሪ ረዳትነት ልጀምር:: እናንተም በእግዚአብሔር አጋዥነት ተከተሉኝ::

ቅድስት አውጋንያ የ3ኛው መቶ ክ/ዘ የክርስትና ፍሬ ናት:: በትውልዷ ሮማዊት ስትሆን አባቷ ፊልዾስ ይባላል:: ሥራውም የጦር መሪ: የሃገርም አስተዳዳሪ ነው:: በስም ያልተጠቀሰች እናቷ ደግሞ ክርስቲያን ነበረች:: ዘመኑ አስከፊ ስለ ነበር (ለክርስቲያኖች ማለቴ ነው) ክርስትናዋን ደብቃ: አልባሌ (አሕዛባዊ) መስላ ትኖር ነበር:: ቅድስት አውጋንያን ስትወልድ ግን ጨነቃት:: እንዳታስጠምቃት የእርሷም ሆነ የሕጻን ልጇ እጣ ፈንታ ሞት መሆኑ ነው:: +ምክንያቱም ባሏ ፊልዾስ ክርስትናን ፈጽሞ የሚጠላ ጣዖት አምላኪ ነበርና:: ከዚያም አልፎ ሰዎች ለጣዖት እንዲንበረከኩም ያስገድድ ነበር:: ስለዚህ እናት ልጇን ሳታስጠምቅ: ግን በፍጹም የክርስትና ትምሕርትና ሥርዓት አሳደገቻት:: +ቅድስት አውጋንያም ጾምን ጸሎትን: ትሕትናን: ትእግስትን የተመላች ወጣት ሆነች:: ግን ምሥጢረ ጥምቀትን ታገኝ ዘንድ ዘወትር ፈጣሪዋን ትማጸን ነበር:: +በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉም አንድ መልካም አጋጣሚ ተፈጠረ:: መኮንኑ አባቷ (ፊልዾስ) በምድረ ግብጽ እስክንድርያ አገረ ገዥ ሆኖ በመሾሙ ጉዋዛቸውን ጠቅልለው ወረዱ:: ምንም ይህ ለቅድስት አውጋንያ መልካም አጋጣሚ ቢሆንም ሌላ ፈተናን አመጣባት::

አባቷ ለአረማዊ መኮንን ሊድራት መሆኑን ሰማች:: አሁን ግን መቁረጥ ያስፈልግ ነበርና ወሰነች:: ወደ አባቷ ገብታም "አባቴ! አንድ ነገር ላስቸግርህ:: አንተ ለምትለኝ ሁሉ እታዘዛለሁ:: ግን ከሠርጌ ቀን በፊት ለአንዲት ቀን በዱር ውስጥ ተናፍሼ: ተዝናንቼ እንድመጣ ፍቀድልኝ?" አለችው:: +ምን እንዳሰበች ያልጠረጠረ አባቷም ከ2 ጃንደረቦች ጋር እንድትሔድ አደረገ:: በርሃ አካባቢ ሲደርሱም ቅድስት አውጋንያ እውነቱን ለ2ቱ ጃንደረቦች ተከታዮቿ ነገረቻቸው:: "እኔ ወደ በርሃ የምሔደው ክርስቲያን ልሆን: ደግሞም ልመንን ነውና ካላሰኛችሁ ተመለሱ" አለቻቸው:: 2ቱም ግን በአንድ ቃል "ሞታችንም: ሕይወታችንም ከአንቺ ጋር ነው" ብለዋት አብረው ገዳም ገቡ::

እንደ ደረሱም ምሥጢራቸውን ለአንድ ጻድቅ መነኮስ ተናግራ እንዲያጠምቃት ጠየቀችው:: መነኮሱም 3ቱንም ካጠመቃቸው በሁዋላ ቅድስት አውጋንያ "አመንኩሰን" ብትለው "ልጄ! ይሔ የወንዶች ገዳም ነውኮ" አላት:: "አባ! ግድ የለህም! እኔ ራሴን እሰውራለሁ" አለችው:: ከዚያም ሥርዓተ ገዳምን አስተምሮ ስሟን "አባ አውጋንዮስ" ብሎ ከማሕበረ መነኮሳቱ ቀላቀላት:: *አውጋንያን *ታኦድራ *አንስጣስያ . . . የመሳሰሉ ስሞች በቀላል መንገድ ወደ ወንድ ስምነት *አውጋንዮስ *ቴዎድሮስ *አንስጣስዮስ . . .በሚል መቀየር ይችላሉና::

