2022-04-28 19:42:43
ሰሙነ ትንሣኤ ክፍል ፪
አዳም ሐሙስ
አዳም የመጀመሪያ ሰውና የሰው ሁሉ አባት ነው፤
በ፮ኛው ቀን የተፈጠረ የሰው ሁሉ ምንጭ ስለሆነ
የሰው ዘር ሁሉ ከእርሱ ተገኝቷል፡፡ በዚህ ዕለት
ለአዳም የተሰጠው የተስፋ ቃል ስለመፈጸሙ፤
(ዘፍ. ፫÷፲፭) አዳም ከነልጆቹ በክርስቶስ ሞትና
ትንሣኤ ነጻ ስለመውጣቱ ይታሰብበታል፡፡
ክርስቶስ በተነሳበት በአምስተኛው ቀን ሐሙስ
አዳም ይባላል፤ ጌታችን አዳምን ከአምስት ቀን
ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ
ብሎ ቃል ገብቶለት እንደነበር በቀሌምንጦስ
ተጽፏል፡፡
አዳምና ሔዋን በገነት ፯ ዓመት ከቆዩ በኋላ
ትእዛዙን በመተላለፋቸው ከኤደን ገነት
አስወጣቸው (ኩፋ.፬፥፲፮፤ዘፍ.፫፥፳፫) «ብዙ
ተባዙ» ያለው ቃል እንዳይቀር በምድር ላይ
ወርደው ልጆችን ወለዱ ይላል፡፡ የተወለዱትም
ልጆችም በቁጥር ፷ እንደሆኑ (፩መቃ. ፳፰፥፮)
የተወለዱት ልጆች ደጎችና ክፉዎች እንደ ነበሩ
በአቤልና በቃየል ታውቋል፤ (ዘፍ. ፬፥፰)፤ አዳም
በዚህ ዓለም ፱፻፴ ዓመት ኑሮ ቅድመ ልደተ
ክርስቶስ በ፵፻፭፻፸ ሚያዚያ ፮ ዐርፏል፡፡
ዐርብ– ቤተ ክርስቲያን
ዐርብ የእግዚአብሔር ቅድስት ማደሪያ በሆነችው
ቤተ ክርስቲያን ተሰይማለች፤ ይህም ሁሉም
ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመባት ዕለት
በመሆኗ ነው፤ ዕለተ ዐርብ፤ የሥራ መከተቻ፤
ምዕራብና መግቢያ በሚሉት ስያሜዎችም
ትጠራለች፡፡
በዕለቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
በመልዕልተ መስቀል ያደረገውን ተአምር
በመስቀሉ ድኅነትን እንዳሳየ፤ በቀራንዮ የሕንጻዋ
መሠረት እንደተተከለላትና ሥጋ መለኮት
እንደተቆረሰላት፤ ልጆቿን ከማሕፀነ ዮርዳኖስና
ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ የምትወልድበት ማየ
ገቦ እንደፈሰሰላት ተገልጾባታል፤
(ኤፍ.፪፥፲፱፤ራዕ.፩፥፮-፰)፡፡
ቅዳሜ– ቅዱሳት አንስት
ቅዳሜ ቅዱሳት አንስት ተብሎ ይጠራል፤ ይህም
ስያሜ በስቅለት ዕለት በልቅሶና በዋይታ
የሸኙትን፤(ሉቃ. ፳፫፥፳፯) በዕለተ ትንሣኤ ሽቱና
አበባ ይዘው ወደ መቃብር የገሰገሱትን፤ ከሁሉም
ቀድሞ ጌታችን በዕለተ ሰንበት ተነሥቶ
ለተገለጸላቸው ማርያም መግደላዊት፤ የታናሹ
ያዕቆብ እና የዮሳ እናት ማርያም፤ የዘብዴዎስም
የልጆቹ እናት ሰሎሜንም መታሰቢያ ለማድረግ
ነው፤«ከሳንምንቱ በመጀመሪያዩቱ ቀን ያዘጋጁትን
ሽቶ ይዘው እጅግ ማልደው ወደ መቃብሩ
ሄዱ፤ሌሎች ሴቶችም አብረዋቸው ነበሩ (ሉቃ.
፳፬ ፥ ፩ )፡፡
እሑድ– ዳግም ትንሣኤ
«ያም ከሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን በመሸ ጊዜ
ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን ስለ ፈሩ ተሰብስበው
የነበሩት ቤት ደጁ ተቆልፎ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ
መጥቶ በመካከላቸው ቆመና÷«ሰላም ለእናንተ
ይሁን» አላቸው፤ ማቴ.፳፥፲፱፡፡ ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ተሰውሮ ከሰነበተ
በኋላ በዕለተ እሑድ በዝግ ቤት እንዳሉ ዳግም
ተገለጸላቸው፤ስለዚህም ዳግም ትንሣኤ ተባለ፡፡
( ምንጭ :-መዝሙረ ማኅሌት ወቅዳሴ፤ ሥርዓተ
አምልኮ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፤ የዮሐንስ ወንጌል
አንድምታ፤ ምዕ. ፳፥፳፬)
116 viewsbisrat, edited 16:42