Get Mystery Box with random crypto!

፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨ መግደላዊት ማርያምና የጌታችን ትንሳኤ ፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨ | ዝክረ ብሒለ አበው

፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
መግደላዊት ማርያምና የጌታችን ትንሳኤ
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
"ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም።" (ዮሐ.20:13)

=>ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ማርያም ተገልጦ የጠፉትን ነፍሳት በሚያድንበት ዘመን ከእሥራኤል አውራጃዎች በአንዱ (በመግደሎን)
ማርያም የሚሏት ሴት ትኖር ነበር:: መግደላዊት እያሉ የሚጠሯት ሐዋርያት (ወንጌላውያን) ናቸው:: ለምን እንዲህ ብለው ጠሯት ቢሉ:- በዘመኑ ማርያም የሚባሉ ብዙ ሴቶች ነበሩና ከእነሱ ለመለየት ነው:: አንድም ሃገሯ (ተወልዳ ያደገችበት) ነውና:: +ማርያም መግደላዊት ይህ ቀረሽ የማይሏት ቆንጆ ነበረች ከዚህም የተነሳ ሰዎች ያደንቁዋት: ወንዶች ይከተሏት ነበር:: በዚህም 7 አጋንንት ተጠግተው 7 ዓይነት ኃጢአትን ያሠሯት ነበር:: በተለይ ደግሞ በዝሙት: በትውዝፍት (ምንዝር ጌጥ) እና ትዕቢት በእጅጉ የታወቀች ነበረች:: +በእንዲህ ያለ ግብር ጸንታ ለዘመናት ኖረች:: በዚያ ወራት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋችንን ተዋሕዶ ያስተምር ነበርና ስለ እርሱ ሰማች:: "ጌታ ኃጥአንን አይጸየፍም (ይቀበላል): አጋንንትንም ያስወጣል" ብለውም ነገሯት:: ጥሪው የእግዚአብሔር ነውና ማርያም መግደላዊት አልዘገየችም:: +ወደ እርሱ ሔዳ ጌታ ባያት ጊዜ ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ነውና አቀረባት:: በቸርነቱም ከራስ ጸጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ የሞሉትን 7 የአጋንንት ነገድ አስወጣላት:: በዚያች ሰዓት ዕለቱኑ እንደተወለደ ሕጻን ከነበረባት ችግር ሁሉ ንጹሕ ሆነች:: ጌታም ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት አንዷ ትሆን ዘንድ መርጦ ተከታዩ አደረጋት:: +ቅድስት ማርያም ከዚህች ቀን ጀምሮ ፍጹም ተቀየረች:: እርምጃዋ ሁሉ የተባረከና የንጽሕና ሆነ:: ጌታን እስከ ዕለተ ሕማሙ ድረስ በመዓልትም: በሌሊትም በቅን አገለገለችው::
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨

ጌታችን ስለ እኛ መከራን በተቀበለባት በዚያች ዕለተ ዐርብም ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ከጐኑ ነበረች:: +ከግርፋቱ እስከ ስቅላቱ እያለቀሰች ተከትላዋለች:: በእግረ መስቀሉ ያለቅሱ ከነበሩ ቅዱሳት አንስትም አንዷ እርሷ ነበረች:: (ዮሐ. 19:25)
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨

ዮሴፍና ኒቆዲሞስ የተባሉትም እግዚአብሔር የባረካቸው ደጋግ ሰዎች የጌታችንን ቅዱስ ሥጋ ከጲላጦስ ተቀብለው እያመሰገኑ በንጹሕ በፍታ ወይም የመግነዝ ጨርቅ ሲከፍኑት፤ በአዲስ መቃብርም አኑረው የመቃብሩን ደጃፍ ሲዘጉ መግደላዊት ማርያም በመቃብሩ አንጻር ተቀምጣ ትመለከት ነበር፡፡ አይሁድ የጌታችን መቃብርን እንዲጠብቁ ጠባቂ ወታደሮችን አዝዘው ነበር፡፡ መግደላዊት ማርያም እሑድ ዕለት በጠዋት የጌታችንን ቅዱስ ሥጋ ለመቀባት ያዘጋጀችውን ሽቱ ይዛ ሌሎቹንም ሴቶች አስከትላ ወደ መቃብሩ ወጣች፡፡ ወደመቃብሩ ስትደርስ የመቃብሩ ድንጋይ ተንከባሎ ነበር፡፡ በድንጋጤ ወደ ውስጥ ስትገባም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አላገኘችውም፡፡ የጌታችንን ሥጋ ማን እንደወሰደው ልታውቅ አልቻለችም፡፡ እየሮጠችም ወደ ሐዋርያት መጥታ “ጌታን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም” አለቻቸው፡፡ ጴጥሮስና ዮሐንስ ይህን በሰሙ ጊዜ ወጥተው ወደ መቃብሩ ሮጡ፡፡ ወደ መቃብሩ ውስጥ ሲመለከቱም የተከፈነበትን ጨርቅ ብቻ ተመለከቱ፡፡ ስለዚህም ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡ መግደላዊት ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ ውጭ ቆማ ቆየች፡፡ ድንገት ወደ መቃብሩ ዝቅ ብላ ብትመለከት ሁለት መላእክት የጌታችን ሥጋ በነበረበት ቦታ ላይ ተቀምጠው አየች፡፡ እነርሱም ለምን እንደምታለቅስ ጠየቋት፡፡ እርስዋም “ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም” አለቻቸው፡፡ ይህንንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል አንድ ሰው ቆሞ አየች፡፡ የአትክልት ቦታው ጠባቂ መስሏት፡፡ ሰውየው “ለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ?” አላት እርሷም ,,የጌታዬን ሥጋ አንተ ወስደኸው ከሆነ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ” አለችው፡፡  ያነጋግራት የነበረው ሰው ግን የአትክልት ቦታ ጠባቂው አልነበረም፡፡ ማን እንደሆነ አወቃችሁ?  የሚወደን ስለ እኛ የሞተልን ከሙታንም መካከል ተለይቶ በሦስተኛው ቀን የተነሣው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር፡፡ በመጨረሻም በስሟ ማርያም ብሎ ሲጠራት አወቀችው፡፡ ከሙታን ተለይቶ እንደተነሣ ለሐዋርያት በሙሉ እንድትነግር ላካት፡፡ እርሷም በደስታ ወደ ሐዋርያት ተመልሳ ነገረቻቸው::
ጌታችንም ከእመቤታችን ቀጥሎ ከፍጥረት ወገን ትንሳኤውን ያየችና የመጀመሪያዋ የትንሳኤው ሰባኪ ትሆን ዘንድ አደላት::
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
ክርስቲያኖች በሙሉ በትንሣኤ በዓል በደስታ እንዘምር አምላካችንንም እናመስግን፡፡  ይህ ታሪክ የሚገኘው ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መካከል በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 20 ቁጥር 1 ላይ ነው፡፡

፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
መልካም የትንሳኤ በዓል ይሁንላችሁ!!!
፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