ከዚህች ዕለት ጀምራ ቅድስት አውጋንያ በአባ አውጋንዮስነቷ ተጋድሎን ጀመረች:: ቀን ቀን ወንዶች መነኮሳት የሚሠሩትን ከባድ ሥራ ሁሉ ስትሠራ ትውልና ሌሊት በትጋት ስትጸልይ ታድራለች:: ለ1 ዓመት ያህል በፍጹም ተጸምዶ ገዳሙን አገለገለች:: በነዚህ ጊዜያት የመጡባትን ፈተናዎችም ታገሰች:: ዓለምን የናቀችለት: የአባቷን ቤተ መንግስት የተወችለት ክርስቶስ ኃይሏ ነበርና:: በዚያ ሰሞንም የገዳሙ አበ ምኔት በማረፉ መነኮሳትን የሚመራና የሚናዝዝ ሌላ አበ ምኔትን ለመምረጥ ሱባኤ ገቡ::

ከሱባኤ ወጥተው ሲሰበሰቡ ግን ያመጡት የመንፈስ ቅዱስ መልእክት የሚገርም ነበር:: የሁሉም ዓይን ወደ አባ አውጋንዮስ ተወረወረ:: እርሷ ምሥጢሯን (ሴትነቷን) ታውቃለችና ደነገጠች:: ምርጫው ግን የመንፈስ ቅዱስ ነበርና ግድ ብለው በእነዛ ሁሉ መነኮሳት ላይ እረኛ ሁና ተሾመች:: በእርግጥ እርሷ ሴት በዚያውም ላይ ወጣት ናት:: ግን እውነተኛ የክርስቶስ ወዳጅ ነበረችና በፍጹም ትጋት መነኮሳትን አስተዳደረች:: ጸጋው ቢበዛላት የተጨነቀውን ታረጋጋ: የታመመውን እጇን እየጫነች በጸሎቷ ትፈውስ ነበር:: በዚህም መነኮሳቱ ደስ ተሰኙ::

እርሷ ግን ስለዚህ ፈንታ ብዙ ፈተናዎችን በአኮቴት ታሳልፍ ነበር:: ስም አጠራሯም ከበርሃ ወጥቶ ወደ ከተሞች በመግባቱ ድውያን እየመጡ ከእርሷ ዘንድ ይፈወሱ ነበር:: አንድ ቀን ግን ያልተጠበቀ ፈተና መጣባት:: +አንዲት ሰይጣን ያደረባትን ሴት ካዳነቻት በሁዋላ: መልኩዋ እጅግ ውብ ስለ ነበር የዝሙት ጥያቄን አቀረበችላት:: (ሴቷ ለሴቷ ማለት ነው) ለእርሷ ወንድ መስላታለችና:: ቅድስት አውጋንያ ግን ገሥጻ ሰደደቻት:: በዚህ የበሸቀችው ያቺ ክፉ ወጣት ወደ ከተማ ሒዳ ለሃገረ ገዢው ፊልዾስ (የቅድስቷ አባት) ክስ አቀረበች:: +እርሱ (ፊልዾስ) አውጋንያ ከጠፋችበት ቀን ጀምሮ በስሟ ጣዖት አሠርቶ የሚሰግድ ሆኖ ነበር:: ወጣቷ "በገዳም ያሉ መነኮሳት: በተለይ አውጋንዮስ የሚሉት መሪያቸው አስገድዶ ከክብር ሊያጐድሉኝ ሲሉ አመለጥኩ" ብላ በሃሰት በመክሰሷ ገዳሙ እንዲመዘበር: መነኮሳቱም እንዲገረፉ መኮንኑ ፊልዾስ አዘዘ:: +በግርፋቱ መካከልም ብዙ መነኮሳት ሞቱ:: የእነርሱ ስቃይ ያንገበገባት ቅድስት አውጋንያ ግን አባቷን ለብቻ ወስዳ አስምላ ማንነቷን ገለጸችለት:: የናፈቃት ልጁን ሲያገኝ ደስ ብሎት መነኮሳቱን እንዲተዉ አዘዘ:: +ለብቻ ከልጁ ጋር ተቀምጦም ያለፈውን ነገር ሁሉ ነግራ ስለ ሰማያዊ ሕይወት አስረዳችው:: በስሟ የተቀረጸውን ጣዖትም ሰብራ አባቷን አስጠመቀችው:: እርሱም መንኖ ለዓመታት ኖረ:: ከዚያም ዻዻስ ሆኖ ተሹሟል::

