Get Mystery Box with random crypto!

#ታህሳስ_8_የትዕግስተኛዋ_እናት_የቅድስት_እንባመሪና_ልደት_ነው። የቅድስት እንባመሪና እናትና አ | ዝክረ ብሒለ አበው

#ታህሳስ_8_የትዕግስተኛዋ_እናት_የቅድስት_እንባመሪና_ልደት_ነው።

የቅድስት እንባመሪና እናትና አባት ባለጸጋ የነበሩ፣ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ፣ መልካም ምግባር የነበራቸው ነበሩ፡፡ እንባመሪና ገና ሕፃን ሳለች እናቷ ዐረፈች፤

በዚህን ጊዜ አቧቷ ወደ ገዳም በመሄድ ሊመነኩስ ፈለገ፤ ንብረቱንም አውርሷት ለመሄድ ሲነሣ እንባመሪናም (ልጁም) አብራው መነኩሴ መሆን እንደምትፈልግ ነገረችው፡፡ ንብረቱን ሽጦ ለችግረኞች ከሰጠ በኋላ ከልጁ ጋር መንኩሶ እግዚአብሔርን እያገለገለ ለመኖር በመወሰኑ ልጁን አስከትሎ ወደ ገዳም ሄደ፡፡ ሴቶች ከወንዶች ገዳም መግባት ስለማይፈቀድላቸው ፀጉሯን ላጭቶ የወንድ ልብስ ካለበሳት በኋላ ወደ ገዳም አብረው ገቡ፤ በጾም፣ በጸሎት፣ በገድልና በትሩፋት ብዙ ዓመት ከኖሩ በኋላ የእንባመሪና አባት ታመመ፤ ልጁንም ለገዳሙ አበምኔት አደራ ሰጠና ዐረፈ፡፡

እንባመሪናም በጽኑ ተጋድሎ ሴት መሆኗን ማን ሳያውቅ በጾም፣ በጸሎትና በትሩፋት ሥራ በረታች፡፡ ታዲያ በአንድ ወቅት መነኮሳቱ ወደ መንደር ለሥራ ጉዳይ ሲላኩ እንባመሪናንም አስከትለው ተጓዙ! ለገዳሙ የሚያስፈልገውን እህል ከሰዎች በመሰብሰብ እያጠራቀመ ለመነኮሳቱ የሚሰጥ አንድ ደገኛ ሰው ነበር፡፡ እንደተለመደው የሰበሰበውን እህል ለመውሰድ ከቤቱ ገቡ፤ ምሽትም ስለነበር መነኰሳቱ በእንግድነት እዚያው አደሩ፡፡ በጠዋትም ተነሡና ወደ ገዳሙ ተጓዙ፡፡ መነኮሳቱ ሰውየው ቤት በእንግድነት ባደሩበት ዕለት አንድ ክፉ ሰው ከሰውየው ቤት ገብቶ የሰውየውን ሴት ልጆ አስነውሮ ሄደ፡፡ ሰውየው በጣም የሚወዳት በእንክብካቤ ያሳደጋት በወግ በማዕረግ የቆየች ልጁ ነበረች ግን ያ ክፉ ጎረምሳ ንጽሕናዋን አጎደፈው፤ መነኮሳቱም የተሰጣቸውን ኃላፊነት ፈጽመው ወደ ገዳማቸው ተመለሱ፡፡

ከሦስት ወር በኋላ ያ የገዳሙን ንብረት እየሰበሰበ መነኮሳቱን በመርዳት የሚያገለግለው ባለጸጋ ሴት ልጅ ነፍሰጡር መሆኗ ታወቀ፡፡ ሰውየውም በክብር፣ በወግና በማዕረግ ባል አጋባታለው እያለ ሲያስብ ድንገት አርግዛ (ነፍሰ ጡር ሆና) ሲመለከት በጣም አዘነ ፡፡  ቤተሰቦቻችን እኛ በሥርዓት፣ በጥሩ ሥነ ምግባር፣ በንጽሕና አድገን የእኛን መልካም ነገር፣ ደስታ ወግ ማዕረግን ማየት ይፈልጋሉ፡፡ ታዲያ እኛም ጥሩ ሥነ ምግባር ያለን ራሳችንን ከከንቱ፣ ከክፉ ነገር በመጠበቅ መኖር ይጠበቅብናል፡፡

ሰውየው ልጁ ድንገት ከሥርዓት ውጪ ባል ሳታገባ ልጅ ልትወልድ መሆኑን ሲመለከት በጣም አዘነ፡፡ ልጁን ከክብር ያሳነሰበትን፣ ሕልሙን ያበላሸበትን፣ ደስታውን የነጠቀበትን ፣ ሰው ማን እንደሆነ ትነግረው ዘንድ አስጨነቃት፡፡ ማን እንደዚህ እንዳደረጋት በጣም ሲጨንቃት ”ቤታችን በእንግድነት መጥተው ከነበሩ መነኮሳት መካከል ወጣቱ መነኩሴ እንባመሪና ነው‘ እንደዚህ ያደረገኝ አለች፡፡ ይህንን ያለችበት ምክንያትም ያ ከክብራ ያሳነሳት ክፉ ጎልማሳ ”እኔ መሆኔን ከተናገርሽ እገልሻለሁ‘ ብሏት ስለነበር ነው፡፡ አባትየውም ከገዳሙ ሄዶ ለአበምኔቱ አመለከተ፡፡