ታህሳስ 5 ቀን ስለ ክርስቶስ አንገቱን ተሰይፏል:: ቅድስት አውጋንያ ግን ከግብጽ ወደ ሮም ሒዳ የደናግል ገዳምን መሠረተች:: በሥሯም አምላክ 3,300 ደናግልን ሰበሰበላት:: እነርሱን ስታጽናና: ስትመክር: ስትመራ ለዓመታት ኑራ በአካባቢው ገዢ ሃይማኖቷን እንድትክድ ተጠየቀች:: "እንቢ" በማለቷ እርሷም እንደ አባቷ በዚህች ቀን ተሰይፋ ሰማዕት ሆናለች:: አብረዋት የመነኑ 2ቱ ጃንደረቦችም ዻዻሳት ሆነው ቤተ ክርስቲያንን አገልግለዋል::

<< *ድንግል: *መናኝ: *ፈዋሽ: *ናዛዥ: *አበ ምኔት: *እመ ምኔት: *ጻድቅትና *ሰማዕት ለሆነች ለእናታችን ቅድስት አውጋንያ ክብር ይገባል! >>

ለእግዚአብሔርም ክብር ይሁን እኛንም በሰማዕቷ ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።
27 viewsbisrat, 17:00
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-12-12 19:58:09
24 viewsbisrat, 16:58
ክፈት / አስተያየት ይስጡ
2022-12-12 19:56:25 #ታህሳስ_4_ሐዋርያው_ቅዱስ_እንድርያስ_ሰማዕትነት_የተቀበለበት_ዕለት_ነው ::

እንድርያስ ማለት "ተባዕ" (ደፋር: ብርቱ) ማለት ነው:: ድፍረት መንፈሳዊ አለውና::
"ድፍረት መንፈሳዊ" ስለ ክርስቶስ: ስለ ቀናችው ሃይማኖት ሲሉ በራስ ላይ መጨከን: ራስን አሳልፎ መስጠት: መከራንም አለመሰቀቅ ነው:: ይሕንንም አበው "ጥብዓት" ይሉታል::

ቅዱሱ ሐዋርያ ተወልዶ ያደገው በቤተ ሳይዳ አካባቢ ሲሆን የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ትንሽ ወንድም ነው:: አባቱም ዮና ይባላል:: ገና ከልጅነቱ ጀምሮ አሣ ማጥመድን ከትልቅ ወንድሙ ተምሯል::

እድሜው ከፍ ባለ ጊዜ ኦሪትን ተምሮ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆኗል:: ከእርሱም እያገለገለ ለ6 ወራት ተምሯል:: በወቅቱ ከወንጌላዊው ዮሐንስ (ወልደ ዘብዴዎስ)  ጋር ቅርብ ባልንጀራም ነበር::

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ያን ድንቅ ምሥጢረ ሥላሴ ከተመለከቱትም አንዱ ነው:: ጌታ ከጾም (ከገዳመ ቆረንቶስ) በተመለሰ ጊዜ እንድርያስ መንፈስ ቅዱስ አነሳስቶት ተከትሎታል::

መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ "ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘያዐትት ኃጢአተ ዓለም - የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ እነሆ" ማለቱን ሰምቶ ቅዱስ እንድርያስ ጌታን ተከተለ:: በዚህም የመጀመሪያው የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመባል በቃ:: (ዮሐ. 1:47) ሊቁ ማር ገላውዴዎስም እመቤታችንን ሲያመሰግናት:- "ለሐዋርያ እንድርያስ ቀዳማዊ ማርያም ሃይማኖቱ:: (ለመጀመሪያው ሐዋርያ ለእንድርያስ ሃይማኖቱ ማርያም አንቺ ነሽ)" ብሏል:: (መልክዐ ስዕል)

ቅዱሱ ሐዋርያ ስሉጥ (ፈጣን) አገልጋይ እንደ ነበርም ወንጌል ይነግረናል:: (ዮሐ. 6:9, 12:22) ለ3 ዓመታት ከ3 ወራት ከጌታ እግር ሥር ተምሮ: በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሎ ምን ሃገረ ስብከቱ ልዳ ብትሆን ብዙ አሕጉረ ዓለምን ሰብኩዋል::

ሐዋርያው ከጌታ ጋር በመርከብ ውስጥ ተነጋገረና ቅዱስ ማትያስን ሰውን ከሚበሉ ሰዎች እጅ አዳነ:: ቅዱስ እንድርያስ 30 ቀናት የሚፈጅ የባሕር ላይ ጉዞ ለማድረግ ከአርድእቱ ጋር ወደ ወደብ ቢሔድም መርከበኞች ሁሉ አናሳፍርም በማለታቸው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወጣት መርከበኛ መስሎ ሐዋርያውንና አርድእቱን የሠላሳውን ቀን መንገድ በሰዓታት ልዩነት እንዲጨርሱ አድርጉዋል::

ቅዱስ እንድርያስም ፍጡር (እንዲሁ ሰው) መስሎት ሰብኮለታል:: መርቆታልም:: መርከበኛው ጌታችን መሆኑን ሲያውቅም ደንግጦ አልቅሷል: "ማረኝ?" ብሎታል::
ጌታችንም "አይዞህ እኔ ካንተ ጋር ነኝ" ብሎታል::

ቅዱስ እንድርያስም ለጊዜው በቤተ እሥራኤል መካከል ደፋር የነበረ ሲሆን ለፍጻሜው ግን እስከ ሞት ደርሶ ስመ ክርስቶስን በድፍረት ገልጧል::

የቅዱስ እንድርያስ ሃገረ ስብከቱ ልዳ (ልድያ) ናት:: ይህቺን ሃገር: አስቀድሞ ሊቀ ሐዋርያቱ (ትልቅ ወንድሙ) ቅዱስ ዼጥሮስ አስተምሮባታል:: ቅዱስ ዼጥሮስ ወደ ሮም ሲዘልቅ ቅዱስ እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ገብቶ ብዙ ደክሞባታል:: በቀደመው ዘመን ልዳ እንደ ዛሬው ትንሽ ሃገር አልነበረችም:: ቅዱሱ ሐዋርያ ወደ ቦታው ገብቶ: ስመ ክርስቶስን ሰብኮ ብዙዎችን ቢያሳምንም የጣዖቱ ካህናት ግን ተበሳጩ:: በእርግጥ እነርሱ የሚያጥኗቸው ድንጋዮች አማልክት እንዳልሆኑ ጠንቅቀው ያውቃሉ::

ነገር ግን ከብረው: ገነው: ባለ ጠጐችም ሆነው የሚኖሩበት ሐሰት እንዲገለጥ አይፈፈልጉምና እውነትን ከመቀበል ሐዋርያቱን ማሳደዱን ይመርጡ ነበር:: አሁንም የልዳ ከተማ ሕዝብ ማመናቸውን ሲሰሙ በቁጣ ሠራዊት ሰብስበው: ጦርና ጋሻን አስታጥቀው: ሐዋርያውን ያጠፉ ዘንድ እየተመሙ መጡ::

ቅዱስ እንድርያስ ይህንን ሲያውቅ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል "ጥዑመ-ቃል" የሚባለውን ቅዱስ ፊልሞናን (ኅዳር 27 ቀን ያከበርነውን ማለት ነው) ጠርቶ የቅዱስ ዳዊትን መዝሙር ገልጦ ምዕራፍ (113:12) ላይ ሰጠውና "ጮክ ብለህ አንብብ" አለው:: ቅዱስ ፊልሞናም በቅዱስ መንፈሱ ተቃኝቶ ያነብ ጀመር:: "አማልክቲሆሙ ለአሕዛብ ዘወርቅ ወዘብሩር:: ዓይን ቦሙ ወኢይሬእዩ:: እዝን ቦሙ ወኢይሰምዑ:: አንፍ ቦሙ ወኢያጼንዉ . . . የአሕዛብ አማልክት ከወርቅና ከብር የተሠሩ ናቸው:: ዓይን አላቸው: ግን አያዩም:: ጀሮ አላቸው: ግን አይሰሙም:: አፍንጫ አላቸው: ግን አያሸቱም . . ." አለ:: +በፍጻሜውም "ከማሁ ለይኩኑ ኩሎሙ እለ ገብርዎሙ / የሚሰሯቸው ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ" ብሎ ጸጥ አለ::