እንባመሪናም ባልሠራችው ሥራ፣ ባልፈጸመችው በደል ተከሰሰች፡፡ ለክብር የመጣባት ፈተና ነበርና ራሷን መግለጥ (ሴት መሆኗን) ተናግራ ”አልፈጸሙክኝም ‘ ማለት እየቻለች በዚህ የተነሣ ሴት መሆኗ እንዳይታወቅ ፣በማለት በትዕግሥት ”አዎ ፈጽሜያለው፤ ግን ይቅርታ አድርጉልኝ! ልጁ ሲወለድ አሳድጋለሁ አለች፤ አበምኔቱ በጣም አዘነ፡፡ ከመነኰሳቱ መካከል በዝሙት ተፈትኖ የወደቀ፣የአገልጋያቸውን ሰው ልጅ የበደለ መነኩሴ በገዳሙ በመገኘቱ አለቀሰ፡፡ ከዚያም እንባመሪና ከገዳም ተባረረች።

ከዚህም በኋላ ይቅርታ እንዲደረግላት ጠይቃ ከጽኑዕ ቅጣት በኋላ ከገዳሙ አቅራቢያ እንድትኖር ተፈቀደላት፡፡ የሰውየው ልጅም ወለደች፡፡ ሕፃኑንንም ታሳድግ ዘንድ ለእንባመሪና ሰጧት፡፡ በጣም አሳዛኝ ነገር ነው፡፡ ሴት ሆና ሳለ ራሷን በትሕትና ባለመግለጿ ባልሠራችው ተወንጅላ የእርሷ ያልሆነውን ልጅ በአባትነት እንድታሳድግ ተሰጣት፡፡

ይገርማችኋል እንባመሪና ያንን ሕፃን ወተት ከሰላም እረኞች እየለመነች አሳደገችው፡፡ እርሷም በጾምና በጸሎት በተጋድሎ ኖረች፡፡ ከዚያም ልጁ አደገና የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ተማረ፡፡ ከገዳም ገብቶ በዚያም መነኮሰ፤ እንባመሪናም ታማ ዐረፈች፡፡

በዚህን ጊዜ መነኮሳቱ ተሰበሰቡ ገንዘው ሊቀብሯት ሲሉም ያን ጊዜ ወንድ ሳትሆን ሴት መሆኗን ተመለከቱ በጣም አዘኑ፤ አለቀሱም፤ ባልሠራችው ሥራ ተወቅሳና ተቀጥታ፣ ያልወለደችውን ልጅ ልጅሽ ተብላ፣ ደክማ አሳድጋ፣ አስተምራና እንዲመነኩስ በማድረጓ ጽናትና ትዕግስቷን አስታውሰው አለቀሱ፡፡ ”ማሪን!‘ እያሉ ሁሉም ተጸጸቱ፣

የልጅቷንም አባት ወደ ገዳሙ አስጠሩና የሆነውን ሁሉ ነገሩት፡፡ ልጁን ያስነወረችው እርሷ እንዳልሆነች ባወቀ ጊዜ መራራን ኀዘን አዘነ፡፡ ከቅድስት እንባመሪና አስክሬን ላይ ተደፍተው ”ማሪን!‘ እያሉ አለቀሱ፡፡ የሰውየውም ልጅ እውነቱን እንድታወጣ ተጠየቀችና እንባመሪና ምንም እንዳላደረገቻት ተናገረች፡፡

ከዚህም በኋላ እርሷንም ያስነወራትንም ጎረምሳ ክፉ ሰይጣን ያዛቸውና ከእንባመሪና መቃብር ሄደው ኃጢአታቸውን በሕዝቡ ሁሉ ፊት እስኪያምኑ ድረስ እጅግ አሠቃያቸው፡፡
በእውነት የእንባመሪና ተጋድሎ ድንቅ ነው! አምላካችን በረከቷን ያድለን፤ ከእንባመሪና ታሪክ የምንማረው ትዕግሥትን ነው፡፡ ሰይጣን በሰዎች አድሮ ማንነቷን በመግለጥ ከገዳም እንድትወጣ ቢጥርም እርሷ ግን በትዕግሥት ያልሠራችውን አምና ተቀብላ ለበለጠ ክብር በቃች፡፡ ውሸት ለጊዜው ተቀባይነት ቢታገኝም እውነት ግን አንድ ቀን እንደምትገለጥና ሐሰተኞች እንዲሚያፍሩና እንደሚቀጡ ያስተምረናል፡፡ ስለዚህ በሕይወታችን ታማኞችና እውነተኞች ልንሆን ይገባል፡፡ ክብርን አለመጠበቅና ያለሥርዓት መጓዝ ትልቅ ዋጋ እንደሚያስከፍል ማስተዋል አለብን፡፡ ራሳችንን ጠብቀን መኖር እንደሚገባንም ተምረናል፤  ነገሮችን ሳንመረምርና ሳናጣራ በሰው ላይ መፍረድ እንደማይገባ፣ በጾምና በጸሎት ጠላታችን ሰይጣንን ድል እንደምናደርገው ከቅድስት እንባመሪና ታሪክ እንማራለን፡፡ 

የእግዚአብሔርን ወዳጆች የቅዱሳንን ታሪክ፣ የሕይወት ተጋድሎ፣ ክብራቸውን የምንማረው እኛም እንደነርሱ ራሳችንን ከክፉ ነገር ጠብቀንና መልካም ሠርተን መኖር እንድንችል ነው፡፡ በምንማረው ትምህርት ቅዱሳንን አርአያ ልናደርጋቸው ይገባል፤ ትሑታን፣ሰዎችን አከባሪ፣ በመሆን በቤተ ክርስቲያን እያገለገልን ልናድግ ይገባናል፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! እኛንም በትዕግስተኛዋ እናት ጸሎት ይማረን አሜን
፡፡ ይቆየን!!!