ይህንን የሰሙት ካህናተ ጣዖትና ሠራዊታቸው የልባቸው መታጠቂያ ተፈታ:: በደቂቃዎችም የመንፈስ ቅዱስ ምርኮኛ ሆነው በቅዱስ እንድርያስ ፊት ሰገዱ:: እርሱም አጥምቆ ወደ ምዕመናን ማሕበር ቀላቀላቸው::

አንድ ጊዜ ደግሞ ከልዳ አውራጃዎች በአንዱ እንዲህ ሆነ:: በጨዋታ ላይ ሳሉ የክርስቲያኑ ልጅ የአሕዛቡን ቢገፈትረው ወድቆ ሞተ:: የሟቹ አባትም የገዳዩን አባት ዮሐንስን (ቀሲስ ነው) "ልጅህን በፈንታው እገድለዋለሁ" አለው:: ቀሲስ ዮሐንስ ግን "ለመምሕሬ ለእንድርያስ እስክነግር ድረስ ታገሠኝ" ብሎ ሒዶ ለሐዋርያው ነገረው:: +በወቅቱ ቅዱስ እንድርያስ የወንጌል አገልግሎት ላይ ስለ ነበር ቅዱስ ፊልሞናን ላከው:: ፊልሞና ወደ አካባቢው ሲደርስ ሁከት ተነስቶ አገረ ገዢው ሕዝቡን ይደበድብ ነበርና ቀርቦ ገሠጸው:: "የተሾምከው ሕዝቡን ልታስተዳድርና ልትጠብቅ ነው እንጂ ልታሰቃይ አደይለም" ስላለው አገረ ገዥው ቅዱሱን አሰቀለው:: ተሰቅሎም ሳለ ይገርፉት ነበርና አለቀሰ:: ምክንያቱም ቅዱስ ፊልሞና ሕጻን ነበርና:: በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሲያለቅሱለት ቁራ: ወፍና ርግብ ቀርበው አጽናኑት:: ከእነርሱም መርጦ ርግብን ወደ ቅዱስ እንድርያስ ላካት:: ርግብ በሰው ልሳን ስትናገር የሰማት አገረ ገዢው ተገርሞ ቅዱሱን ከተሰቀለበት አወረደው:: ሰይጣን ግን በብስጭት በመኮንኑ ሚስት አድሮ ልጁን አስገደለበት:: በሃዘን ላይ ሳሉም ቅዱስ እንድርያስ ደረሰ::

በመኮንኑ ሚስት ያደረውን ሰይጣንን ወደ ጥልቁ አስጥሞ የሞተውን አስነሳው:: መጀመሪያ የሞተውን ሕጻን ደግሞ ፊልሞና አስነሳው:: በእነዚህ ተአምራትም መኮንኑ: ሕዝቡና ሠራዊቱ በክርስቶስ አምነው ተጠመቁ::

ቅዱስ እንድርያስ በእድሜው የመጨረሻ ዘመናት ከልድያ ወጥቶ በብዙ አሕጉራት አስተማረ:: ስሟ ባልተጠቀ አንዲት ሃገር ውስጥ ግን በእሳት ሊያቃጥሉት ሲሉ እሳት ከሰማይ ወርዳ በላቻቸው:: +ድጋሚ ሌሎች ይዘው አሰሩት: ደበደቡት አሰቃዩት:: በሌሊትም ጌታ መጥቶ አጽናናው::

ታሕሳስ 4 ቀን በሆነ ጊዜም ወደ ውጭ አውጥተው: ወግረውና ሰቅለው ገድለውታል::

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያው ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
26 viewsbisrat, 16:56
ክፈት / አስተያየት ይስጡ